Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያዊው ኒዮ-ሊበራሊት ፀሐፊ

0 367

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያዊው ኒዮ-ሊበራሊት ፀሐፊ

                       ኢዛና ዘመንፈስ

የኦብጀክቲቪዝም ፍልስፍና አመንጪዋ አየንራንድ በዓለም ዙሪያ በርካታ ደቀመዛሙርቶች አሏት፡፡ ደረጃና ቁጥራቸው ይለያይ እንጂ አየንራንድ ኢትዮጵያ ውስጥም አድናቂዎች እንዳሏት ይታወቃል፡፡ የአየንራንድ ፍልስፍና ገብቷቸዋል/አልገባቸውም? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በዚህ ፅሁፍ ከፍልስፍና ከተከታዮቿ አንዱን እንመለከታለን፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ  ቋሚ አምደኛ የሆነው ዮሐንስ ሰ.   መመልከት ይቻላል  

ብዙዎቹ የነፃው ፕሬስ ሚዲያ ላይ አዘውትረው ሲፅፉ የምናውቃቸው ጋዜጠኞችና ታዋቂ አምደኞች፣ በእጅጉ የሚመሳሰሉበት መሰረታዊ ችግር መንግስትንና አገሪቱ የምትመራበትን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት በፀረ የኢትዮጵያ አንድነት ፈርጀው፣ ይህንኑ እምነታቸውን  እየተቀባበሉ መልሰው መላልሰው ከማመንዥግ ያለፈ ቁምነገር አስነብበውን የማያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ አቶ ዮሐንስ ሰ. ግን ለዚህ ዓይነቱ የተቃውሞ ፖለቲካ ቅኝት እምብዛም ትኩረት የሚሰጡ ፀሐፊ አይመስሉም፡፡

አቶ ዮሐንስ ሰ. ምናልባትም በኛ ሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው አፍቃሪ ኒዮሊበራሊዝም ከመሆናቸው የተነሳ፤ እርሳቸው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሚታወቁበት የተለየ ጉዳይ፤ ዘወትር የሚፅፏቸው አርቲክሎች ሁሉ፤ በተለይም ለምዕራቡ ዓለም  አስተሳሰብ ጥብቅና ለመቆም ባለመ ባዕድ መንፈስ የተቃኙ በመሆናቸው ነው፡፡ እንደዚህ ፀሐፊ ከአሜሪካዊቷ ፈላስፋ ከአየንራንድ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ተፅእኖ በመነጨ መንፈስ የምዕራቡን ዓለም ዘመናዊ አሳቤ ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ሲል ያለ መታከት የሰበከ ፀሐፊ ስለመኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለዚህም የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የህትመት ጉዞ የፃፏቸውን በርካታ አርቲክሎች መመልከትና እውነታውን መረዳት ይቻላል፡፡

ጋዜጣው መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እኚህ ሰው (መጀመሪያ ላይ ሰለሞን ገ. በሚል ስም ይፅፉ ነበር) ያቀረቧቸውን መጣጥፎች በሙሉ ለመመርመር ሞክሬ፤ ስለምንም ዓይነት ርዕሰ ጉዳይ ቢፅፉ፤ የሃሳባቸው ማጠንጠኛ የምዕራባውያኑን ኒዮሊበራሊስቶች አክራሪ የነፃ ገበያ ስርዓት ለሁሉም የዓለም ሀገራት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ችግሮች ፍቱን መፍትሔ እንደሆነ አድርጎ ከመቁጠር የመነጨ ስብከት ላይ የተመሰረተ ጭብጥ ማንሳታቸው እንደማይቀር መገንዘብ ችያለሁ፡፡

አቶ ዮሐንስ ሰ. ቅጥ ባጣ የኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ አቀንቃኝነታቸው ምክንያት ያለ ርህራሄ የሚያብጠለጥሉትን ፌዴራላዊ ስርአት በሚተቹባቸው ፅሁፎች ሁሉ፤ እያንዳንዱ ችግር የሚመነጨው ከምንከተለው የቅይጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሆነና “ኢትዮጵያውያን ተያይዘን ከመጥፋታችን በፊት የምዕራቡ ዓለም የተቀዳጀውን ዕድገትና ብልፅግና ለመቀዳጀት የሚያስችለንን ስርዓት ያለምንም ማቅማማት መቀበል እንደሚጠበቅብን” በአፅንኦት ከማስጠንቀቅ ቦዝነው እንደማያውቁም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

ፅሐፊው ከኢህአዴግ መራሹ መንግስት ጋር የማይግባባቸው ዋነኛ ምክንያት ርዕዮተ ዓለማዊ የአቋም ልዩነት እንደመሆኑ መጠንም፤ ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደርን ዲሞክራሲያዊ መብት ላጎናፀው የፌዴራሊዝም ስርዓት አወቃቀራችን ያላቸው አመለካከት እጅግ የተሳሳት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የሚያቀነቅኑት ሊበራላዊ አስተሳሰብ መገለጫ ስለሆነው የግለሰብ ነፃነት መከበር አለመከበር ብቻ ለመስበክ ባለመ የማያቋርጥ ሙግታቸው መሀል ሀገራችን አሁን የምትመራበት ብሄራዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ስርዓተ  ጠቃሚ እሴቶችን የሚያሳንስ ፀጉር ስንጠቃቸውን ከመሰንዘር የተቆጠቡበት አጋጣሚ የለም ብሎ ማጠቃለል ይቀላል፡፡

ፀሀፊው በማራኪ የአተራረክ ብቃታቸው እያሰማመሩ የሚያቀርቡበት አማላይ ስብከት በተለይም ጀማሪ አንባቢያን ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር ይችል ይሆናል፡፡ እውነታው ግን ወዲህ ነው፤ በህይወት የሌለችው ራሺያ-አሜሪካዊቷ ደራሲና ፈላስፋ አየንራንድ ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት እንደፃፈችው የሚነገርላት የኦቭጀክቲቪም ንድፈ-ሃሳብ አሁንም ድረስ ለመላው የዓለም ሀገራት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ፍቱን መፍትሄ ይሆናል ብሎ ማመን ፈፅሞ ተገቢነት የሌለው ማጠቃለያ ነው፡፡ እንኳንስ በዛሬው ዓለም አቀፋዊ እውነታ ውስጥ፣ ያኔ በዘመነ ቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም ቢሆን የአየንራንድን  የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፍልስፍና (ትንተና) መሰረት ያደረገው የነፃ ገበያ ስርዓትና “ገደብ የለሽ የግለሰብ ነፃነት” እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ያዋጣል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡

እንደ ኢትዮጵያ የራሳቸውን ማንነት የሚገልፁበት ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም  ታሪካዊ፣ መንፈሳዊ፣ ስነልቦናዊ ብሎም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሰረት ያላቸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩበት ሀገር ነባራዊ እውነታ የሚያዋጣው የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት ብዝሃነትን ለማስናገድ በሚያስችል መልኩ ሲነደፍ ብቻ ነው፡፡

አቶ ዮሐንስ ለወትሮው ሰብዓዊ ፍጡር ከምድራዊ የጉስቁልና ህይወት የሚላቀቅበት ብቸኛ የዕድገትና የብልፅግና፣ እንዲሁም የነፃነት መንገድ ስለመሆኑ የሚተርኩለት የሊበራሊዝም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፅንሰ ሃሳብ ቅድስናው እያከተመ እንደሆነ መገንዘባቸውን ያመኑበትን ፍንጭ የገለፁልን ባለፈው ሰሞን “አራት የጥንቃቄ ምክሮች ለመንግስትና ለኢህአዴግ” በሚል ርዕስ የፃፉት ፅሑፍ ላይ ነበር፡፡ ፀሐፊው መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም  በተለይም ለገዥው ፓርቲና እርሱ ለሚመራው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ባቀረቡት የወቅቱን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ያገናዘበ  ምክራቸው ላይ “ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የምዕራባውያን የብልፅግና ምንጭ ሆኖ የቆየው የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ቀውስ ገጥሞታል፡፡ በዚህም ምክንያት  ዓለማችን ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ የለም፡፡ የኛም ሀገር ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ይሻል፡፡” ሲሉ አስረግጠው እንዳስገነዘቡ አይዘነጋም፡፡ አየንራንድ ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት የፃፈችው መፅሐፍ ላይ ስለ ሊበራላዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ንድፈ ሃሳብ “ቅድስና” የመሰከረችበትን የሚያማልል ትንታኔ ቀንጭበው በማቅረብ ጭምር “ነበር” ወደመሆን እየተቃረበ ለሚገኘው አክራሪ የነፃ ገበያ ስርዓት እርማታቸውን የማውጣት ያህል በቁጭት መብከንከናቸውን አስታውሳለሁ፡፡

ኢትዮጵያው ኒዮ ሊበራል ፀሐፊ ከሰሞኑ ደግሞ አንድ አስገራሚ ፍርደ ገምድልነት ጎልቶ የተንፀባረቀበት መጣጥፍ አስነብበውናል፡፡  ቅዳሜ ግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ የህብረተሰብ ዓምድ ላይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸውን ከፓሪሱ ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ቀውስን የማስወገድ ስምምነት ለማስወጣት መወሰናቸው እኛንም ጭምር እንደሚጠቅም አርገው ሊያሳምኑን የሞከሩበትን ሃተታ አነጋጋሪና አስተዛዛቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ስለዚህም “አንተን የሚመለከት ነገር ተነስቶ ሲነገር እየሰማህ አንዳች ምላሽ ሳትሰጥበት ከቀረህ ልክ ጉዳዩን እንደተቀበልከው ይቆጠራል” ይባላልና የአዲስ አድማስ ጋዜጣው ዮሐንስ ሰ.፤ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከአንድ አሜሪካን ያህል ልዕለ ሃያል ሀገር ከሚመራ ሰው የማይጠበቅ ስለመሆኑ የታመነበት ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ማድነቃቸው አልበቃ ብሎ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምታራምደውን የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ “ዓለም አቀፉን ማህረሰብ ለማስደሰት ሲባል ብቻ የሚደረግ ከንቱ ድካም” አስመስለው ያቀረቡበት ሰሞነኛ መጣጥፍ ሊታረም የሚገባውን  ሆኖ እንዳገኘሁት ለመግለፅ ነው ፡፡

ምንም እንኳን ፀሐፊው በሰብዓዊ ፍጡር የጋራ ህልውና ላይ እጅግ በጣም አሳሳቢ የጥፋት አደጋ እያስከተለ ስለመሆኑ በምድራችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊቃውንቶችም ጭምር የተመሰከረለትን፤ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ ችግር “እንደተራ ስጋት” ቆጥረው፤ ሀገራችን የምታደርገውን የአካባቢ ጥበቃ ጥረት ሁሉ “የስልጣኔ ፀር ነው” እስከ ማለት የሚደርሱ ግለሰብ መሆናቸውን አሳምሬ የማውቀው ቢሆንም፤ እንዲህ እንደ አሁኑ “በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” የሚያሰኝ ዓይነት ውዳሴ  ሊግቱን ሲሞክሩ በቸልታ ማለፍ ግን ተገቢነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም፤ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ስምምነት ሀገራቸውን የማስወጣት ውሳኔ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ አርሶና አርብቶ አደር ህዝቦች፤ ያለዕዳቸው ለተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ እየተጋለጡ ድርቁ በሚያስከትለው የምግብ እጥረት ሲማቅቁ የሚስተዋሉበት ኢ-ፍትሐዊ እውነታ ተባብሶ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሆኖ ሳለ፤ እንደበጎ እርምጃ ቆጥረው ሊያሳምኑን መሞከራቸው ሰውዬውን ይበልጥ ለትዝብት የሚዳርጋቸው ሆኖ ይሰማኛልና ነው፡፡

ዶናልድ ታራምፕ አሜሪካና ሌሎችም የምዕራቡ ዓለም ባለፀጋ ሀገራት የድንጋይ ከሰል ማምረትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ለዜጎቻቸው የቅንጦት ኑሮ፤ ይበልጥ መደላደል ይበጃል የሚሉትን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ የሚያደርጉትን የምጣኔ ሀብታዊ ግስጋሴ አጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ፤ መወሰናቸው ማድነቅ ከማስተዛዘብም በላይ ነው፡፡ እኛ አፍሪካውያን ህዝቦች “ኤልኒኖ” የተሰኘው ተፈጥሯዊ ክስተት በሚያስከትለው የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ለድርቅ አደጋ እየተጋለጥን ራሳችንን መመገብ ሲያቅተን በቸልታ ማየትን ያህል ፍርደ ገምድልነት ሊገኝ ይችላልን? እንደኔ እምነት ከሆነ ግን የለም ባይ ነኝ፡፡ ታዲያ ይህ ፀሐፊ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕን ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ከቶውንም “እንደ ኢትዮጵያ ላሉት የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚጠቅም እርምጃ” ሲሉ በአድናቆት ያሞካሹበት መጣጥፍ መነቀፍ ይበዛበታልን ወገኖቼ?

በዚህች ቅፅበት ውስጥ እንኳን እኮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያን ጎረቤቶቻችን የሰለጠነው ዓለም ባለፀጋ ሀገራት አልጠግብ ባይነት፤ ድምር ውጤት እንዳስከተለው ከሚታመንበት የአየር ንብረት ቀውስ በሚመነጭ የድርቅ አደጋ ምክንያት እጅጉን የከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠው በረሃብ ቸነፈር እየማቀቁ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው፡፡ ለነገሩ እርሳቸውን የመሰለ የምዕራቡን ዓለም ነጮች ከስህተት የፀዱ አማልዕክት አድርጎ ለመቁጠር የሚቃጣው ኒዮ-ሊበራሊስት ፀሀፊ ከዚህ የተሻለ የፍትሀዊነት መመዘኛ መነፅር እንዲኖረው አይጠበቅም፡፡ ለማንኛውም ግን ምላሹን ለአንባቢያን የህሊና ፍርድ እየተውኩኝ  እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy