Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዋጪው የድርቅ መከላከያ!!

0 291

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 አዋጪው የድርቅ መከላከያ!!

                                   ይነበብ ይግለጡ

በሀገራችን ለረዥም ዘመናት እየተፈራረቀ ሲከሰት የነበረውን ድርቅ ለመከላከል ለመመከት በሚቻልበት ሁኔታ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ድርቁ በተለያየ ጊዜያት በሰውም በእንሰሳትም ላይ መጠነ ሰፊ አደጋ ሲያስከትል ኖሮአል፡፡በንጉሱ በደርግ ዘመንና አሁንም በኢህአዴግ  ተከስቶአል፡፡አይነቱ ግዝፈቱና መጠኑ የተለያየ ቢሆንም ድርቅ በሀገር  ከሚያስከትለው አደጋ አንጻር ታላቁን ዋጋ የሚከፍለው ሕዝብ ነው፡፡ሲያስከፍለንም ኖሮአል፡፡ዛሬ ይህንን ተፈጥሮአዊ አደጋ ለመቀልበስ የተፈጥሮ ጥበቃና የመስኖ ልማት ስራ በሰፊው እየተሰራ ይገኛል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተከተል ያለው መንገድ ከመቼውም የቀድሞ ዘመናት የበለጠ አዋጪ ነው፡፡ድርቁ የተፈጥሮ ክስተት በመሆኑ ከአየር ሁኔታዎች መለዋወጥ በተለይም የተፈጥሮ የአየር ንብረት በበካይ ጋዞች መሞላትና መበከል ለዚህም ምንጮቹና መነሻዎቹ  የበለጸጉና ያደጉ ሀገራት ከከባድ ኢንዱስትሪዎቻቸው የሚለቁት በካይ ጋዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም መንስኤነት እነአላስካን የመሰሉ አለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ማለት ይቻላል የነበሩ የተፈጥሮ የበረዶ ግግሮች እያቀለጡ በበረዶ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ ድብን የመሰሉ ብርቅዬ እንሰሳት መጠጊያ እያጡ ያሉበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው፡፡ለተፈጥሮ አየር መዛባት በዋነኛነት ተጠያቂው በእናት ተፈጥሮ ላይ የዘመተው ሰው ነው፡፡ለበርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች መነሻውም ይሄው ነው፡፡አደጋውም ተመልሶ የሚያጠቃው ሰውን ነው፡፡

ሀገራችን በተለያየ ጊዜያት መልኩን እየቀያየረ ሲከሰት የኖረውንና የሚከሰተውን ድርቅ ለመመከት ለመቆጣጠር የተከተለችው ብቸኛው አማራጭ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራን እንዲሁም የመስኖ ልማትን በተጠናከረና በዳበረ መንገድ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በስፋት እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ይህ ዘዴ አዋጪም ጠቃሚም መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቶአል፡፡

ወንዞቻችንን ሀይቆቻችንን ሳንጠቀምባቸው እንዲሁ ለዘመናት ኖረናል፡፡ተጎዳን እንጂ ተጠቃሚ አልሆንም፡፡የብዙ ታላላቅና የበርካታ አነስተኛ ወንዞች ባለቤትም ነን፡፡እነዚህ ሁሉ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው ሰርተን መለወጥና ለጥቅም ማዋል ተስኖን በድርቅ ስንጠቃ የኖርነው፡፡ድንበር አለፍና ተሻጋሪ ወንዞችም አሉን፡፡ትልቁን ከኢትዮጵያ ተነስቶ ሱዳንና ግብጽን አቋርጦ ሜዲትራንያን ባሕር የሚገባው የአባይ ወንዝ ባለቤቶችም ነን፡፡

ወንዞቻችን ከእኛ ሄደው ሌሎች ሀገራትን ሲያለሙ ሲለውጡ ኖረዋል፡፡ዛሬ ጊዜና ዘመን ፈቅዶ ለእራሳችን ጥቅም የሚውሉበት ሰፊ መንገድ ተከትለናል፡፡እኛ እየተራብን በድርቅ እየተመታን ሌሎች ድርቅን ረሀብን ድህነት የሚባለውን ሳያውቁት ኖረዋል፡፡የእኛ ችግር የነበረው ተፈጥሮ ሀብታችንን በእውቀት ተጠቅመን መጠቀም አለመቻላችን ነው፡፡ዛሬ የተቀየሱት አዋጪ መፍትሄዎች በስፋት እየተሰራባቸው በመሆኑ ድህነታችንን ከመቅረፍ ልማትና እድገትን ከማስገኘት አንጻር ትልቅ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡  

በተፈጥሮ ጥበቃ ስራው ረገድ በተከታታይ አመታት በተሰራው ስራ የተራቆቱ መሬቶችን በደን ችግኞች የማልበስ ስራ ከፍተኛ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡የተጎዱ መሬቶችን የማከም ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዝናብ ወቅት የመሬቶችን መሸርሸር ለመቀነስ ተችሎአል፡፡ በርካታ አካባቢዎች ቀድሞ ያልነበረ የተሻለ የደን ሽፋን አግኝተዋል፡፡የተፈጥሮ የአየር ንብረቱም ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ ይገኛል፡፡

የመስኖ ልማትን በተመለከተ በሁሉም ክልሎች ሰፊ ስራዎች ቀደም ካሉ አመታት ጀምሮ  እየተሰራ ይገኛል፡፡በከባድ ዝናብ ወቅት ውሃዎችን በስፋት በተቆፈሩ ጉድጓዶች በማቆር  በአካባቢው ውሃ በማይኖበት ወቅት ለጓሮ አትክልቶች ማልሚየነት እንዲሁም ውሃውን በማከም ለመጠጥ መጠቀም በሚቻልበት ደረጃም እየተሰራም ነው፡፡

ውሃ ባይኖርና ለረዥም ጊዜ ቢጠፋ አርሶ አደሩ ራሱንና ልጆቹን በመስኖ ልማቱ ተጠቃሚ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ተፈላጊና መሰረታዊ የጓሮ አትክልቶችን በመትከል በመንከባከብ ከቤተሰቡም አልፎ ገበያ በማውጣት እየሸጠ ለመጠቀም የገቢ ምንጭም ለማግኘት ይረዳዋል፡፡በተግባር ስራ ላይ ውሎ አዋጪነቱ ታይቶአል፡፡ወንዞችን በመጥለፍ ለመስኖ ስራ በማዋሉም ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የግብርና ስራ ያልተለመደ ስለነበር በሰፈራ እንዲሰባሰቡ መስኖን በመጠቀም የተለያዩ እርሻዎችን እንዲያለሙ የተደረገው ጥረት ስኬታማ የሆኑ ውጤቶቸን አስመዝግቦል፡፡ሰፊ የመስኖ ልማትን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ሀገራቸውን ያለሙ የውጭ ገበያቸውንም ያሳደጉና ተጠቃሚ የሆኑ ሀገሮች በብዛት አሉ፡፡ግብጽ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሀገር ነች፡፡ያውም የእኛኑ የአባይ ወንዝ በመጠቀም፡፡ የእኛም የወደፊት እርምጃ በዚሁ መንገድ የሚራመድ መሆን አለበት፡፡ዘመናዊ የሜካናይዝድ እርሻዎች የሚለሙት መስኖን በመጠቀም ነው፡፡

በዚህ መልኩ ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽኖችን ካስፋፋን የተፈጥሮ ጥበቃ ስራችንን አጠናክረን ከቀጠልን የመስኖ ልማትን በስፋት ከተጠቀምን ድርቅና ረሀብን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የምንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡በአማራ ክልል ዋግ ሕምራ  ዞን ባለፉት ተከታታይ አመታት የተገነቡ አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድብ ስራዎች ድርቅን አስተማማኝ በሆነ መንገድ በመቋቋም በምርት እድገት መጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መግለጹ የመስኖ ስራ ምን ያህል ውጤታማ እየሆነ በመምጣት ላይ እንደሚገኝ  በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡

ይሄን ለናሙናነት አነሳነው እንጂ ብዙ ክልሎች ስራውን በስፋት በማስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ የመስኖልማትና የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ሀገራዊ ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ እንደሚለውጠው የታመነ ነው፡፡አምና በኤልኒኖ ምክንያት ተከስቶ የነበረው ድርቅ ካለፉት አመታት ጋር ሲነፃፀር የከፋ የነበረ  ቢሆንም  መንግስት በሰጠው አፋጣኝ ምላሽ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ የጎላ ችግር ሳይከሰት ችግሩን መመከት ተችሎአል፡፡ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት ውኃን በማሰባሰብ በበጋ ወቅት የሚፈጠረውን የውኃ እጥረት ለመቋቋም እንዲቻል ሕብረተሰቡን በማስተባበር ከፍተኛ ርብርብ በመደረጉ  ለውጥ ማግኘት ተችሏል፡፡

በዚሁ የመስኖ ስራ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ  በውኃ  እጥረት ይቸገሩ የነበሩ 35 ሺህ አርሶ አደሮችን 180 ሺህ እንስሳትን የውኃ ችግር መፍታት ተችሎአል፡፡በገጠር ለሚኖሩ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡  

 በደቡብ ወሎ ዞን ባለፉት አመታት የተገነቡ አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድብና የተፈጥሮ ኃብት ልማት ስራዎች ድርቅን በመመከትና በመከላከል ረገድ እንዲሁም የምርት እድገትን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማድረግ የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡    

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት ውሃን በማጠራቀም በበጋ ወቅት የሚፈጠረውን የውኃ እጥረት ለመቋቋም በተደረገው ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ጠንካራ ስራ የተገነቡት ግድቦች   በቂ ውኃ መከማቸት ችለዋል፡፡

ይሄ ትልቅ ለውጥና ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው፡፡ከመስኖ ስራውና ከግብርናው ጋር በተያያዘም በቀጣዩ የመኸር ወቅት ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ ሰብል ለማምረት ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ከሰሞኑ የገለጸ ሲሆን በመኽር አዝመራው ከ12 ነጥብ 75 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት በአርሶ አደሮች ታርሶ በዘር ለመሸፈን እየተሰራ የሚገኝ መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደንታሞ ለመገናኛ ብዙሀን አስታውቀዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy