Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ የትኛውንም አገር የመጉዳት ፍላጎት የላትም!

0 343

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ የትኛውንም አገር የመጉዳት ፍላጎት የላትም!

                  ዳዊት ምትኩ

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ በማደግ ላይ ያለችውን አገራችንን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ከማስፋፋት ባሻገር፤ የተፋሰሱን አገራት ጥቅም የሚያስከብር ነው። ከግድቡ አገራቱ እንዲጠቀሙ በሚያስችል መልኩ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ለምተው በጋራ እንዲጠቀሙ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ፤ አገራችን የትኛውንም አገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት የሚያመላክት ነው።

የህዳሴው ግድብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ከተደረገ ጀምሮ፤ ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉም እንደየ አቅሙ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ እንዲሁም ቦንድ በመግዛት እስካሁን ያበረከቱት አስተዋፅኦ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሀገራችን ለዘመናት በድህነትና በኋላቀርነት የኖረች ናት፡፡

ህዝቦቿ ለዘመናት የልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ሳቢያም የረሃብና የድርቅ ሰለባ ሆነው ዘመናቸውን አሳልፈዋል። ይህን ዕውነታ ማንኛውም የዓለም ማህብረሰብ ሲናገረውና ህዝባችንን ሲያሸማቅቅ የኖረ ሃቅ ነው። እንዲያውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገራችን ስያሜ በመዝገበ ቃላት ላይ ሳይቀር የረሃብ ትርጓሜውን ለማስረዳት በምሳሌነት ይጠቀስ ነበር፡፡

ይሁንና ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ነባሩ የሽንፈትና የድህነት ካባ ቀስ በቀስ እየተቀየረ በመምጣት ላይ መሆኑ ከማንም በላይ ምስክር የሚሆነው የችግሩ ተቋዳሽ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ በተለይም መንግስት ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሶ ምልዕዓተ ህዝቡን ባሳተፈ አኳኋን የጀመረው ያልተቋረጠው ርብርብ ባለፈው አስራ ሁለት ዓመታት ውጤታማ ፍሬ ማፍራት ታሪካችንን በአዲስ መልክ ቀይሮታል። ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ በአዲስ መዝገበ ቃላት ላይ መመዝገብ ችለናል—ከሰሃራ በታች ነዳጅ ከሌላቸው ሀገሮች ቀዳሚ የዕድገት ተምሳሌት በመባል።

ይህም የሀገራችን ህዝቦች ‘ድህነት በቃን’ በማለት ከዚሁ ቀደም እግር ተወርች አስሮ የያዛቸውን የ“አይቻልም” መንፈስን “በይቻላል” የቀየሩበት ታላቅ የልማት ፕሮጀክት አንዱና ዋነኛው የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስራውን ከተጀመረ እነሆ ድፍን አምስት ዓመታትን ሊያስቆጥር በጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ብቻ ይቀሩታል፡፡ የህዳሴያችን መደላድል ፈጣሪ ከሆኑት የልማት ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ ፕሮጀክት፤ የዚህ ትውልድ አሻራ በመሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ የልማት ተቋም ነው፡፡

ከዘመናት በፊት ያለፈው ትውልድ ለእኛ አወርሶን የሄዱው የአክሱም፣ የጎንደርና የላሊበላ ስልጣኔ- ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ጥበብ በመሆኑ በኩራት ለቱሪስት መስህብነት እየተጠቀምንበት ያን ትውልድ እያስታወስነው ነው፡፡ የእኛው ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። ይህም ለመጪው ትውልድ ልማትን እንጂ ልመናን ያለማውረስ ራዕይን የሰነቀ ነው፡፡

የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት በታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ለግንባታው አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን መልካም ተግባራቸውን አሁንም በልበ ሙሉ አጠናክረው እየቀጠሉ ናቸው፡፡ በእስካሁኑ የግድቡ ግንባታ ከግማሽ በላይ እስኪደርስ ድረስ በአራቱ ማዕዘናት የሚገኙት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ርብርብ ከማድረግ አለተቆጠቡም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለግንባታው ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል መንግስት ያዘጋጀውን ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ተወጥቷል፤ በመወጣትም ላይ ይገኛል፡፡ የቦንድ ግዥውን እያከናወኑ ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ናቸው—ከህፃን እስከ አዋቂ ድረስ። ለዚህም ነው  ‘የህዳሴው ግድብ ግንባታ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ ፕሮጀክት ነው’ እየተባለ የሚነገረው፡፡

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈጸሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማነሳሳት ረገድ እየተጫወቱት ያለው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያውያን የትላንት ታሪክ ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር በአንድ ላይ በመዝመት ጠላት ላይ ድል መንሳት ነበር፡፡

ይሁንና ከዚህ ሀገርን ከጠላት መከላከል ተግባር በዘለለ ህዝቡ ለልማት የተባበረ ክንድ እንዳይኖረው ያለፉት መንግስታት ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ነገር ግን የኢፌዴሪ መንግስት የትኛውም የሀገራችን ቀደምት መንግስታት ደፍረው የማያውቁትን በአባይ ወንዝን የመጠቀም መብታችንን ካወጀ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በተገኘው የልማት አጋጣሚ ያለ ዕረፍት እየሰራ ነው።

ወትሮም ቢሆን ይህ ድህነት ያንገሸገሸው ህዝብ እንስራና ሀገር በጋራ እንገንባ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና ኖሮበት አይደለም፡፡ አስተባብሮ የሚያሰራው አካል ካለ ሀገሩን በስራ መለወጥ እንደሚችል ባለፉት 15 ዓመታት በተከታታይ ባስገኘው ፈጣንና ተምሳሌታዊ እድገት ማስመስከር የቻለ ህዝብ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ማንንም የመጉዳት ባህል የላቸውም—የመጥቀም እንጂ። እንደሚታወቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ በሚገኘው ምጣኔ ሃብታችን ሳቢያ፣ ግብርና የመሪነት ሚናውን በሂደት ለኢንዱስትሪው ሲያስረክብ ለሚፈጠረው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው። ለግብፅ ጭምር ኤሌክትሪክ በመሸጥም የውጭ ምንዛሪ አቅማችን እንዲጎለብት ማድረጉ አይቀሬ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት የነደፈውና ተፈፃሚ በመሆን ላይ የሚገኘው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በማሳካት የሀገራችን ህዳሴ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ በማድረግ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

የኢፌዴሪ መንግስትም ሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉን በማቀጣጠል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራን ይፋ የማድረጉ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። እርግጥ የግድቡ ግንባታ ለዘመናት የዘለቀውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን የመቀየርና ያለመቀየር ጉዳይ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ ሊያጠያይቅ አይችልም። በመሆኑም የግድቡን ግንባታ የማሳካቱ ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ህይወት የመለወጥና ያለ መለወጥ ጥያቄና ውሳኔ ብቻ አይሆንም— የቀጣዩን ትውልድ ህልውና የማረጋገጥና ያለማረጋገጥ ብሎም ሀገራዊ ህልውናን የማስቀጠል ሀገራዊ ፋይዳ ያለውም አንድ ማሳያ በመሆኑም ጭምር እንጂ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ጭምር መሆኑ በሀገራችን በተደጋጋሚ ተገልጿል። እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ላለባቸው እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ ይሆናል። ይህም በህዳሴው ግድብ ምክንያት የሚጠቀም እንጂ የሚጎዳ አገር እንደማይኖር ማሳያ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy