Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አልተቀበልኩትም ስም ከምግባር ሲገጥም!

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አልተቀበልኩትም ስም ከምግባር ሲገጥም!

ሰለሞን ሽፈራው

“ስምን መልአክ ያወጣዋል” የሚለው አገርኛ ተረት ምንን እንደሚያመለክት ማብራሪያ የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ይህን ምሳሌያዊ አነጋር የሚያስከትለው፤ አንድ ሰው ለስሙ የሚመጥን ምግባረ መልካም ስብዕናን የተላበሰ ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ መገመት የሚከብድ አይደለምና ነው፡፡ በአንፃሩ “መልከ ጥፉ፤ በስም ይደግፉ” የሚባልላቸው ሰዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡

ለአብነት ያህልም አንድ ደስታ የሚባል ሰው በነገረ ስራው ሁሉ ሌሎችን የሚያስከፋ ሆኖ ሲገኝ “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ” የሚለውን አሽሙር አዘል አማርኛ የሚጋብዝ ተደርጎ ሊወስድ ይቻላል፡፡ ቅድስት የምትባል ምግባረ መልካም ሴት ወይዘሮ ያጋጠመችው ያገሬ ሰው “ስምን መልአክ ያወጣዋል” ሲል አድናቆቱን ለመግለፅ መሞከሩም አይቀሬ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን እኔ በዚህ መጣጥፍ ላነሳ የፈለግኩት፤ የዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም ስም ከተግባራቸው ጋር የገጠመ (የተጣጣመ) ስለመሆኑ የመኪያወሳ መሰረተ ሀሳብ ነውና አሁን በቀጥታ ወደዋናው ነጥብ አልፋለሁ፡፡

እንግዲያውስ የዶክተር ቴዎድሮስ አባት ስም (አድሐኖም) ወደ አማርኛ ሲተረጎም “አዳናቸው” እንደማለት መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡ እናም ከዚህ ቀጥተኛ ትርጉም አኳያ ሲታይ የዶክተሩ ሙሉ ስም ቴዎድሮስ አዳናቸው ማለት እንደሆነ አድርገን በመውሰድ፤ እንዴት ከምግባራቸው ጋር እንደሚገጥም ለመመልከት እንሞክር፡፤ ስለዚህም፤ ዛሬ ላይ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለመመረጥ ስለበቁት ጎልማሳ የህክምና ሙያ ምሁር ከማንሳቴ በፊት፤ የህፃኑ ቴዎድሮስ አድሐኖም ገ/እየሱስ የልጅነት ዘመን ህልም ምን ይመስል ነበር? ለሚለው ጥያቄ የተወሰነ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ነጥቦችን እንመለከት ዘንድ ጠቃሚ መስሎ ይሰማኛል፡፡

ይሄን ስልም ደግሞ፤ ዶክተሩ ራሳቸው ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በተመረጡበት የጀኔቫው መድረክ ላይ ለምን የህክምና ሙያን ሊመርጡ እንደችሉ ተጠይቀው “ገና ልጅ እያለሁ አንድ ወንድሜ ታመመና የህክምና ዕርዳታ ቢያገኝ ኖሮ በቀላሉ ሊድን ይችል የነበረ ሲሞት ስላየሁ ነው ሳድግ ዶክተር መሆን አለብኝ ብዬ የወሰንኩት” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሼ፤ ታዲያ ባለታሪካችን ያን በጨቅላነት ዕድሜያቸው ያለሙትን የማለዳ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሲሉ ያሳዩት ጥረት ሁሉ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ህፃናት በአርአያነት ሊጠቀስ የሚገባው አይደለምን? ወደሚል ነጥብ የሚወስድ አስተያየት ለመሰንዘር ፈልጌ ነው፡፡

ስለሆነም፤ ከዚህ አኳያ የዛሬው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም፤ የልጅነት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሲሉ ያሳዩት ያላሰለሰ ጥረትና የተቀዳጁት ስኬት በእርግጥም ለአርአያነት የሚበቃ እንጂ ተራ ውዳሴ ከንቱ አይደለም የሚል እምነት ነው ያለኝ እኔ፡፡ ለዚህም ደግሞ፤ ከትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቹ አብራክ የተከፈለው ህፃን ቴዎድሮስ አድሐኖም ተወልዶ ባደገባት መቐለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው አፄ ዮሐንስ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማር ጀምሮ፤ ያሳይ ስለነበረው ትጋት ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ጓደኞቹ ጥቂት እንዳልሆኑ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህልም፤ ከዶክተር ቴዎድሮስ ጋር አብረው ከተማሩት የመቐለ ልጆች አንዱ መሆኑን ያጫወተን ታጋይ አርቲስት ኢያሱ በርሔ “ቴዎድሮስ አድሐኖም ጎበዝ የህክምና ዶ/ር የመሆን ህልም እንደነበረው እኔራሴ አውቅ ነበር” ሲል መናገሩ ትዝ ይለኛል፡፡

እንግዲህ የባለታሪካችን ወላጆች ልክ እንደማንኛውም እናትና አባት ሁሉ ገና ያኔ ወደዚች ምድር ሲመጣ ለህፃን ልጃቸው ያወጡለት የተፀውኦ ስም ከወደፊቱ የህይወት ዘመን ጥረትን የሚጠይቅ መልካም ምግባሩ ጋር እንዲገጥም ሲሉ ያደረጉት ነበር ለማለት የሚያስደፍር ምንም ዓይነት ምክንያታዊ መከራከሪያ ማቅረብ ባይቻልም፤ ዛሬ ላይ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለመመረጥ የበቁት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም፤ዕልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን አክመው ወይም ደግሞ አሳክመው ስለማዳናቸው ግን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እናም ስለኚሁ ትጉህ ምሁር ዜጋችን የምናውቀው እውነት፤ ስማቸውን ከተጨባጩ ተግባራዊ ጥረታቸው ጋር እንዲጣጣም ያደረገ ሆኖ ስለማግኘታችን እንመሰክር ዘንድ አነሆ ህሊናችን አስገድዶናል፡፡

ስለዚህም እኔ በግሌ፤ የዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖምን የአመራር ሰጭነት ብቃትና ትጋት መረዳት የጀመርኩት፤ እርሳቸው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ቤተሰብ ልጠይቅ ወደ ገጠራማው የክልሉ አንድ አካባቢ በመሔዴ ምክንያት ያየሁትን ለውጥ ተከትሎ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ በመላው የኛ ወረዳ ገጠራማ ቀበሌዎች የሚኖሩ የእናት-የአባት ወገን ዘመዶቼን ለመጠየቅና ከረጅም ጊዜ መለያየት የሚመነጭ ናፍቆቴን ለመወጣትም ጭምር ስንቀሳቀስ የታዘብኩት አጠቃላይ እውነታ፤ እኔ ከዚያን ጊዜ በፊት ለማውቀው የአገር ቤት ኑሮ እንብዛም ያልተለመደ ሆኖ አግኝቼዋለሁና ነው፡፡ በተለይም የአካባቢው አርሶ አደር ህብረተሰብ የየግል ንፅህናውን በአግባቡ ስለመጠበቅ አስፈላጊነት እንዲገነዘብና ታሞ ከመማቀቅ ይልቅ አስቀድሞ መጠንቀቅን ባህል እንዲያደርገው በማስተማር ረገድ የክልሉ ጤና ቢሮ የመደባቸው ባሙያዎች የሚጫወቱትን አውንታዊ ሚና ሳይ የተለየ የደስታ ስሜት ተሰምቶኝ እንደነበር ነው ትዝ የሚለኝ፡፡

እንግዲያውም ከዚሁ ለኔ ያልተለመደ (አዲስ ነገር) ሆኖ ከተሰማኝ የግል ንፅህና አጠባበቅ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ አንዱ አርሶ አደር ዘመዴ ያኔ በጨዋታ መሐል ምን ብሎኝ እንደነበር ማውሳት የማህበራዊ ለውጡን ትክክለኛ ድባብ (ገፅታ) የሚያመለክት ሊሆን ይችላልና የማስታውሰውን ያህል አንስቼ ላውጋችሁ፡፡ ማለትም፤ ለወትሮው ገጠር ስሔድ አጋጥሞኝ  የማያውቅ አዲስ ክስተት ሆኖ ስላገኘሁት፤ እያንዳንዱ አባወራ ገበሬ የየራሱን የመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ እየማሰ በጨረቃ አጥር ከልሎ ሲጠቀም የሚስተዋልበት አግባብ እንዳስገረመኝ ስነግረው ለአርሶ አደሩ ዘመዴ “አሀ እንደ ድሮው በየእዳሪው መፀዳዳትማ ከማሳፈርም አልፎ የሚያሳስር ጭምር ከሆነ ቆየ እኮ አጎቴ!” ሲል ነበር የመለሰልኝ፡፡

የክልሉ መንግስት በእያንዳንዱ የቀበሌ ገበሬ ማህበር የመደባቸው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የአርሶ አደሩን ህብረተሰብ ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ስለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ሲነግረኝም “አታይም እንዴ ልክ እንደ ከተሜዎቹ በየደጃፋችን ከጀሪካን የተበጀ እጅ መታጠቢያ ተቀምጦ” ብሎ ጀመረና “ሳሙና የመግዛት አቅም ባይኖረን እንኳን እጃችንን በአመድ ፍትግ አድርገን ሳንታጠብ ምግብ እንዳልበላ ነው የጤና ባለሙያዎቹ አጥብቀው ያስጠነቀቁን” በማለት ነው ያጠቃለለው ገበሬው ዘመዴ፡፡ ይህ እንግዲህ መደበኛ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና ኬላ በእያንዳንዷ የገጠር ገበሬ ማህበር ተገንብቶ ስራ መጀመሩን  ተከትሎ እየተስተዋለ ያለውን ተጨባጭ ለውጥ የሚያመለክት የነዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም ውጤታማ ጥረት መገለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡

መቸስ እንደ ኢትዮጵያ ስር የሰደደ ድህነትና ኋላ ቀርነት ያለቅጥ ተንሰራፍቶ በቆየበት ሀገር ውስጥ የሚኖርን የገጠር ህዝብ ወደ ተሻለ የአኗኗር ዘይቤና ዘመናዊነት ለመውሰድ ሲባል የሚደረግ ጥረት መጀመር ያለበት ከዚህ ውጭ ሊሆን እንደማይችል ይሰማኛል፡፡ እናም ይሄን የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ዶክተር ቴዎድሮስን ከትግራይ ክልል አምጥቶ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሆኑ ማድረጉ ተገቢ ውሳኔ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ደግሞ፤ ሰውየው የሀገሪቱን የጤና ሴክተር በመሩባቸው ዓመታት ውስጥ ስለተመዘገበው አመርቂ ውጤት የዓለም ማህበረሰብም ጭምር የማያሻማ ማረጋገጫውን ሲሰጥ የተደመጠበትን አግባብ ማንሳት ብቻ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፤ ይልቁንም ደግሞ፤ በእርሳቸው መሪ ተዋናይነት የተነደፈ ስለመሆኑ የሚነገርለት ሀገር አቀፍ የማህበራዊ ጤና ልማት ስትራቴጂ (ፓኬጅ) ዓለም አቀፉን ማህረሰብ ለማሳመንና ኢትዮጵያ ከመላው የአፍሪካ ሀገራት የተሻለ ድጋፍ እንድታገኝ ለማድረግ ያስቻለም እንደነበር ይታመናል፡፡

ዶክተር ቴዎድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሆኑ ጀምሮ፤ያሳዩት የማስፈፀም ብቃትና በዚያው ልክም የተገኘው ስኬታማ ውጤት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሀገራችን የጤና ዘርፍ ልማት ማስፋፊያነት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ የቀጠለበት አግባብ ስለመስተዋሉ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ በግልፅ አነጋገር፤ ኢትዮጵያ ከዓለም የፋይናንስ ተቋማት ላይ የምታገኘውን የብድር፤ ወይም የዕርዳታ ገንዘብ በትክክል ለታለመለት ተግባር የምታውል ሀገር መሆኗ እየታመነበት እንዲመጣ በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም የጤናውን ሴክተር የመምራት ብቃትና ትጋት ያሳደረገው አውንታዊ ተፅእኖ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ ከዶክተሩ የልጅነት ዘመን ህልም ጋር በተያያዘ የህክምና ሙያቸው የሰጡት ብስለትና ትጋት የተሞላበት የአመራር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት በፈጠረው የሥልጣን ሽግሽግ ምክንያት፤ የኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተደርገው ለአራት ዓመታት ያህል እንደሰሩም የሚታወስ ነው፡፡ እናም ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት ውስጥ ያሳዩትን የፖለቲካ ስብዕና ለታዘበ ሰው፤ ዶክተሩ በሳል ዲፕሎማሲያዊ ጥበብን የተካኑም ጭምር እንጂ ጎበዝ ሐኪም ብቻ እንዳልሆኑ መረዳት አይከብድም፡፡

በተለይም ደግሞ፤ እርሳቸው እንደ አንድ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር በህዝብ ዘንድ የሚታወቁበት ጉልህ ባህሪ ተደርጎ የሚወሰድላቸው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበው በመወያየትና በመተማመን ችግሮችን ለማቃለል ከመጣር የማይቦዝኑ ሰው መሆናቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ሃሳቤን በተሻለ መልኩ የሚያዳብርልኝ ሆኖ የሚሰማኝም ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ አህመድ ኢማኑ “እርሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርም ሆነ ያው እንደወትሮው ሁሉ ከማንኛውም ሰው ጋር እየተገናኘ ከመሳቅና ከመጫወት የሚያግደው ነገር አይኖርም” ሲሉ ሰሞኑን ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት አስተያየት ዶክተር ቴዎድሮስን የገለፁበት አግባብ ነው፡፡

ሌሎች ዶክተሩን በቅርብ የሚውቋቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ምሁራንም እንዲሁ “ቴዎድሮስ አድሐኖም ማለት ዕውቀት ከቅንነት የታደለ ሰው ነው” የሚለውን የአቶ አህመድ ኢማኑ ሃሳብ እንደሚጋሩ የሚያመለክት አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ዶክተሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው በሰሩባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ፤ ከኢትዮጵያውያን የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ጋርም ጭምር በቲውተር ገፃቸው አማካኝነት እየተገናኙ የስደተኛ ወገኖቻችንን ግለሰባዊ ችግር ሳይቀር ለማቃለል ከመሞከር ቦዝነው እንደማያውቁ ማስታወስ አያዳግትም፡፡

ከዚህ አኳያ እንደ አብነት መነሳት የሚኖርበት ጉዳይ የሚመስለኝም፤ በኛ የዘመን ቀመር በ2006 ዓ.ም የሳዑዲ አረብያ መንግስት ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ ስደተኞች ላይ ያልተገባ እንግልት እንዳይፈጽም ለማሳሰብ ሲሉ በግል የቲውተራቸው ገጻቸው ያሰፈሩት ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት በወቅቱ የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ መስተዋሉ ነው፡፡

ሌላው የዶክተሩ ዴሞክራት ፖለቲካዊ ስብዕና መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ባህሪያቸው ደግሞ ግልጽነት (አለመኮፈስ) ይመስለኛል፡፡ ለምሰሌ ያህልም በ2008 ዓ.ም የተከበረውን ሀገር አቀፋዊ የዲያስፖራ ቀን ምክንያት በማድረግ፤ ከዓለም ዙሪያ ለመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም በሚሊኒየም አዳራሽ መድረክ ላይ ወጥተው የድምፃዊ አሊቢራን ተወዳጅ ዘፈን በኦሮምኛ እንዳዜሙላቸው ያኔ አዲስ አድማስ ጋዜጣ መፃፉን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲሁም በሌላ ባህር ዳር ውስጥ በተካሔደ የዲያስፖራዎች ዓመታዊ ሀገር አቀፍ በዓል ከአማራ ክልል ወጣት ከያኒያን ጋር መድረክ ላይ ወጥተው፤ የጎጃምን ጭፈራ፤ (እንቅጥቅጥ) የጎንደርን እስክስታና የወሎውን ደንገላሳ፤ ሲያስነኩት እንደታዩ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ስለዚህም ለኔ “የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያ ምሁራን ምን ዓይነት የአስተሳሰብ ቁመና እንዲኖራቸው ትመኛለህ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብልኝ፤ ልክ እንደ ቴዎድሮስ አድሐኖም ዕውቀት ከቅንነት የተጎናፀፉ እንዲሆኑ ስል ነው የምመልሰው፡፡ እንዲሁም ደግሞ “ኢህአዴግ እንደ አንድ ገዥ ፓርቲ መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያሸከሙትን ታሪካዊ ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ፤ በተለይም የከፍተኛ የአመራር አካላቱ ፖለቲካዊ ስብዕና ምን መምሰል አለበት ትላለህ?” ብባልም፤ የምሰጠው ምላሽ አሁንም የዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖምን አርአያነት እንዲከተሉ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን ጃኔቫ ሲውዘርላንድ ውስጥ በተካሔደው የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞነኛ ምርጫ ላይ ዶክተሩ ማሸነፋቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ፤ መገናኛ ብዙሃን ዜናውን እዴት አጉልተው ሲዘግቡት እንደተስተዋሉ የሚያስታውሱ ነጥቦችን ጠቅሼ ላብቃ፡፡

በዚህ መሰረትም፤ ታዋቂው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ “የዓለም ጤና ድርጅት አሁን ገና ትክክለኛውን መሪ አገኘ” የሚል ዜና በፊት ለፊት ገፁ ላይ ከዶ/ር ቴዎድሮስ አድሐኖም ምስል ጋር ይዞ ስመውጣቱ የኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ነግረውናል፡፡ እንደ ቢቢሲ፤ አልጀዚራ፤ ሮይተርስና ኤ.ኤፍ.ፒ. ዓይቶቹ የዓለማችን ታላላቅ ሚዲያዎችም እንዲሁ፤ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም በእርግጥም ለቦታው የሚመጥኑ ሰው መሆናቸውን የሚያትት ዜና እንደፃፉ ነው ፋና ብሮድ ካስትንግ ኮርፖሬት ካቀረበው ጥንቅር ለመረዳት የቻልኩት፡፡ ታዲያ ይህ የዶ/ሩ የዘመናችንን ዓለም ህዝቦች ከፈርጀ ብዙ ሥጋዊ ደዌ ለመታደግ ክቡር ተልዕኮ እስከ መመረጥ መድረስ፤ ስም ከምግባር ሲገጥም አያሰኝምን ወገኖቼ!? እንደኔ እምነት ከሆነ ግን ያሰኛል ባይ ነኝ፡፡ በተረፈ ለእንደርሳቸው ዓይነቶቹ የሀገራችን ምሁራን ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ ስል “ትዝብትና ፀሎት” በሚል ርዕስ ከፃፍኳት ግጥም ላይ ጥቂት መስመሮችን እነሆ ተጋበዙልኝ ….. ፡፡

 

ኮሌጅ በጥሰው፤ ጥቁር ቆብ ሲጭኑ፤

ከመሰልጠን ይልቅ፤ እየሰየጠኑ፤

ፊደል ባልቆጠረ፤

አርሶ አደር ህዝብ ላይ፤ አጉል ሊኮፈሱ፤

ተማሪ ቤት ገብተው፤ ለወግ የቀሰሱ፤

ሽል መጣሪዎቹ፤ እነ አፍንጫ አድማሱ …

እምነትን፤ እውነተን፤

ፍትህን በስሙ፤ አንቀው የሚገድሉ፤

ሸፍጥ እማይታክቱ፤ ቀላባዮች ሁሉ፤

ነው እንጂ በቁጥር፤ እየበረከቱ፤

(ሚዛን እየደፉ)

ዕውቀት ከቅንነት፤ የተጎናፀፉ፤

ልባም ልብ ያላቸው፤ ጥቂቶች መች ጠፉ!?

አሜን ከንፍሮ ውስጥ፤ ጥሬ እንደሚወጣ፤

እስቲ ከየደብሩ፤

አንድ ቅን አሳቢ፤ ብልህ ሰው አንጣ፡፡

መዓሰላማት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy