Artcles

ከልማት እንጂ አሉባልታ የሚገኝ ጥቅም የለም!

By Admin

June 20, 2017

ከልማት እንጂ አሉባልታ የሚገኝ ጥቅም የለም!

ዳዊት ምትኩ

ፅንፈኛው ሚዲያ የዚህን ሀገር ሰላም ለማወክ ያላስወራው አሉባልታ የለም። ሰላማችንን ለማወክና የጀመርነውን ዕድገት ለማቀጨጭ ያልቧጠጠው ነገር የለም። በተለይም ወጣቱን ወዳልተፈለገ መንገድ ለመምራት ያከናወናቸው ፀረ-ሰላም ተግባሮች በርካታ ናቸው። ይሁንና ወጣቱ ከትናንት ዛሬ የተማረና ሁኔታዎችን በሚገባ የተገነዘበ ነው። በጽንፈኞችና በዘረኞች አሉባልታ ሊፈታ የሚችል አይደለም።

እርግጥ በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠ ርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ መጠንም ከሱ ብሔር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡ ያስባል፡፡ ያልማል፡፡

ይህ የጥበት ሃይል በመስበክ ብቻ ራሱን አያቅብም፡፡ የብሔሩ አባል ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሠራል፡፡ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፀር በመሆንም ሌላውን ዜጋ ለመጨፍለቅ ይሞክራል—ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡

ታዲያ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅኑ ጠላት የሆኑትና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሃገሮች ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በሰላማችንና በልማታችን ላይ የተደቀኑ እንቅፋትና ጋሬጣዎች መሆናችው ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡ እናም የእነዚህ የጥፋት አስተሳሰብ በሮች ሊከረቸሙ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡

የትምክህት ኃይሉ በግንቦት ሰባት፣ ጠባብ ኃይሉ ደግሞ በኦነግ ፊታውራሪነት ለራሱ እንኳ መሆን ባልቻለውና ማተራመስና ሽብርን የዕለት እንጀራው ባደረገው የኤርትራ መንግሥት አይዞህ ባይነት ኢትዮጵያን የማፈራረስና ከፈጣን ልማቷ የማደናቀፍ ተልዕኮ ተቀብለው ላለፉት ዓመታት የሽብርና የጥፋት ተግባርን ያለመታከት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን በመላ ኢትዮጵያውያንና በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጽናት የጥፋት ተልዕኳቸውን መፈፀም ባይችሉም፡፡

ራሱን ግንቦት ሰባት ብሎ የሚጠራው የሽብርና የብዝሃነት ጠላት የሆነ የትምክህት ኃይል በኢትዮጵያ የሰፈነው የብሄር ብሔረሰቦች የማንነት፣ የቋንቋና የሃይማኖት እኩልነትን ፈጽሞ የማይቀበል፣ በአንድን ብሔር ስም የሚነግድና በተግባር እንደታየው የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ደመኛ ጠላት ነው፡፡ የትምክህት ሱሱን መወጣትና የአስመራውን ከፍ ሲልም የአንዳንድ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚሹ ሃይሎችን ተልዕኮ በመያዝ የቀን ቅዠት ሰንቆ ሽብርና ትርምስ ለመፍጠር አቅዶ ይሰራል—የቀቢፀ ተስፋው አለመሳካት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡

ገደብ የሌለው የሥልጣን ጥሙን ለማርካት በህዝቦች መካከል ግጭትና መተላለቅን የሚፈጥሩ መርዘኛ መረጃዎችን የሚረጭ ከዚህም የፖለቲካ ትርፍ አትርፎ የአራት ኪሎውን ቤተመንግሥት እቆጣጠራለሁ ብሎ የሚያስብ ከንቱ ድርጅት ነው— ትምክህተኛው ግንቦት ሰባት፡፡  ፊት ለፊቱ የተገተረን እውነታ ለመካድ የሚውተረተር እብሪተኛ ቡድንም ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ቡድን በዓላማም ሆነ በአስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው የጠባብ ኃይልም በኦሮሞ ህዝቦች ደም ሲነግድ በኖረው ኦነግ የተባለ አሸባሪ ድርጅት የሚመራና የኤርትራ መንግሥት የጡት አባቱ የሆነለት የጥፋት ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ ‘የኦሮሞን ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ብሔር ገንጥዬ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር እፈጥራለሁ’ በሚል የቀን ህልም ውስጥ የተዘፈቀ የሽብርተኞች ስብስብም ነው፡፡

የትላንት ገዥ መደቦች በህዝቦች ላይ የፈፀሙትን በደል ሁሉ የአንድ ብሔረሰብ አባላት እንደፈፀሙት አድርጐ የጥላቻ መርዝ መርጨትና አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂት ሲፈጥር ማየትም የማይለወጥ ራዕዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው— ‘እገሌ የተባለውን ብሔረሰብ አባል ከክልልህ አባረው ወይም አጥፋው’ በማለት የማያቋርጥ ስብከቱን ሲያሰማ የሚኖረው፡፡

በጥበት ሃይልነት የሚነሳው ሌላው አካል ጃዋር መሃመድ የተሰኘው የእነ ግብፅ መንግስት ተቋማት ተላላኪ ነው፡፡ የጃዋር የጥበት መጠን ‘አንገቱን በሜጫ’ እስከሚል አስገራሚ ዲስኩር የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህ ግለሰብ በፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ዳረጎት ሰጪነት ያቋቋመውን “OMN” የተሰኘን ጣቢያ በማቋቋም ሀገራችን ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር ተሯሩጧል። በርካታዎች ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ እንዲቀር አድርጓል። በድሃው የኦሮሞ ልጅ እጅ ፍም እሳትን በመያዝ ወጣቶችን ባልተገባ መንገድ መርቶ ብጥብጥ ፈጥሯል። “አኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል ብሂልን በመከተል በሌላኛው ላይ እሳትን ለመለኮስ ጥረት አድርጓል፡፡

እንግዲህ ከላይ አጠር ባለ መልኩ ልዩነታቸውን የተመለከትናቸው የትምክህትና የጥበት ኃይሎች በቅርቡ በጥብቅ የሚያቆራኛቸውን ነገር አግኝተው ፍቅራቸው ጣራ መንካቱን እናስታውሳለን፡፡ ይሁንና ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ትምክህትና ጥበት አምሳያዎች ቢሆኑም በአንድነት መስራት ስለማይችሉ አንደኛው ራሱን የበላይ በማድረግ መብት ለሌላኛው ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ‘የእገሌ ብሔር ልሂቃን’ እያለ ስም በማውጣት በማንነት ጥያቄዎች ላይ ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ ጥንብ እርኩሱን ሲያወጣ ይስተዋላል።

ይህ የወል የመተቻቸት በሽታቸውም በጋራም ሆነ በተናጠል ብዝሃነት መለያዋ በሆነች ታላቅ ሀገር እንዳይኖሩ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ በአንድ ወቅት “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል እሳቤ በሽብር በአመፃ አውድማ ላይ ተሰማርተውና በጥፋት ጋብቻ ተጣምረው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መገለጫ የሆነችውን ሀገራችንን ለማተራመስ ሞክረው ብዙም ሳይቆዩ አንዱ በሌላኛው ላይ ጣቱን ለመቀሰር በቅቷል፡፡

ይህ የጥፋት ሀገራችንን ወደ ለየለት ብጥብጥ ውስጥ የሚያስገባት በመሆኑ የእነዚህ ሃይሎች መግቢያና መውጫ በር ይገባዋል፡፡ ወጣቱ የእነዚህን ሃይሎች በተለይም በሚዲያዎቻቸው የሚያስወሯቸውን አሉባልታዎች ዓላቸውን በግልፅ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ እነርሱ በሚያስወሩት ሁኔታ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ መንግስት እያደረገ ያለውን ተግባር ያውቃል፡፡ ከልማት እንጂ ከአሉባልታ የሚገኝ ነገር እንደሌለም ስለተገነዘበ የእነዚህን ሃይሎች የቅጥፈት አጀንዳ ተረድቶ ሁሌም ፊቱን ወደ ልማት መመለስ ይኖርበታል፡፡ ልማት እንጂ አሉባልታ የሚፈይደው ነገር የለምና፡፡