Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኩረጃን አምክኑ

0 410

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኩረጃን አምክኑ

ኢብሳ ነመራ

የ10ኛ ክፍል ፈተና ከግንቦት 23 እስከ 25፣ 2009 ዓ/ም ተሰጥታል። 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ገደማ ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል። ፈተናው ያለአንዳች ችግር  በሰላም ነበር የተጠናቀቀው። የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችም የ2009 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በመውሰድ ላይ ናቸው። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱት ተማሪዎች ቁጥር ከ288 ሚሊየን በላይ ነው። በሃገሪቱ ሁለት ፈተናዎች (የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል) በሃገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጡ የ8 ክፍል መልቀቂያ ፈተና በብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት ደረጃ የሰጣል።

ተማሪዎች ከክፍል ወደክፍል ለመዘዋወር በትምህርት ዘመን ተርም የሚወስዱት ፈተናም ሆነ ሃገር አቀፍና ብሄራዊ ፈተናዎች ግባቸው የተማሪዎችን ብቃት ፈትሾ ማረጋገጥ ነው። የተማሪዎችን ብቃት ማረጋገጥ ግብ ደግሞ የሃገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ ማስጠበቅ ነው። በየትምህርት ደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች የሚዘጋጅ ፈተና የተማሪዎችን ብቃት በማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ዓላማውን ማሳካት እንዲችል ተፈታኙ ተማሪ እጅ እስኪደርስ በምስጢር መጠበቅ አለበት። እያንዳንዱ ተማሪ ፈተናውን ለራሱ ብቻ እንዲሰራ ማድረግም አስፈላጊ ነው። ቅድመ ፈተና ፈተናዎች እንዳይሰረቁና በፈተና ወቅት ተማሪዎች እንዳይኮራረጁ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረገው ለዚህ ነው።

ፈተና ከመሰጠቱ በፊት ፈተናን በመስረቅ ይፋ የማውጣት ነገር በኢትዮጵያ የተለመደ አይደለም። 1980 እና 81 ዓ/ም ገደማ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተሰርቆ እንደነበረ የሚያመለክቱ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች አሉ። በወቅቱ የመገናኛ ቴክኖሎጂ እንደአሁን ስላልረቀቀና ስላልተስፋፋ ተሰርቆም ቢሆን ከተሰረቀበት አካባቢ አልፎ በመላ ሃገሪቱ አልተሰራጨም። መሰረቁ ይፋ ያለተደረገው ለዚህ ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት የ12ኛ ከፍል  አንድ ትምህርት ፈተና፣ ፈተናው ከመሰጠቱ አስቀድሞ ተሰርቆ እንደነበረ የታወሳል። በወቅቱ የ12ኛ ክፍል ፈተና ኮድ 14 የእንግሊዝኛ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱ በመረጋገጡና ሌሎች ፈተናዎች ተሰርቀው ላለመውጣታቸው ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ማግኘት ስላልተቻለ ሁሉም ፈተናዎች እንዲቋረጡ መደረጉ ይታወሳል።

ተሰርቆ የነበረው ፈተና በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨቱና ከመፈተኛ አዳራሽ አስቀድሞ በርካታ ተማሪዎቸ አይተውት ስለነበረ ፈተናነቱ አብቅቶ ነበር። እናም ፈተናው እንዲቋረጥ መደረጉ ትክክለኛ እርምጃ ነበር። እርግጥ ፈተናው እንዳይሰረቅ ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት። በወቅቱ ፈተናው በድጋሚ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተዘጋጅቶ ከአንድ ወር በኋላ ተማሪዎቹ እንዲወስዱ ተደርጓል። በድጋሚ የተዘጋጀው ፈተና ያለተሰረቀ ቢሆንም፣ ፈተናዎች የተሰረቁ በማሰመሰል የተለያዩ ፈተናዎች ከነመለሳቸው በማህበራዊ ሚዲያ ተለቀው እንደነበረ ይታወሳል። በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁት ፈተናዎች ሃሰተኛ ቢሆኑም ፈተናው አንድና ሁለት ቀናት በቀሩበት ጊዜ ተፈታኝ ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድረው ነበር። በተረጋጋ መንፈስ ለፈተና መዘጋጀት የነበረባቸው ተማሪዎች ተሰረቀ የተባለውን ፈተና ፍለጋ ሲባዘኑ ነበር። በተለይ ፈተናው አንድ ቀን ሲቀረው ማህበራዊ ሚዲያ ተቋርጦ በነበረበት ወቅት፣ ተማሪዎች ኔትዎርክ አለ ወደተባለባቸው አካባቢዎች በመሄድ ሲደክሙ ውለዋል። ሌሊቱን ሙሉ ተሰረቀ የተባለውን ሃሰተኛ ፈተና ሲያጠኑ ያደሩም በርካቶች ነበሩ። ተሰርቋል የተባለውን ፈተና ለመመልከት ከቤታቸው ውጭ የማያውቋቸው ሰዎች ቤት  ያደሩ ተማሪዎችም ነበሩ። ተሰረቀ የተባለውን ፈተና የማግኘት እድል ያጡት ደግሞ በመረበሽና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ነበር ወደፈተና አዳራሽ የገቡት። ይህ በተወሰነ ደረጃ በጥቂት ተማሪዎችም ላይ ቢሆን አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ ያለፈ መሆኑ አይካድም።

በያዝነው ዓመት እንደባለፈው ፈተና እንዳይሰረቅ የትምህርት ሚኒስቴርና የሀገር አቀፍ ፈተናዎችና ምዘና ኤጀንሲ ልዩ የጥንቃቄ ስርአት ዘርግተዋል። የትምህርት ሚኒስቴር የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ለስርቆት እንዳይጋለጡ ጥብቅ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ያስታወቀው ከፈተናው አንድ ወር አስቀድሞ ነበር። ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ባለፈው አመት በ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ ተከስቶ የነበረው የፈተና ስርቆት እንደማይደገም አረጋግጧል። ፈተናዎቹን በማሰራጨትና ቁጥጥር በማድረግ የሚሳተፉ ከ72 ሺህ በላይ ሰዎችን የያዘ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ ተደራጀቷል። ፈተናዎቹ በካሜራ የሚጠበቁበት ሁኔታም ስራ ላይ እንዲውል ተደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ ፈተናዎቹ እስከሚደርሱበት ቦታ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ቀደም ሲል ጥቅም ላይ የውሉ የነበሩ የፈተና ማሸጊያዎቹ እንዲቀየሩ ተደርጓል። ቀደም ሲል የነበሩት የወረቀት የፈተና ከረጢቶች በፕላስቲክ ማሸጊያ እንዲቀየሩ ተደርጓል።

የፈተናውን ምስጢራዊነት ከመጠበቅ ባሻገር ፈተና የተሰረቀ በማስመሰል ሃሰተኛ ፈተና በማሰራጨት በተፈታኞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ሃሰተኛ ፈተናዎቹ ሊሰራጩ የሚችሉበትን የማህበራዊ ሚዲያዎች የመዝጋት እርምጃ ተወስዷል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ተፈታኝ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያው በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይሸበሩና ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲፈተኑ ለማድረግ ሲባል ማህበራዊ ሚዲያው ተነጥሎ  እንዲዘጋ መደረጉን አስታወቋል። የማህበራዊ ሚዲያው ብቻ ፈተናው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በመላ ሀገሪቱ ለአንድ ሳምንት ያህል ዝግ ሆኖ ይቆያል።

ፈተናዎች ለተማሪዎች እስከሚሰጡበት ሰአት በምስጢርነት በመያዝ የብቃት መመዘኛነቱንና በአጠቃላይ የሃገሪቱን የትምህርት ጥራት ማረጋገጫነቱን  ለማስጠበቅ የተደረገው ጥረት መልካም ነው። ይሁን እንጂ ፈተናዎች የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ዓላማቸውን እንዳያሳኩ የሚያሰናክለው የፈተና መሰረቅ ብቻ አይደለም። ኩረጃም የፈተናን የብቃት ሚዛንነት በማዛባት ዓላማውን እንዳያሳካ ከሚያደርጉ ችግሮች መሃከል ቀዳሚው ነው።

የፈተና ኩረጃ በየትኛውም ሃገር፣ በማንኛውም የትምህርት ደረጃ የነበረና አሁንም ያለ ችግር ነው። ኩረጃ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አለ፣ በዩኒቨርሲቲዎችም አለ። ወደሃገራችን ሁኔታ ስንመለስ ኩረጃ እንደማንኛውም ሃገር በኢትዮጵያም ትምህርት በነበረበት ጊዜ ሁሉ ነበረ። ይሁን እንጂ በተለይ ባለፉ ሶስት አስርት ዓመታት በአዋጅ የተፈቀደ እስኪመስል ተስፋፍቷል። ኩረጃ አሁን ይፋዊ ገጽታ ተላብሷል። እንደነውር የሚታይበትም ሁኔታ በዚሁ ልክ ቀንሷል። አሁን በሃገራችን ያለው ሁኔታ ኩረጃ የሚሸከም ባህል ተፈጥሯል ለማለት የሚያስደፍር ነው ።

ኩረጃ በአዋጅ የተነገረ ይፋዊ ገጽታ እየያዘ የመጣው በ1970ዎቹ ማገባደጃ ላይ ነው። በወቅቱ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሃከል በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ብዙ ተማሪዎችን በማሳለፍ የመንግስትን እውቅና የሚያስገኝ ፉክክር ነበር። ታዲያ በዚህ ሶሻሊስታዊ የስራ ውድድር አሸነፎ እውቅና ለማግኘት የትምህርት ቤቶች አስተዳደርና መምህራን ጭምር የሚሳተፉበት የተደራጀ ኩረጃ የሚካሄድበት ሁኔታ ነበር። ትምህርት ቤታቸው ብዙ ተማሪዎችን ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲያስገባ በማደረግ የአሸናፊነትን እውቅና ለማገኘት መምህራን ጎበዝ ተማሪዎች ሌሎችን በማስኮረጅ ትምህርት ቤታቸውን እንዲያስጠሩ በይፋ ሃላፊነት የሚሰጡበት ሁኔታ ነበር። እናም በዚህ ወቅት ተማሪዎች የራሳቸው ያለሆነ ውጤት ይዘው ወደዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፤ ብዙዎቹ ትምህርታቸውን ከግብ ማደረስ አለመቻላቸው ግን እርግጥ ነው። የራሳቸው ያልሆነ ውጤት ካገኙት መሃከል በርካቶቹ በወቅቱ በሃገር ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚቀበሏቸው የማይተናነስ ቁጥር ላላቸው ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ይሰጡ ወደነበሩ ሶሻሊስት ሃገራት ሄደዋል።

ኩረጃ በዚህ ሁኔታ ጀምሮ እስካሁን ዘልቋል። አሁን አሁን ደግሞ የተደራጀ ኩረጃ የሚሰተዋለው በግል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው። አንዳንድ የግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በርካታ ተማሪዎችን በማሳለፍ ደንበኛ ለመሳብ የተደራጀ ኩረጃ እንዲካሄድ የሚያበረታቱ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። በአነዚህ ትምህርት ቤቶች በርካታ ተማሪዎች የእነርሱ ባልሆነ ወጤት ወደመሰናዶ የትምህርት ደረጃ ተሸጋግረዋል። ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገቡም አሉ። ይህ ኩረጃ ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ተዛምቷል። እርግጥ በከፈተኛ የትምህርት ተቋማት በስፋት የሚታየው ኩረጃ ከተርም የጥናት ጽሁፍ ጀመሮ እስከመመረቂያ የጥናት ጽሁፍ ባሉ ስራዎች ላይ ነው። የመመረቂያ ጥናት አሁን አሁን ገበያ ላይ ወጥቷል። ቸሁን ከአምስት ዓመት በፊት የመመረቂያ ጽሁፍ እናዘጋጃለን የሚሉ ማስታወቂያዎችን በታክሲዎች ላይና በተለያዩ ቦታዎች ተለጠፈው የሚታዩበት ሁኔታ ነበር። አሁን ማስታወቂያዎቹ በይፋ አይታዩ እንጂ የመመረቂያ ጽሁፍ ገበያው ግን ደርቷል። ታዲያ ይህ የጥናት ጽሁፍ ዘረፋ በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችም ዘንድ የሚስተዋልበት ሁኔታ አለ።

ይህ የሌሎችን የፈተና ስራና ጥናት በመወስድ የሚካሄድ ኩረጃ ችሎታ ያላቸውንና የሌላቸውን አደባልቆ ወደከፍተኛ የትምህርት እርከንና ወደሰራ ዓለም በማሰማራት ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ እንደባህል መያዙ ሌላ አደገኛ መዘዝ አለው። ኩረጃ የራስ ያልሆነን (unearned) ነገር በእጅ በማስገባት የግል ፍላጎትን የማርካት ድርጊት ነው። ኩረጃ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምረው የሚለማመዱትና የሚለማባቸው ሙስና ነው። የሙስና አመለካካት በትምህርት ቤት የሚዘራው በኩረጃ ነው። ኩረጃን በሚቀበል ባህል ውስጥ ያደገ ሰው በምክር የማይፈርስ የሙስና ግንብ ነው። ሙስናን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ደግሞ በኢኮኖሚ አይበለጽግም፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር አይበቅልበትም፣ ዴሞክራሲ አይጎለብትበትም። በመሆኑም የኢኮኖሚ ብልጽግና የማምጣት፣ መልካም አስተዳደር የማስፈንና ዴሞክራሲን የማጎለበተ አቅም ያለው ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት የነገው ትውልድ የሚበቅልባቸው ትምህርት ቤቶች ኩረጃን ያምክኑ።

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy