Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አየር መንገዱ ከሳዑዲ ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን በትኬት ዋጋ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ አደረገ

0 1,545

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ባወጣው የምህረት አዋጅ ምክንያት ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን በትኬት ዋጋ ላይ 50 በመቶ ቅናሽ አድርጓል።

የምህረት አዋጁ ሊጠናቀቅ 20 ቀናት ብቻ የቀሩት ሲሆን፥ እስካሁን ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የጉዞ ሰነድ ወስደዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ ለሌላቸውና ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ዜጎች ብቻ በአየር ትኬት ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ማድረጉን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ለአንድ ጉዞ ይጠይቅ የነበረውን 1 ሺህ 800 የሳዑዲ ሪያል ወደ 900 የሳዑዲ ሪያል ዝቅ ማድረጉንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።

ቅናሹ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት አንድ አካል እና ማበረታቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለትርፍ የተቋቋመ እንደመሆኑ ዜጎች እንዳይንገላቱ በሚል የሰራው ስራም ትልቅ ነው ብለዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ህጋዊ የስራ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የ90 ቀናት የምህረት አዋጅ ማወጇ ይታወሳል።

መጋቢት 21 2009 ዓ.ም የተጀመረው የምህረት አዋጅ ሰኔ 20 2009 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

ይህንን ተከትሎም የሳውዲ መንግስት ለጠንካራ እርምጃ ክንዱን እያጠናከረ መሆኑ ቢታወቅም፤ የምህረት አዋጁ ከሚመለከታቸው በ100 ሺህ ዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መካከል እስካሁን ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ከ21 ሺህ አይበልጡም።

ከሳዑዲ የተመሰሉ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ያለው ሁኔታ የሀገሪቱ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ እና መስሪያ ፈቃድ በሌላቸው ዜጎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ መዘጋጀቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በሳዑዲ ያሉ እና አዋጁ የሚመለከታቸው እህት ወንድሞቻቸው ከሶማሊያ ቦሳሶ እስከ ሪያድ በተዘረጋው የደላሎች የሀሰት ቅስቀሳ እንዳይታለሉ ተመላሾቹ ይጠይቃሉ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ተመላሾች 20 ቀናት ብቻ የቀረው የምህረት አዋጅ ሲጠናቀቅ በሳዑዲ አረቢያ ምድር ያሉ ሰነድ አልባ ዜጎችን የሚያድን ቡድን በሳዑዲ መንግስት በኩል መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አሁናዊ ሁኔታውም መንግስት በፀጥታ ሃይሉ በኩል ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስም፥ የመጨረሻው ሰዓት ተቃርቧልና በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን የቀሩትን የምህረት አዋጅ ጊዜያት እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችም ከሳዑዲ አረቢያ ለሚመለሱ ዜጎች ተገቢውን አቀባበል እና እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በስላባት ማናዬ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy