Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአፍሪካ ቀዳሚው ምጣኔ ሃብት

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአፍሪካ ቀዳሚው ምጣኔ ሃብት

                                                       ታዬ ከበደ

ሰሞኑን የዓለም ባንክ የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት በተመለከተ አንድ ሪፖርት አውጥቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የታንዛንያ፣ አይቮሪኮስት እና ሴኔጋልን አስከትሎ በተያዘው የአውሮፓውያኑ ዓመት ከአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃ እንደሚይዝ የባንኩ ትንበያ አስረድቷል።

በተመሳሳይ ሁኔታም ኢትዮጵያ የኬንያን የምጣኔ ሃብት ዕድገት በመብለጥ የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት ቁንጮ ላይ እንደምትገኝ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ባለፈው ሚያዚያ ወር ባወጣው መረጃ መጥቀሱ ይታወቃል። ለዚህም በምክንያትነት የኢትዮጵያ ባለ ሃብቶች በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያላቸው ንቁ ተሳትፎና የውጭ አገሮች በዋናነትም የቻይና ባለ ሃብቶች ሀገሪቱን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ ማድረጋቸው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የመሪነት ደረጃ ላይ እንድትቆናጠጥ እንዳደረጋት የገንዘብ ተቋሙ አስታውቋል።

ታዲያ እዚህ ላይ ይህ የአፍሪካ ምጣኔ ሃብታዊ መሪነታችን በተያዘው የፈረንጆች ዓመት እንዴት ሊከናወን ቻለ? ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የደርግ ስርዓት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠንካራ ክንድ የዛሬ 26 ዓመት ገደማ በተገረሰሰ ማግስት፤ የመንግስት ዋነኛ ስራ በመላ ሀገሪቱ ተተብትቦ የቆየውን የደርግ የዕዝ ኢኮኖሚ አሰራር መዋቅር የመለወጥና የማሸነፍ ኃላፊነት ነበር። ዳሩ ግን የተመሰቃቀለውን የደርግ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ አሰራርን በ‘ነበር’ ለማስቀረት ቀላል ትግል አልጠየቀም። በዚህ ሂደት ውስጥም እስከ አራት ዓመታት ድረስ ያገለገለው የሽግግር መንግስት ውስብስብ አሰራሮቹን እያስወገደ በመምጣቱ፤ ሀገሪቱ ከነበረችበት ስር የሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እየተሰራ ለነበረው ዕመርታዊ ለውጥ በር ሊከፍት ችሏል። ይህ የለውጥ ምዕራፍም ተጠናቀቀ። ታዲያ እዚህ ላይ ‘ተጠናቀቀ’ ሲባል፤ በቃላት ሊገለፁ የሚይችሉ በጣም ፈታኝና አዳጋች ተግዳሮቶች መታለፋቸውን ልንዘነጋ አይገባም።

በዚህ ሂደት ውስጥም በወርሃ ህዳር 19987 ዓ.ም ሀገራችን አዲስና ደማቅ ታሪክን ለመፃፍ በቅታለች። መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደው፣ አምነውና ተስማምተው በገዛ ፍቃዳቸው ሀገሪቱን የምትመራበትን ህገ መንግስትን አፀደቁ፤ የዛሬ 22 ዓመት ገደማ። ህገ መንግስቱ የመላው ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራዕይን የሚያሳካ ሆኖ በመጽደቁም፤ ዛሬ በተጨባጭ በሀገሪቱ እየተመዘገቡ ያሉት ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቶች የእርሱው ፍሬዎች መሆናቸው አያጠያይቅም።

በመሆኑም ባለፉት 26 ዓመታት የሀገራችንንን ኢኮኖሚ ስር ከሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲሁም የህዝቡን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ስራ ላይ ውለዋል። ውጤታቸው ስኬታማ እንደነበርም ከእነዚህ ዓመታት በፊት የነበረችውንና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በማየት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል—“ማየት ማመን ነው” እንዲል ብሂሉ። የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር የጎላ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ልዩነት አላት። ደርግ ከእነ ዕዝ ኢኮኖሚዋ ባለ ባዶ ካዝና አድርጓት ጥሏት የሄደው የትናንትዋ ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ በበሊዮን የሚቆጠር በጀት መዳቢ ሆናለች።

ላለፉት ስድስት ዓመታት ተኩል ያህል በሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ ያለፈችውና በማለፍ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፤ የትናንት ቁስሏን ከመመልከት ይልቅ ህዘቦቿን በአንድነት እያሳተፈች በልማት ጎዳና በመገስገስ ላይ ትገኛለች። በዚህም ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የምትሻለዋን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል በመግቢያዬ አካባቢ የጠቀስኩትን ዓይነት ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦችን እያስመዘገበች በሂደት የምስራቅ አፍሪካን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት ለመምራት የምትችልበትን አቅም መገንባት የምትችል መሆኑን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጭምር እማኝነታቸውን እየሰጡ ነው።

ርግጥ ዓለም አቀፉ ተቋማት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያወጧቸው የትንበያ ዘገባዎች ለእኛ ከማሰብ አሊያም ኢትዮጵያን ለመጥቀም ከመፈለግ የመነጩ አይደሉም። በሀገራችን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የምጣኔ ሃብት አቅምን ከመተንበይ የተገኙ ግኝቶችን መሰረት አድርገው የሚያከናውኑት ተግባር መሆኑን ማንም የሚስተው ሃቅ አይመስለኝም። እናም በመጪው ጊዜያት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የቀጣናው መሪ ቢሆን ምንም የሚያስደንቅ ጉዳይ አይመስለኝም—ትናንት ሀገራችን በትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራች ያከናወነቻቸው ስራዎች ዛሬ ለምንገኝበት እምርታ ምቹ ምህዳርን መፍጠር የቻሉ ናቸውና።  

የደርግ ስርዓት ከወደቀ በኋላ ያንን የደቀቀ ኢኮኖሚ ለማቃናት ከባድ መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ አስቀድሞ የተተነበየ ጉዳይ ነበር። እናም በወቅቱ ተራራ የሚያክለውን የሀገሪቱን ድህነት ለመዋጋት ሶስት መርሆዎች መቀየሳቸውን እናስታውሳለን። በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት መንግስትና ህዝብ የተጓዙባቸው መንገዶች በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተንሰራፋውን ድህነት ለማሸነፍ ፈጣን ባለመሆናቸው፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ የዕድገትና ድህነትን የማስወገድ መርህ መዘርጋት አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሔ ሆኖ ተወስዷል።

እስከ የመጀመሪያው ተሃድሶ ዋዜማ ድረስ የፈራረሱና ያረጁ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋማትን ለማደስ፣ ኢኮኖሚውን ከኋሊት አዙሪት በማላቀቅ ወደፊት ለመመልከትና ትክክለኛ አቅጣጫን እንዲይዝ ለማድረግ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ቀላል አልነበሩም። በእነዚህ ዓመታት በዋነኛነት የመንግስት አስተዳደርንና ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልተማከሉ የማድረግ፣ ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ገበያ መር ስርዓት የማምጣት፣ በፖሊሲ መዛባት በጦርነትና በተፈጥሮዊ ክስተቶች ሳቢያ የተሽመደመደው ኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲቀየር የማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል። ውጤትም ተገኝቶባቸዋል።

ከመጀመሪያው ተሃድሶ መባቻ ጀምሮ በተወሰዱት ርምጃዎች የተሟላ ዝግጅት በመደረጉ እንዲሁም ህዝቡም መንግስት የቀረፃቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ በማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ወደ ተሻለ እመርታ ሊሸጋገር ችሏል።

ላለፉት 15 ዓመታት መንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎችን በተመረጠ አኳኋን በመስራቱ ብሎም ያሉትን ውስን ሃብቶች መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል እንዲሁም የልማት ሃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበትና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነትና ፍትሃዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲመጣ ተደርጓል።

በእኔ እምነት ከእነዚህ 15 የፈጣንና ተከታታይ ምጣኔ ሃብታዊ እመርታዎች ውስጥ ሀገራችን ባለፉት ስድስት ዓመታት ዕውን እንዲሆኑ ያደረገቻቸው የልማት ዕቅዶች የነበረንን የዕድገት ፍጥነት ይበልጥ ያጎኑት ናቸው። በተለይም የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ እጅግ በጣም የተለጠጠና ሊደረስበት የማይችል መስሎ ቢቀርብም፤ ሀገራችን አብዛኛዎቹን የዕቅዱን ውጤቶች ማሳካት ችላለች። ሁለተኛውንም ዕቅድ ማሳለጥ ከጀመረች ሁለት ዓመት ሊሞላት ነው።

ታዲያ ከሰሞኑ የዓለም ባንክ የተነበየው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የገለፀው የሀገራችን የአፍሪካ ቀዳሚ ምጣኔ ሃብት እመርታ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገቢራዊ እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው። ታዲያ ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በዕቅድ ዘመኑ የያዘቻቸውን ዕቅዶች እያሳካች መሆኑን ነው። እናም ዕቅዱ በ2012 ዓ.ም ሲጠናቀቅ የሀገራችን ምጣኔ ሃብት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ነብይ መሆን የሚጠይቅ አይመስለኝም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy