Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሁንም ጊዜው አልረፈደም!

0 410

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁንም ጊዜው አልረፈደም!

                                                            ደስታ ኃይሉ

የሳዑዲ መንግስት ያስቀመጠው የሶስት ወራት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ መንግስት በርካታ ተግባሪችን ከውኗል። መንግስት የጊዜ ገደቡ ካለቀ በዜጎቹ ላይ ሊከተል የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ ከወዲሁ በመገንዘብ ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፤ የምህረት አዋጁ እንደወጣ ሰሞን ስደተኞቹ ያለ ችግር ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዲመለሰሱ ከሳዑዲ መንግስት ጋር የሚነጋገር ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ቡድን ሪያድ በመገኘት ኢትዮጵያዊያኑ ንብረታቸውን ይዘው እንዲገቡ በማድረግ ስምምነት አድርጓል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁም ተመላሽ ስደተኞች ወደሚገኙበት የተለያዩ ስፍራዎች በማቅናት አበረታትተዋቸዋል።

መንግስት ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው ሲገቡም 21 የሚሆኑ የመገልገያ ዕቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል። እነዚህ ከታክስ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱ ቁሳቁሶች ዝርዝር፣ ስደተኞች ጅዳና ሪያድ በሚገኙ የኤምባሲው ቢሮዎች እንዲሁም የጉዞ ሰነዶች በተዘጋጁላቸው ሁሉም ቦታዎች ማግኘት እንደሚችሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።

ከዚህ በተጨማሪ ተመሳሳይ የጉዞ ሰነድ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት መቋቋማቸው ይታወቃል። ከእነዚህ ማዕከላት ውስጥ በሪያድ ሚሲዮን፣ ቡረይዳና ዋዲ ደዋስር (ሪያድ አካባቢ)፣ እንዲሁም በጅዳ ሚሲዮን በመካ፣ ከሚስሸጥ፣ ጄዛንና መዲና የሚገኙት የጎዞ ማሳለጫ ቦታዎች ይጠቀሳሉ። ሌሎችም በዚያች ሀገር ውስጥ ዜጎቻችን የሚገኙበት ቦታዎች ሁሉ የሚወጡበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

የመንግስት ጥረት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የሀገሪቱ ህዝቦች ንብረት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ባወጣው የምህረት አዋጅ ምክንያት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ያለ አንዳች ችግር በፍጥነት መጓጓዝ እንዲችሉ አድርጓል። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ተደርገውም ወደ ሀገር ቤት የተመለሰው ዜጋ የተጠበቀውን ያህል አይደለም።

ይህም በዚያች ሀገር የሚገኙት ዜጎች የተዘናጉ መሆናቸውን ያሳያል። ሆኖም አሁንም ጊዜ ስላልረፈደ ዜጎቻች ወደ ሀገራቸው መመለስ ይችላሉ። አሁንም ቢሆን የደላላዎችን ወሬ ሊሰሙ አይገባም። ደላላዎቹ ዜጎችን ከችግር ሊታደጓቸው አይችሉም።

ምንም እንኳን ህገ ወጥ ደላላዎች ‘የሳዑዲ መንግስት ምንም አያደርጋችሁም’ በማለት የተሳሳተ ወሬ በስደተኞቹ መካከል እየነዙ ቢሆንም፤ ሃቁ ግን ጊዜው ሲደርስ በህገ ወጥ ዜጎች ላይ ስለሚወሰደው ርምጃ የሪያድ የፀጥታ ክፍሎች እየተወያዩበት ነው።

ይህም ልክ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት የሪያድ መንግስት እንዳደረገው ህገ ወጦች ብሎ የፈረጃቸው ዜጎችን ንብረት በመውረስና በማንገላታት ጭምር ከሀገሩ እንደማያባርር ማንም ዋስትና ሊሰጥ የሚችል አይመስለኝም—የየትኛውም ሀገር መንግስት በህገ ወጥ ስደተኞች ላይ ስለሚወስዳቸው ማናቸውም ርምጃዎች ወሳኙ እርሱ ብቻ ስለሆነ ነውና።

ታዲያ ህገ ወጥ ደላላዎቹ ይህን የተሳሳተ ወሬ እየነዙ የሚገኙት ባለማወቅ ለእነርሱ አሁንም ገንዘብ ከፍለው የሚሄዱት ወገኖች እንዳይቀሩባቸው በመስጋት መሆኑን ሰነዱን ያልወሰዱት ዜጎች ሊያውቁ የሚገባ ይመስለኛል። ህገ ወጥ ደላለዎቹ የሳዑዲ መንግስት ከሚወስዳቸው ርምጃዎች ሊያስጥሏቸው እንዳማይችሉም እንዲሁ።

ያም ሆኖ ህገ ወጥ ደላላዎቹ ያሻቸውን ቢያወሩም፤ የሳዑዲ መንግስት ፍላጎት ግን የየትኛውም ሀገር ዜጋ በህጋዊ መንገድ በሀገሩ ውስጥ ተመዝግቦ እስካልኖረ ድረስ ከሀገሩ ማስወጣት መሆኑን ዜጎቻችን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም የተጀመረው የምህረት አዋጅ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ይጠናቀቃል። ይህም የቀሩት ቀናት ጥቂት መሆናቸውን ያሳያል። ሆኖም አሁንም ጊዜው ስላልረፈደ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የጉዞ ሰነዶችን መውሰድ ያለባቸው ይመስለኛል—የአንድ ቀን ዕድሜም ቢሆን ከጥፋት ይታደጋልና።  

በእኔ እምነት እነዚህ በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥነት በሳዑዲ ውስጥ የሚገኙት ዜጎች ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ፍላጎት ካላቸው በህጋዊ መንገድ ወደዚያው ማቅናት ይችላሉ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ መንግስቶች ዜጎች በህጋዊ መንገድ ተገቢውን ስልጠና ወስደው ወደ ሳዑዲ እንዲሄዱ የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ በመፈራረማቸው ነው። እናም ይህን መፃዒ ዕድል ለመጠቀም በዚያች ሀገር የሚገኙት ዜጎች በቅድሚያ ወደ ሀገር ቤት መምጣት ይኖርባቸዋል። ይህ ወርቃማ ዕድል ሊያመልጣቸው የሚገባ አይመስለኝም።

ታዲያ እዚህ ላይ በአንዳንድ ወገኖች የሚነሳ አንድ የተሳሳተ አስተሳሰብን ማጥራት የሚገባኝ ይመስለኛል። ይኽውም ‘ለሳዑዲ ተመላሾች ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ሲባል ምን ማለት ነው?’ የሚለው ሃቅ ነው። ርግጥ መንግስት ለዜጎቹ አቅሙ በፈደቀ መጠን ድጋፍ እያደረገ ነው። ቀደም ሲል በማሳያነት ያቀረብኳቸውና ከሳዑዲ መንግስት ጋር ዜጎች በያሉበት ቦታ ሁሉ የጉዞ ሰነዶችን እንዲወስዱ የማመቻቸት፣ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የዜጎቹን ህይወትና ንብረት ለመታደግ ያደረጋቸው ስምምነቶች፣ ዜጎቻችን ንብረታቸውን ሳይቀሙና አሻራ ሳይሰጡ እንዲወጡ እንዲሁም አየር መንገዱ መዳረሻዎቹን እንዲጨምርና የትኬት ዋጋም በግማሽ እንዲቀንስ ማድረጉ ብሎም ሌሎች ጥረቶች ማከናወኑን መጥቀስ ይቻላል።

በእኔ እምነት ይህ የመንግስት ጥረት አቅም በፈቀደ መጠን የተከናወነ ነው። ስደተኞቹ ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላም እንደ ማንኛውም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ እየተሳለጠ በሚገኘው የልማት ስራዎች ውስጥ በአቅማቸው ሊሳተፉ ይችላሉ። በቂ ጥሪት ያላቸውም ሀገራቸው ውስጥ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት መስክ በግልም ይሁን በጥምረት ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ይህ ሀገር በዕድገት ላይ የሚገኝ በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በየደረጃው በልማቱ ላይ እንደሚያደርገው አስተዋፅኦ ተጠቃሚ እንደሚሆነው ሁሉ፤ እነርሱም በልማቱ ላይ በሚጫወቱት ሚና ልክ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት ይህን ሁኔታ ያመቻቻል።

ይህን ምቹ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። ከዚህ ቀደም ይገቡ የነበሩት ቁሳቁሶች ላይም ለውጥ ተደርጓል። መንግስት እነዚህን ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ የፈቀደው ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ለማበረታታት ነው። በአሁኑ ወቅት መንግስትና ህዝቡ በሀገራችን ውስጥ እየፈጠሩት ያለው ሁኔታ ለሚሰራ ማንኛውም ዜጋ የተመቻቸ ነው።

በሳዑዲ መንግስት እንዲወጡ የተጠየቁ ዜጎቻችን ማናቸውንም የስራ ዓይነቶች የሚያውቁ ናቸው። የስራ ክቡርነት ባህልንም እንዲሁ። እናም በዚህ በተመቻቸው ሀገራዊ የስራ ድባብ ውስጥ ባላቸው አቅም ስራ በመፍጠር ጠንክረው ከሰሩ ይለወጣሉ። ይህን እውነታ አውቀውም አሁንም ጊዜው ስላልረፈደ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy