Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከምርቃት ባሻገር

0 1,160

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቁሶች አንዱ ሰርግ ነው፡፡ ታዲያ ተወዳጁ የሰርግ ባህላችን በሀገራችን በሁሉም ማህበረሰቦች ዘንድ የተለመደ ሲሆን፤ ድግሱም ‹‹ያለው ማማሩ›› በሚለው ብሂል አራማጆች ዘንድ የሚተገበር ነው፡፡ ነገሩ ትውፊታዊ ወግ ማዕረግ የሚታይበት ቢሆንም፤ ሁካታዊ የኢኮኖሚ ቀውስን የሚያስከትልም ነው፡፡ በርግጥ አሁኑ ወቅት መጋባት እንጂ መደገስ ብዙም የለም፤ ቢኖርም የሰውን ሰርግ በልተው ውለታ ባለባቸው ሰዎች ዘንድ አሊያም የዘመናችን ከበርቴ ባለሀብቶች ለዝናቸው ሲባል የሚከውኑት ነው፡፡ ይልቅ አዲስ የትዝብቴ ማዕቀፍ ወደ ሆነው ጉዳይ ልምጣ፡፡ ዛሬ ላይ በሰርግ ምትክ የድግስ ቦታውን የተቆናጠጠው የሰርግ ታነሽ ወንድም እየተባለ የሚጠራው ምርቃት ሆኗል፡፡

በዘመኑ ትልቁን የድግስ ግሳንግስ በሰው ጫንቃ ላይ እየጣለው የሚገኘው ምርቃት ይኸው ስንቱን ባለ እዳ አድርጓል፡፡ መመረቅ የቃሉ ጥፍጥና ብቻ በቂ ነበር፤ ግና ምን ያደርጋል የድግሱ ምሬት አንገት አስደፊ ሆኗል፡፡

የድግስ አደጋገስ ባህላችን ‹‹ከማን አንሼ›› በሚል ፈሊጥ የታጀበ መሆኑን ተከታሎ አላስፈላጊ ለሆኑ ኪሳራዎች መዳረግ ተለምዷዊ ድርጊት እየሆነ ይገኛል፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከእገሌ ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያ ዲግሪ ከተመረቅኩ አንድ አመት ይሞላኛል፡፡ ደግሞም ከጥቂት ቀናት በኋላም እገሊት በምትባል አነስተኛ ተቋም ውስጥ ለስራ የተቀጠርኩበትን አንደኛ ወሬን አከብራለሁ፡፡ የምርቃቴን ድግስ ለእንግዶቼ ለማብላት የጓጓሁትን ያህል በአመቴ የመጀመርያ ደመወዜን ለመብላት በጉጉት ሜዳ ላይ ዱብ ዱብ እያልኩ ነው፡፡ መቼም የዩኒቨርሲቲ ህይወት ቀላል እንዳልሆነ ገብቶ የወጣ ያውቀዋል፡፡ ለዛም ይመስለኛል በቀላሉ ስራ የማናገኘው፡፡ እኔም ስራ አጥነቴ የሰጠኝን የአንድ አመት እረፍቴን ያለ ደመወዝ ካጣጣምኩ በኋላ የስራውን አለም ተቀላቀልኩ፡፡

በእኔ ህይወት ውስጥ ፍላጎትና ትምህርት፤ እንዲሁም ትምህርትና ስራ ከሰኔና ሰኞ ጋር ፉክክር የያዙ ይመስል ግጥምጥሞሻቸው የተአምር ያህል ሆነብኝ፡፡ ልክ እንደ ጓደኛዬ፤ እርሱ ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ይወዳል ፍላጎቱ ግን ሙዚቀኛነት ነው፡፡ የተማረ መካኒክ ስራው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ እኔም ምኞቴ ሌላ፣ የተማርኩት ሌላ፣ ስራዬ ሌላ፣ የምሰራውም ለሌላ ነው፡፡ ይህም ማለት ፍላጎቴ ህክምና ማጥናት፣ የተማርኩት ውሃ ምንድስና፤ የምሰራው የቤት መጥረጊያና መወልወያ ጅምላና ችርቻሮ አከፋፋይ ሱቅ ውስጥ ነው፡፡ አሁን ነገር አለሙ ስለተዘበራረቀብኝ የትኛው ነገር እንደባከነ እንኳን አላውቅም ብቻ የኔ ሀሳብ ፍላጎትና ትምህርት አልያም ትምህርት እና ስራ መገጣጠሙ ላይ ሳይሆን ሻጭና ገዢ በሌላ አባባል እኔና ደንበኛ መገጣጠማችን ላይ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲ እያለሁ በተለይ የመጨረሻው አመት ተማሪ ሆኜ በሰበብ በአስባቡ ቤተሰቤን ገንዘብ እቀበል ነበር፡፡ ምክንቱም ከጥቂት ወራት በኋላ ስራ ይዤ እንደምክሳቸው እርግጠኛ ስለነበርኩ፡፡ ከምለብሰው የሱፍ ልብስ አቅም እንኳን ሁለት ነበር ያስገዛሁት፡፡ ለምን ካላችሁ አንዱ ለመመመረቂያ ጽሁፍ ማቅረቢያና በተማሪው ለሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ አምሬና ደምቄ የምታይበት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ለምርቃቴ ቀን ቤቴ ውስጥ ለሚኖረው የድግስ እለት የማሸበርቅበት ነው፡፡

የአምስት አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬን ሳጠናቅቅ ደስታዬ ምናልባት ሰማያዊ ሚዛን ካልሰፈረው በቀር በምድር ልኬት እንዴት ብዬ እንደምገልፀው አላውቅም ነበር፡፡ እኔና ቤተሰቤም ይህንን ልዩ ደስታ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በምርቃት ድግስ ለማጣጣም ሽር ጉዱንና ጎንበስ ቀናውን አጣደፍነው ፡፡

መቼም እኛ ሀገር ከማን አንሼ የምትባል በማይክሮስኮፕ እንኳን የማትታይ ቫይረስ አይሏት አልያም ፈንገስ ነገር አለች አይደል? እናም በዚህች ደዌ የተመታነው እኔና ቤተሰቦቼ፤ ይህን ድግስ እንደነ እንትና ልዩ ለማድረግ ሲባል እኔ በምክር፣ አባቴ በብድር፣ እናቴ በእቁብ እህቴ በመላ፣ ወንድሜም በቅፈላ ያገኙትን ገንዘብ አሰባሰቡና ድግሱ ተጀመረ፡፡ ተጀምሮም አልቀረ ከእንግዶች ጋር ተከበረ፡፡ እንደ ጉድ ተበላ ተጠጣ የተስተናጋጁ ምርቃት ተሰብስቦ በክሬዲት ሀወር ተካፍሎ ማስተርስ ይሆነኝ ይመስል አዥጎደጎዱት፡፡ በጣም የሚገርመው የሰበሰብኩት ምርቃት ሁሉ ከምግብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ አንዱ ተነስቶ “ የመጀመርያ ደሞዝህንም ለመብላት ያብቃን” ይላል፡፡ ተማረ የሚባለው አካልም “ ማስተርስህን ሰርተህ ደግሞ ለመብላት ያድርሰን” ይላል፡፡ ሌላውም ተነስቶ “ሰርግህንስ የምንበላው መቼ ነው?” ይላል፡፡ የልጅህን ክርስትና ለማብላት ያብቃን የሚሉ ድምፆችም እየተወረወሩ ይመጣሉ፡፡

ደስ ስንል ምክንያት እየፈጠርን በሰው ድካም እና እንግልት መብላት ብቻ፤ እኔ ስቃዬን በልቼ እማራለሁ እነሱ እየሳቁ ይበላሉ፡፡ በስራ አጥነት የሰቀቀን ዘመኔ ዞሮ ያላየኝ የመጀመርያ ደመወዜን ሳገኝ አብሮኝ መብላት ይመኛል፤ አግብቼም ወልጄም እንደዛው፡፡ ምርቃቴ አልቆ እስከመጨረሻው የድስት ጥራጊ ህቅታ ድረስ ሁሉም ነበሩ፡፡ ከድንኳን ማፍረስ እስከ ብድር መመለስ ግን ማንም ከጎናችን አልነበረም፡፡ እኔ ስራ ይዤ ከሚከፈለኝ ደህና ደሞዝ ላይ እቁቡም እድሩም እንደሚከፈል ነበር እቅዳችን፡፡ ከተራ ምኞት ያልዘለለ ከንቱ ቅዠት፡፡

ከቀናት በፊት እንደልማዴ ስራ ፍለጋን ስንከራተት ከየት መጣ ያልተባለ ዝናብ ተልእኮዬ ላይ እንቅፋት ሲሆንብኝ፤ እሱም ይለፍ እኔም ልረፍ ብዬ ወደ አንድ ሱቅ በረንዳ ልጠለል ጎራ አልኩ፡፡ ዝናቡ ከጣሪያው ጋር እኔም ከባለ ሱቁ ጋር ወጋችንን ገጠምነው፡፡ የሆድ የሆዳችንን ስናወራ ቀድሞ ሱቅ ውስጥ ይሰራለት የነበረ ሰራተኛ በድንገት እንደለቀቀና አሁን ሰራተኛ በማጣት እንደተቸገረ አወጋኝ፡፡ በቃ የሰው መገናኛውና የስራውም መገኛው መንገድ አይታወቅምና በተግባባንበት አፍታ ሱቅ ውስጥ ገብቼ እራሴን ስራ ላይ አገኘሁት፡፡ ለመንገዴ እንቅፋት ለስራ አጥነቴም እረፍት የሆነኝ ዝናብ ወደመጣበት ሲመለስ እኔ ግን እዛው ሱቅ ውስጥ ቀረሁ፡፡

ሌላው ሀሳብ የሆነብኝ ምናልባት ከአንድ አመት በኋላም በሆነ ኮንስትራክሽን ውስጥ ለምህንድስና ለስራ መወዳደሬ አይቀርምና፤ ያኔ አሁን ከምሰራበት ሱቅ የሚፃፍልኝን የስራ ልምድን እንዴት ብዬ ከዶክመንቴ ጋር እንደማያይዘው ሳስበው ግን ይጨንቀኛል፡፡ ባለሱቁ እንዲህ ብሎ ስራ ልምዴን ይፅፍልኛል፦ “ አቶ እገሌ በድርጅታችን ውስጥ በቤት መጥረጊያና መወልወያ ሽያጭ ሰራተኛ ሆነው ላለፉት 12 ወራት በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በስራቸው ቅን እና ታታሪ ከመሆናቸውም በላይ ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁ ጠንካራ ሰራተኛ ናቸው፡፡ አቶ እገሌ ከደመወዛቸውም ላይ ተገቢውን ግብር ለመንግስት የከፈሉ መሆናቸውን እየገለፅን፤ ቀሪው የስራ ዘመናቸው የተሳካ እንዲሆን ድርጅታችን ከልብ ይመኛል፡፡ ከሰላምታ ጋር፡፡”

ልብ አድርጉልኝ በምህንድስና ተምሮ በሽያጭ መስክ ላይ ለተሰማራ ስራ ወዳድ ዜጋ የሚፃፍ የስራ ልምድ ነው፡፡ የሚገርመው መጥረጊያ ሻጬ ከሚከፈለኝ ጥቂት ሳንቲም ላይም ግብር ከፋይ መሆኔ ነው፡፡ እንዲህም ሰርቼ ለሀገሬ እድገት የበኩሌን አበረክታለሁ፡፡ ምናልባትም መንግስት ከእኔ የሚሰበስባት የስራ ግብር እድሏ ሆኖ መሰረተ ልማት ላይ ይሆናል የምትውለው፤ ምናልባትም በዚህ የስራ ልምዴ የምገባበት ኮንስትራክሽን ከእነዚህ መሰረተ ልማት ስራዎች አንዱን ሊገነባ እኔን መሀንዲስ ያደርገኝ ይሆናል ማን ያውቃል?

አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ሁሉንም ነገር አየር ላይ በተንጠለጠለ ተስፋ ሳይሆን እንደ አቅማችን አድርገነው ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ብድር የመመለስ ጭንቀትና እቁብ የመክፈል ውጥረት አይኖርብንም ነበር፡፡ለድግስና ለስራ ፍለጋ ሲባል ለደላላውም ለትራንስፖርትም ያበከንኩትን ገንዘብ አንዴ አሰባስቤ የራሴን ስራ ጀምሬበት ቢሆን ኖሮ አሁን የት በደረስኩ ነበር ቢያንስ እዳዎችን አቃልዬ የራሴ የሆነ ነገር ይኖረኝ ነበር፡፡

አዲሱ ገረመው

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/environment/item/13116-2017-06-16-19-09-50#sthash.xbg8sRI6.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy