Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትግል እና ዓላማው

0 1,024

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትግል እና ዓላማው

                        ኢዛና ዘመንፈስ

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከፈተው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተሟላ ሀገር አቀፋዊ የጋራ ግንዛቤ  በማስጨበጥ ረገድ እምብዛም ውሃ የሚያነሳ ስራ አለመሰራቱን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ የተነሳም፤ የደርግ ኢ.ሰ.ፓ ወታደራዊ አገዛዝ ይገለገልበት የነበረውን ፈርጀ ብዙ የአፈና መዋቅር፤ በትጥቅ ትግል ሂደት አስወግደው ወደስልጣን ስለመጡት የፖለቲካ ሃይሎች መሰረታዊ ባህሪ ህዝቡ ማወቅ የሚገባውን ያህል እንዲያውቅ ያደረገ ክፍተት እንደተፈጠረ ይታመናል፡፡

አብዛኛዎቹ አገራችን ሊሂቃን ከየራሳቸው ፖለቲካዊ የጀርባ ታሪክ ጋር በተያያዘ  ምክንያት፤ አዲሱን የስር ነቀል ለውጥ  የሚያዩበት መነፅር ሚዛናዊነት የጎደለውና እውነታውን ለማፋለስ ባለመ መልኩ የሚሰነዘር ጭፍን ተቃውሞ ላይ የተመሰረተ ውግዘትን ማስከተሉ ለተፈጠረው የግንዛቤ ክፍተት እንደዋነኛ አሉታዊ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ የተነሳም፤ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ህዝቦች የተበሰረው የግንቦት 20 ሀገር አቀፋዊ ድል ተከትሎ ወደ ፖለቲካዊ ስልጣኑ ስለመጡት ሃይሎች አጠቃላይ ቁመና፤ በቅጡ ለመረዳት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የማስጨበጥ አስፈላጊነት ጉዳይ የሚገባውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡

ለ17 ዓመታት በዘለቀ ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ሂደት ውስጥ አልፈው ደርግ የሚያህል እጅግ በጣም ግዙፍ የጦር ኃይል የነበረው ወታደራዊ መንግስት ለማስወገድ የበቁት የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለያዩ ተፅእኖ ምክንያት ክፉኛ መፈተናቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡  

ለዚህም  የቀድሞው የኢፌዴሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት ቀርበው “የጦርነት እሳትና የትጥቅ ትግል ውጣ ውረድ ያላንበረከካቸውን ጓዶቻችንን ስኳር አንበርክኳቸዋል” ሲሉ የተደመጡበትን ክስተት ጨምሮ፤ ሌሎች የኢህአዴግ አንጋፋ የአመራር አካላት በየአጋጣሚው ተመሳሳይ ሃሳብ ሲያንፀባርቁ ስለመስተዋላቸው ማስታወስ ይቻላል፡፡ በተለይም ደግሞ የህወሐት መስራቹ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ከሻዕቢያ ወረራ ቀደም ብሎ መቐለ ውስጥ በተካሔደ  የኢህአዴግ ከፍተኛ የአመራር አካላት ስብሰባ ላይ “ደርግን ካስወገድን  በኋላ የትግሉን መሰረታዊ ዓላማ የመዘንጋት አደጋ እያጋጠመን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል” የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ መስማቴን በዚህ አጋጣሚ ላነሳ  እፈልጋለሁ፡፡

ይህ የትጥቅ ትግሉ ዘመን ኢህአዴግ የፖለቲካ ባህል ከደርግ ውድቀት በኋላ እየተሸረሸረ ስለመሆኑ ሲያስገነዝቡም አቶ ዓባይ ፀሐዬ “የከተማ ነዋሪው ህብረተሰባችን መካከል ስንገባ እየገጠመን ያለው ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ከምናውቀው አርሶ አደር ህዝብ አስተሳሰብ ጋር የሚቃረንና ወደ ስነ-ምግባራዊ ንቅዘት እንድንዘፈቅ የሚገፋፋ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮብናል” ነበር ያሉት፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ የ1993ቱን ተሃድሶ አካሔዶ ችግሩን ትርጉም ባለው ስፋትና ጥልቀት ለመቅረፍ የሞከረበትን የመፍትሔ እርምጃ መውሰዱ የሚዘነጋ ጉዳይ አይሆንም፡፡

በዚያን ጊዜው የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች የተሃድሶ መድረክ፤  የፖለቲካ ሃይሎች ከደርግ ውድቀት በኋላ እጅጉን ሲፈታተናቸው ስለቆየው  የግል ኑሮ ለማመቻቸት ሲባል የትግሉን መሰረታዊ ዓላማ የመዘንጋት አዝማሚያ በግልፅ አንስቶ የገመገመ የጋራ አቋም ላይ የተደረሰበት አመርቂ ውጤት እንደተገኘበት ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግን የሚያህል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አዳዲስ አባላትን ከስር ከስር እያፈራ ቀጥሎ የአውራ ፓርቲነትን መዋቅራዊ ቁመና ለመያዝ የበቃ መሰረተ ሰፊ የፖለቲካ ግንባር፤ አንድ ወቅት ላይ በተካሔደ የተሃድሶ መድረክ ብቻ ከመሰል የስነ-ምግባራዊ ንቅዘት አደጋ የፀዳ ማድረግ እንደማይቻል ህዝቡ በየአጋጣሚው ሲገልፅ ይደመጣል፡፡  

ኢህአዴግ በገመገመበት የቅርብ ጊዜ መድረክ “መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ መብትና ጥቅም ማረጋገጫነት ከማዋል ይልቅ ለየግል ፍላጎታችን ማሟያ አድርገን እየተገለገልንበት ነው” የሚል አቋም ላይ ደርሶ የለ? ስለዚህም ትግልና የግል ፍላጎት በጎላ መልኩ የሚገለፅ ፍልሚያ እንደያዙ ለመረዳት የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ የተመለከተውን የግምገማ ውጤት ማየት  ይበቃል የሚል እምነት አለኝ ፡፡

ምክንያቱም ገዢው ፓርቲ በዚያ የግምገማ ውጤት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ “የመንግስት ስልጣንን አስፈላጊነት በተመለከተ እንደ ሀገር ያለው አረዳድ የተዛባ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አመራሩም የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣና ህብረተሰቡን በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት የሚያማርር፤ ብልሹ አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንዲመጣ እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር በትግል እየተደፈቀ ከመሄድ ይልቅ፤ ልማታዊ አስተሳሰብን የሚያቀጭጭ የበላይነት እንዲይዝ አድርጓል” ሲል የማያሻማ አቋሙን ለህዝቡ አሳውቋል፡፡ ኢህአዴግ በጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ላይ በተለይም የራሱን ውስጣዊ ድክመቶች ለመቅረፍ ያለመ ጥረት ሲያደርግ በመቆየቱ ተደጋግሞ የተነገረን ጉዳይ እንደሆነም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በዚህም በከፍተኛው አመራር አካል ግምገማ ማጠቃለያ ላይ የጥልቅ ተሃድሶውን አስፈላጊነት ለመላው የሃገራችን ህዝቦች ይፋ ያደረገበት መግለጫ በህብረተሰቡ ዘንድ አሳድሮ የነበረውን ተስፋ ያህል ተጨባጭ ውጤት ያመጣ የእርምት እርምጃ ሲወሰድ እየተስተዋለ አይደለም የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ የሚደመጡ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም፤ በተለይ ለፌደራሊዝም ስርዓታችን በጎ አመለካከት ያላቸውና የሥር ነቀል ለውጥ ሂደቱ ላይ ሲቃጣ የሚስተዋለውን ተደጋጋሚ የቅልበሳ አደጋ፤ የሚጋብዙ የመልካም አስተዳደር እጦትና እንዲሁም መሰል ችግሮች ትርጉም ባለው መልኩ ተፈትተው ማየትን የሚሹ ወገኖች “መንግስት የጥልቅ ተሃድሶውን መድረክ ሲጀምር ለሃገራችን ህዝቦች የገባውን ቃል አክብሮ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን መታገል ረገድ መሬት ላይ ወርዶ ሊታይ የሚችል ተግባራዊ የእርምት እርምጃ እስካልወሰደ ልክ ራሱን በራሱ ጠልፎ ለመጣል እንደመረጠ ይቆጠራል” እሰከ ማለት ይደርሳሉ፡፡

ሌላው በዚህ አጋጣሚ ሳላነሳው ማለፍ የማይኖርብኝ ተያያዥ ጉዳይ ደግሞ ዘንድሮ የተከበረውን የግንቦት 20 ድል በዓል 26ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየት የሰጡ የኢህአዴግ ነባር ታጋዮች፤ ትግልና የቅንጦት ኑሮ ተፋጥጠው የሚስተዋሉበትን አግባብ ሲገልፁ ስለመደመጣቸው ነው፡፡

በዚህ መሰረትም ከብአዴን መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ህላዊ ዮሴፍ፤ እንዲሁም የህወሃቱ ነባር ታጋይ አቶ ተክሌ ሽፈራው እና ለጊዜው ስማቸውን የዘነጋሁት የኦህዴድ ሴት ነባር ታጋይ ናቸው፡፡ ሶስቱም አንጋፋ የገዢው ፓርቲ ታጋዮች የየድርጅቶቻቸውን የትጥቅ ትግል ዘመን በፈርጀ ብዙ ወጣ ውረድና መስዋዕትነት የታለፈ ታሪክ ለሬዲዮ ጣቢያው አድማጮች ያስታወሱበት ቆይታ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት ፤ ለዚህ መጣጥፌ ማዳበሪያ የአቶ ተክሌ ሽፈራው ንግግር ለአብነት ያህል አሳጥሬ እጠቅሳለሁ፡፡

ኢህአዴግ የፖለቲካ ኃይሎች ከትናንት እስከ ዛሬ የሚታወቁበትን ወይም የቆሙለትን ህዝባዊ ዓላማ ለማሳካት ሲባል በትጥቅ ትግሉ ዘመን የታለፈበትን ውስብስብ ፈተና፤ ከአሁኑ ሁኔታ ጋር እያነፃፀሩ ለማስረዳት የሞከሩበት አግባብ “ያኔ እያንዳንዷን ድርጅታዊ ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲባል የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ የህይወት መስዋዕትነትን እስከ መክፈል ሊደርስ የሚችል አደጋን መጋፈጥ የሚጠይቅ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን ግፋ ቢል የምቾት መስዋዕትነት መክፈል ነው ሊጠይቀን የሚችለው ትግሉ” የሚል ሆኖ ስላገኘሁት ወድጀዋለሁና ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy