Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንድ ሜዳ – አንድ ግብ

0 595

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጉዞ ማስታወ ወዳጆቼ! ባለፈው ሳምንት የጉዞ ማስታወሻዬ «በሊማሊሞ ሀዋሳ» ጉዞ በአውቶቡስ ውስጥ የነበረውን ማራኪ ገጽታ ጨምሮ ድንገት በመንገድ ላይ ስላጋጠመን የጎርፍ መጥለቅለቅ ጥቂት እንዳስቃኘኋችሁ ይታወሳል። ለዛሬ ደግሞ ቀጣዩን የመንገድ ቆይታና ሌላውን የሀዋሳ ውሎ እነሆ! ብያለሁ።

የዓለም ጤናን ከተማ እንደተሻገርን የአብዛኞ ቻችንን ፊት ለማስተዋል ሞከርኩ። ታላቅ እፎይታና ደስታ ይነበብበት ነበር። አሁን አብዛኛው ተጓዥ የሚያስበው ቁርስና ምሳውን እንዴት እንደሚያገኝ ነውና የምግብ ቤቶች መረጣ ተጀምሯል። ሊማሊሟችን በሙዚቃ ታጅቦ ጉዞውን እያፋጠነ ነው። አብዛኛው መንገደኛ ድካም እየተሰማው ቢሆንም ቀድሞ የተጀመረውን ደማቅ ጨዋታ ላለማቀዛቀዝ ወግ ቢጤ የሚሞካክሩ ደግሞ አልታጡም።

ዝዋይ ከተማ ስንደርስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አለፍ ብሎ ነበር። ቀድሞ በተመረጠውና ብዙዎቹ በተስማሙበት አንድ ምግብ ቤት ገብተን ምሳችንን ከበላንና ወፍራም ቡናችንን ካከልን በኋላ ተመልሰን ጉዟችንን ቀጠልን። እንደቀድሞው ጨዋታው ደርቷል። ሀዋሳ ገብተን ማረፊያችንን ከመፈለጋችን በፊት ግን ከጉዞ አስተባባሪዎቻ ችን ድንገቴ ሃሳብ ቀረበ። ከአንድ ቀን በኋላ የሚመረቀውን የሀዋሳ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከልን ሁሉም መንገደኛ እንዲጎበኝ።

ይህ እንደተሰማ ሁላችንም ወደ ማረፊያችን የመሄድ ሃሳባችንን ለውጠን ማዕከሉን ቅድሚያ ለመጎብኘት ተስማማን። ከቦታው ስንደርስ በጉጉት ሲጠብቁን የቆዩት የማዕከሉ ሠራተኞችና በስፍራው የነበሩ ታዳሚዎች ሁሉ በደማቅ አቀባባል አስተናገዱን። የሜሪጆይ ልማት ማህበር መስራችና ዋና ዳይሬክተር ሲስተር ዘቢደር ዘውዴም ማዕከሉን ካስጎበኙን በኋላ በቀጣይ ሁለት ቀናት የታሰበውን ዕቅድና ከእኛ የሚጠበቀውን ሁነት አንድ በአንድ አሳወቁን።

በማግስቱ በዝርዝር መርሀ ግብሩ ከታቀፉት መሀልም ጋዜጠኞችና አርቲስቶች የሚያደርጉት የእግር ኳስ ጨዋታን ጨምሮ ሴት ጋዜጠኞችና ሴት አርቲስቶች ከደቡብ ሴት ነጋዴዎች ጋር የሚፎካከሩበት የገመድ ጉተታ አንዱና ዋንኛው ነበር። ይሄኔ ሁላችንም አቋማችንን ከሚገጥሙን አቻዎቻችን ጋር አመዛዘንን። እውነት ለመናገር አብዛኞቻችን ሴት ተወዳዳሪዎች ፉክክሩ ፈታኝና ከባድ ሊሆን እንደሚችል ገምተናል። ይሁን እንጂ ሁላችንም «ምን ብቀጥን ጠጅ ነኝ» ይሉትን ብሂል አንግበን በድል እንደምንወጣው ተማማልን። በተመሳሳይ ሁኔታ በወንዶቹ ቡድን የነበረው ስሜት ከዚህ የራቀ አልነበረም።ይህን እያሰብን ወደ ማረፊያችን ስንዘልቅም ቆይታችን አዝናኝ እንደሚሆን እያሰብን ነበር።

እንዳይነጋ የለም ነጋ፡፡ በከባድ ድካም የዛለው አካሌን በጣፋጭ ዕንቅልፍ አሳልፌ ስነሳ ፍፁም ሰላም ተሰምቶኝ ነበር።ወዳጆቼ! ቅዳሜ ማለዳ ሀዋሳ ከተማ እንዲህ ታምራለች እንዴ? ተስማሚ አየሯና የተፈጥሮ ጸጋዎችዋስ ቢሆኑ ትሁት ከሆነው ነዋሪዋ ጋር ተዳምሮ ውበቷን ድንቅ አድርጎታል። አንዳች ቆሻሻ የማይታይባትን ጽዱ ከተማ ስቃኝም የኔዋ አዲስ አበባ ትውስ አለችኝ።

በስሱ የወጣችውን የጠዋት ፀሐይ ጣፋጭ ከሆነ ቁርስ ጋር ተመግበን እንዳጠናቀቅን ሁላችንም የኢትዮጵያ ውያን አሻራ ብቻ ወዳረፈበትና በዕለቱ ለምረቃ ወደሚበቃው ግዙፍ የአረጋውያን ማዕከል አቀናን። ግቢው ትናንት ካየነው ይበልጥ አሸብ ርቆ እንግዶቹን በጉጉት ይጠብቃል። ማዕ ከሉ የተገነባላቸው በርካታ አረጋውያንና ሌሎችም የክብር እን ግዶች ቦታቸውን ይዘዋል። የዕለቱ የክብር እንግዳና የኢትዮጵያ አረጋውያን የበ ላይ ጠባቂ የቀድሞው የኤፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በስፍራው ተገኝተዋል።

ከስምንት ዓመታት ብርቱ ጥረትና ድካም በኋላ ዛሬ ለምርቃት ፍሬ የበቃው ማዕከል የበርካቶችን አረጋውያን ዕንባ የሚያብስና እልፍ ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው። ሲስተር ዘቢደርን ጨምሮ በዕለቱ ንግግራቸውን ያሰሙ ሁሉ የተናገሩትም ይህንኑ ሃቅ ነበር። ከ 12 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ማዕከል በወር ከ3000 በላይ አረጋውያንን ያስተናግዳል። ዛሬ ደግሞ ይህ ውጥን እውን በመሆኑ የበርካቶች ደስታ ልክ አልነበረውም።

የማዕከሉን ደማቅ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ካጠናቀ ቀንና ምሳችን ከጨረስን በኋላ የሁሉም ቀጠሮ የተወሰነው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሜዳ ላይ ነበር። እንዴታ! በዚህ ስፍራ እኮ ወሳኝ ቀጠሮ ተይዟል። ይህ ሰዓት በአንድ ሜዳ ላይ ተገናኝተው ግባቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያነጣጥሩ ተጫዋቾች ይጋጠሙበታል። ይህ ሜዳ ከጨዋታ በኋላ አሸናፊና ተሸናፊ ቡድኖች ቢኖሩትም ውጤቱ የሚሰላው ግን በጋራ አላማ ላይ ተመስርቶ ነው። እናም የዋንጫ አሸናፊ ነኝ ብሎ መኩራራት አይኖርም። ለምን? ቢሉ ደግሞ ሜዳውም አንድግቡም አንድ ነውና።

በኮሜዲያንና ጋዜጠኞች መሀል የሚካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የቦታ ድልድል ይደረግ ዘንድ ምክክሩ ቀጠለ። አርቲስቶቹ አስቀድመው ምደባቸውን የጨረሱ ይመስላል። ጋዜጠኞቹ ግን በድልድሉ እምብዛም ስላልረኩ የተጫዋቾች ለውጥ ለማድረግ ሳያስቡ አልቀረም። በዚህ ወቅት አጭሩንና አንጋፋውን ጋዜጠኛ ይጥና ደምሴን ግብ ጠባቂ ለማድረግ የተደረሰው ስምምነት በጋሽ ይጥና ተከላካይ ካልሆንኩ ውሳኔ ውድቅ ተደረገ ።

በአፋጣኝ የተጫዋች ለውጥ እንደተካሄደም በሁለቱም ጎራ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ዘንድ ብሽሽቁ ተጀመረ። አንዱ ከአንዱ ልቆ ለመታየት የሚያደርገው ድርጊትም እጅግ አስቂኝ ነበር። ቡድኖቹ ጎራ ለይተው በሜዳው ላይ ልምምዳቸውን ሲጀመሩ ደግሞ የኮሜዲያኖቹ እንቅስቃሴ ኩምክና የተሞላበት ስለነበር ሳቅና መዝናናትን ማጫሩ አልቀረም። ጋዜጠኞች «እንደ ምላሳችን ብርቱ ነው እግራችን» በሚል መልዕክት በተቃራኒ ቡድን ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሞከሩ።

የዕለቱ ዋና ዳኛ አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬም ተጫዋቾችን ሰብሰብ አድርጎ የጨዋታ መመሪያ አስተላለፈ። የመስመር ዳኞቹ አንጋፋዎቹ አርቲስቶች አሰፋ በየነና ተረፈ ለማ በቀረበላቸው ወንበር ላይ አረፍ ብለው የጨዋታውን ሜዳ ተረከቡ። የዕለቱ ኮሚሽነርም አርቲስት ገለታ ገብረጻዲቅ መሆኑ ታወቀ። ጥቂት ቆይቶ አርቲስቶቹ በኮሜዲያን ማርቆስ አማካኝነት አቋማቸውን ገለፁ። «የሚዲያ ቡድኑ የሜዳውን ደጋፊዎች በሙሉ ዞረው በመጨበጥ ስላባበሉ እኛም በግልጽ ጉቦ ለመስጠት እንገደዳለን» በማለት በዳኛ ፋንቱ እጅ ላይ የአስር ብር ኖት አኖሩ። ይህን ያየው ተመልካችም በደማቅ ሳቅ አወካ።

አሁን ፊሽካው ተነፍቶ ጨዋታው ተጀምሯል። የመጫወቻ ሜዳው የሜሪጆይን ቢጫ ካኒቴራና ነጭ ማሊያ በለበሱ ኮሜዲያንና ጋዜጠኞች ድምቀትም ታጅቧል። የመስመር ዳኞቹ አርቲስት አሰፋና አርቲስት ተረፈ ከመቀመጫቸው ንቅንቅ ሳይሉ በጭራ ዝንብ እንደሚያባርር ሰው ባንዲራቸውን ከወዲያ ወዲህ ያንከላውሳሉ። ጨዋታው እንደተጧጧፈ ጋዜጠኞቹ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ አደረጉ። ሙከራቸውም አንዷ የቅጣት ምት ሆናላቸው የመጀመሪያቸውን ጎል አስቆጠሩ። የሚዲያ ቡድኑም በታላቅ ፈንጠዝያ እየዘለለ ደስታውን ለመግለጽ ሞከረ።

ይህ በሆነ አፍታ ደቂቃ ውስጥ ዋናው ዳኛ አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ የድካም ስሜት ይታይበት ጀመር። ይህን ያስተዋለችው ተለዋጭ ዳኛ ፍሬህይወት ባህሩም በአስቸኳይ ዳኛውን በቀይ አሰናብታ ሜዳውን በዳኝነት ተቆጣጠረችው። ጥቂት እንደቆየ አርቲስቶቹ አቻ የምታደርጋቸውን ጎል አስቆጠሩ። ይሄኔ የኮሜዲያን ማርቆስ ደስታ የዳኛዋን ግንባር በመሳም ተገለጸና በድጋሚ ሜዳው በደማቅ ሳቅ ታጀበ። በዚህ ግርግር መሀልም ሳይታሰብ ሁለተኛዋን ጎል ጋዜጠኞቹ አስገቡ። ዳኛዋ ከሁለቱም ቡድኖች ጥፋት ፈጽመዋል ያለቻቸውን ሁሉ በቢጫ ካርድ አስጠነቀቀች። ይህን ሁኔታ ከዳር ሆኖ ሲያስተውል የነበረው የመጀመሪያው ዳኛ ፋንቱም በፍጥነት ከመሀል ሜዳ ደርሶ ዳኛ ፍሬህይወትን በተራው በቀይ ካርድ አሰናበታትና መልሶ ሜዳውን ተቆጣጠረው።

የመስመር ዳኛው አሰፋ በየነም ተደላድሎ ከተቀመጠበት ወንበር ድንገት ተንደርድሮ በመነሳት የተተኪውን ዳኛ ኃላፊነት ፈጥኖ ተረከበ። ይህ ሁሉ ሲሆን ተመልካቹ ባልተለመደው የጨዋታ ስልት ደስታውን የሚገልጸው በተለመደው ሳቅና ጭብጨባ ነበር። አርቲስቶቹ ሁለተኛውን ጎል ደገሙ። ደስታቸውን ሳያጣጥሙትም ጋዜጠኞቹ መልሰው አስገቡ። ጥቂት ቆይቶ አርቲስቶቹም ሦስተኛዋን ጎል አስቆጠሩና በእኩል ውጤት ፉክክሩ ቀጠለ።

ኮሜዲያን ማርቆስ ጉራው አልተቻለም። ይባስ ብሎም የጎል ክልሉን ትቶና መሀል ሜዳ ድረስ ዘልቆ ዳንሱን ያስነካው ጀመር። በድርጊቱ የተበሳጩት አዲሱ ዳኛ አሰፋ በየነም አጠገቡ ደርሰው ቢጫ አሳዩት። ጨዋታው በድምቀት ቀጠለ። በደጋፊዎች ማበረታታት ሞራላቸው የተገነባው ተጫዋቾችም በጥንካሬያቸው ገፉበት። እስካሁን በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተመዘገበው ውጤት ሶስት አቻ በመሆኑና ሰዓቱ በመጠናቀቁ አሸናፊውን ለመለየት የፍጹም ቅጣት ምት መስጠት ግድ ሆነ።

ይህ ውሳኔ እንደታወቀ በተገቢው የመቀመጫ ስፍራ ላይ የቆየው አብዛኛው ተመልካች ወንበሩን ትቶ ወደ መሀል ሜዳ ተቀላቀለና ጨዋታውን በቅርበት መከታተል ያዘ። ደግሞስ ከሕግና መመሪያ ውጪ ያሻውን ቢያደርግ የትኛው ዳኛ ሊጠይቀው? ዳኞቹም ቢሆኑ እኮ ሌላ ዳኛ ያሻቸዋል።

አሁን የመጨረሻው ውጤት ሊታወቅ ግድ ብሏል። ከሁለቱም ቡድኖች ተደጋጋሚ የፍጹም ቅጣት ምት ሙከራ በኋላ ወሳኝ የሆነችው የመጨረሻዋ ጎል በጋዜጠኞች ተለጋች። በመጨረሻም «እንደምላሳችን ብርቱ ነው እግራችን ያሉት ጋዜጠኞች 53 በሆነ ውጤት አሸናፊነቱን ተቀዳጁና የጨዋታው ፍጻሜ ሆነ።

እሰይ! የሴቶቹ የገመድ ጉተታ በሰዓት ማነስ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል።

እነሆ! በአንድ ሜዳ ለአንድ ዓላማ የተሰለፉት ቡድኖች ግን የጋራ ግባቸው አንድ ሆኖ አሸናፊነትን እኩል ተጎናጽፈዋል። ወገንን ለማሰብ በልዩነት መሀል ውጤትን ማስመዝገብ ልምዳቸው ነውና።

ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ ሸገር የተመለስነው በሁካታም ብቻ ሳይሆን በተመለከትነው ነገር ሁሉ እረክተንም ነበር።

መልካምስራ አፈወርቅ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy