Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አብረን እንልማ ወይስ አብረን እንቆርቁዝ?

0 282

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አብረን እንልማ ወይስ አብረን እንቆርቁዝ?

ብ. ነጋሽ

ሰሞኑን የናይል ተፋሰስ ሃገራት መሪዎች በኡጋንዳ ኢንቴቤ ተሰባሰበው ነበር። የስብሰባው ባለቤት ናይል ኢኒሼቲቭ የተሰኘው የተፋሰሱ ሃገራት የመሰረቱት ተቋም ነው። በዚህ ስብሰባ ሃገራቱ በተፋሰሱ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ እንደመከሩ ተነግሯል። በዚህ መሰረት የአካባቢ መራቆትና የደን መጨፍጨፍ፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እንዲሁም የተፋሰሱ ሃገራት ችግሮቹን ተቋቁመው በጋራ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ስልቶች ላይ መክረዋል።

የናይል ኢኒሼቲቭ በ1991 ዓ/ም በተፋሰሱ ሃገራት የተመሰረተ ተቋም ነው። ተቋሙን የመሰረቱት፣ ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ናቸው። ኤርትራ በናይል ኢኒሼቲቭ ትብብር ውስጥ በታዛቢነት ትሳተፋለች። የናይል ኢኒሼቲቭ አባል ሃገራት የናይል አጠቃቀም የትብብር ማዕቀፍ ሰነድ አዘጋጅተዋል። ይህን ሰነድ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ቡሩንዲ ፈረመዋል። ቲትዮጵያን ጨምሮ ሶስት ሃገራት ( ሩዋንዳና ታንዛኒያ) የትብብር ማዕቀፉን ለየሃገራቸው ፓርላማ አቅርበው አጽድቀዋል።

የናይል ኢኒሼቲፍ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፋሰሱን የውሃ ሃብት በትብብር ማስተዳደርና ማልማት የሚያስችሉ መርሆች፣ መበቶችና ግዴታዎችን የያዘ ሰነድ ነው። ሰነዱ የተፋሰሱን የውሃ ሃብት በተቀናጀ፣ ቀጣይነት ባለውና በተጣጣመ አጠቃቀም ማልማት የሚያስችል ሁኔታ የመፍጠር ዓላማ አለው። ከዚህ በተጨማሪ የተፋሰሱን ውሃ የአሁኑና መጪው ትውልድ ሊጠቀምበት በሚችልበት ሁኔታ የመንከባከብና የመጠበቅ ዓላማ አለው።

ከዚሀ በመነሳት የትብብር ማዕቀፉን ዓላማዎች ለማሳካት የሚያስችል የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን የተሰኘ ቋሚ ተቋም መመስረት እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። ይህ በትብብር ማዕቀፉ መሰረት ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቅ ኮሚሽን፣ የትብብር ማዕቀፉ የያዛቸውን ስምምነቶች የማጠናከርና ተፈፃሚነታቸውን የማቀላጠፍ ተልዕኮ ይኖረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአባል ሃገራቱ መሃከል ተፋሰሱንና የወንዞቹን ውሃ በመንከባከብ፣ በማስተዳደርና በማልማት ረገድ እንዲተባበሩ ያደርጋል። ሰሞኑን በኡጋንዳ ኢንቴቤ የተካሄደው የናይል ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮችና የመሪዎች ጉባኤ የአካባቢ መራቆትና የደን መጨፍጨፍ፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋትና የተፋሰሱ ሃገራት ችግሮችን ተቋቁመው በጋራ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ላይ የመከረው ከላይ በተገለጸው የትብብር ማዕቀፉ ዓላማ መሰረት ነው።

በመሰረቱ ናይል ወይም አባይ የጋራ ሃብት ነው። ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ውሃ ወደ ሰባቱ የነጭ አባይ የተፋሰሱ ሃገራት የማይፈስ በመሆኑ የመጠኑ መቀነስ ወይም መጨመር በቀጥታ አሉታዊው አዎንታዊም ተጽእኖ የማያደርስባቸው ቢሆንም፣ በተዘዋዋሪ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል። ከኢትዮጵያ የሚመነጨው የውሃ መጠን ቢቀንስ፣ ወደሱዳንና ግብጽ የሚፈሰው ውሃ ላይ ተዕእኖ ስለሊያሳድር ሰባቱ የነጭ አባይ የላይኛው የተፋሰስ ሃገራት ግብጽ ላይ ጉልህ የውሃ መቀነስ ጉዳት እንዳይደርስ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ደግሞ በሃገራቸው ወሰን ውስጥ ከሚፈሰው ውሃ የሚጠቀሙት መጠን ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በተቃራኒው ከኢትዮጵያ መንጭቶ የሚፈሰው ውሃ መጠን ሲጨምር የታችኞቹን ሃገራት ሳይጎዱ የመጠቀም እድላቸው አስተማማኝ ይሆናል። በመሆኑም ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋጋጥ ተፋሰሱን በመንከባከብ ረገድ ሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት መተባባር ይኖርባቸዋል።

እንግዲህ፣ ናይል ወይም አባይ ዘጠኝ ሃገራትን ያስተሳሰረ ወንዝ ነው። አንዱ ውሃውን ለመጠቀም ሲወስን የሌላውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችላ ሊል አይችልም። አንዱ ለሌላው የመጠቀም መብት እውቅና የማይሰጥ፣ የመጠቀም መብቱን ተግባራዊነት የማያከብርና የሚያሰናክል ከሆነ ሁሉም በውሃው በአግባቡ መጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ፍትሃዊ መብቷ ባይከበር ወይም የመጠቀም መብቷን የሚያሰናክል ሁኔታ ቢፈጠር ተፋሰሱን ለመንከባከብ የሚያነሳሳት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት አይኖርም።

የአባይ ተፋሰስ ወንዞች ምንጭ የሆኑ ተራሮችን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ካልተንከባከብን በአጭር ጊዜ ውስጥ የአባይ ውሃ ፍሰት ላይ ጉልህ ማሽቆልቆል ሊፈጠር መቻሉ ደግሞ እርግጥ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የአባይ ተፋሰስ አካባቢ እንክብካቤ መጓደል፣ የውሃው መጠን ላይ መቀነስ ያስከትላል። በሌላ በኩል ውሃውን ለመጠቀም በሚያስቸግርና ጉዳት ባለው ሁኔታ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል። ግድቦች ኢኮኖሚያዊ አዋጭነታቸውን በጉልህ በሚጎዳ ደለል ሊሞሉ ይችላሉ።

በመሆኑም የተፋሰሱ ሃገራት (የታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት የሆኑት ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ) የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ ሃብት ተጠቃሚነት ከመቀበል በተጨማሪ ተፋሰሱን በማልማትና በመንከባከብ ረገድ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።

የናይል ወይም የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሃገራት በዚህ ደረጃ የተሳሰሩ በመሆናቸው የሁሉም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ተፋሰሱን በጋራ ሊያለሙና ሊንከባከቡ ይገባል። እናም ወደናይል ትብብር ኮሚሽንነት ያድጋል ተብሎ የሚጠበቀውን የናይል ኢኒሼቴቭ መመስረታቸውና መስማማታቸው እምቢ ሊሉት የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ ግብጽ ራስዋን ከኢኒሼቲቩ አግልላለች።

እርግጥ ከባለፈው ዓመት ጀምራ ወደኢኒሼቲቩ የመመለስ ጥያቄ አቅርባለች። የኢኒሼቲቩ አባል ሃገራትም ጥያቄውን እየመረመሩት ይገኛሉ። የኢኒሼቲቩን የትብብር ማእቀፍ እስከፈረመችና የቅኝ ግዛት ዘመን የውሃ ድርሻ ስምመነቶች ገዢ ይሁኑ የሚለውን አቋሞን እስካነሳች ድረስ አባል ሃገራቱ ግብጽ ወደኢኒሼቲቩ እንድትመለስ መፍቀዳቸው አይቀሬ ነው። ግብጽ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን ከተቀበለች የኢኒሼቲቩም ይሁን በቀጣይነት የሚመሰረተው ኮሚሽን አባል መሆኗ አስፈላጊም ነው።

እንግዲህ፣ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በአባይ ውሃ መጠቀም የሚገባትን ያህል ሳትጠቀም ብትቆይም በተፋሰሱ ሃገራት መሃከል ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም አስፈላጊነት ላይ ጽኑ እምነት ነበራት፤ አሁንም በዚህ እምነቷ እንደጸናች ነው። በናይል ኢኒሼቲቭ አባልነት የትብብር ማዕቀፉን የፈረመችውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ያደረገችውም በዚህ መነሻነት ነው።

ኢትዮጵያ አሁን በአባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጠውን የመጀመሪያውን ፕሮጀክቷን በመገንባት ላይ ትገኛለች፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን። የኢፌዴሪ መንግስት ይህን ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ሃይል የሚያመነጭ የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት ለመገንባት ሲያቅድ፣ በተፋሰሱ ሃገራት መሃከል ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል መኖር አለበት የሚለውን  መርህ መነሻ በማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አቋም  ሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያከብር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ   አንዱ የተፋሰሱ ሃገር በውሃው እየተጠቀመ፣ ሌላው የበይ ተመልካች የሚሆንበት አካሄድ ኢፍትሃዊ መሆኑን ከማመናቸውም በተጨማሪ፣ ተያይዞ መጥፋትን እንጂ መልማትን እንደማያመጣ ይረዳሉ። ለቀጠናው አገራት ሰላም ጠንቅ መሆኑንም ይረዳሉ።

ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የመጠቀም መብት እንዳላት እያወቀች በአባይ ተፋሰስ ወንዞቿ እስካሁን ሳትጠቀም የቆየችው፣ ለውሃ ድርሻ ባለመብትነቷ እውቅና የነፈገውን የቅኝ ግዛት የውሃ ድርሻና አጠቃቀም ስምምነትን አክብራ አይደለም። በተፋሰሱ ወንዞቿ ሳትጠቀም የቆየችው ውሃውን ማልማት የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ስላልነበራት ነው።

አሁን አቅም ሲኖራት የሌሎቹን ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት መብት አክብራ ወደመጠቀም ተሸጋግራለች። ኢትዮጵያ የተፋሰሱ ሃገራት በጋራ መልማት የሚችሉት ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት መብት ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን ታምናለች። ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ አብሮ ከመቆርቆዝ ውጭ የትም እንደማያደርስም ትገነዘባለች። አብረን እንልማ ወይስ አብረን እንቆርቁዝ?

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy