Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ውይይቱ !!

0 242

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ውይይቱ !!

                                  ታከለ አለሙ

ሰሞኑን በፋና ብሮድካስቲንግና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት የግንቦት ሃያን ሃያ ስድሰተኛ አመት የድል በአል አስመልክቶ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡  የፓናል ውይይት የኢህአዴግና የመንግስት ባለስልጣናትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ምሁራኖችን ታዋቂ ግለሰቦችን በተለያየ መስክ ያሳተፈና በፌደራሊዝም ላይ ሰፊ ውይይቶችና አንኳር ሀሳቦች በተለያየ እይታ የተነሱበት የሰከነ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ትምህርት ሰጭነቱ የጎላ ነው፡፡

ውይይቱ በርካታ ሀሳቦች የተንሸራሸሩበት የተለያዩ ግለሰቦች እምነታቸውን አመለካከታቸውን በነጻነት የተገለጹበት ነው፡፡ በየአመቱ የተመረጡ የታወቁ ሰዎችን በተመሳሳይ መድረክ መጋበዝ ተመሳሳይ ሀሳቦችን በመስማት ድንዛዜ ከመፍጠር ውጭ አማራጭ መፍትሔና ከችግር መውጫ መንገዶችን አያስገኝም የሚሉት አስተያየቶች ያመዝናሉ፡፡የመድረኩ አመራርም አመት ከአመት በመድረክ መምራት ፍቅር በከነፉ ሰዎች ተይዞ ነው የሚታየው፡፡ሀገሪቷዋ ሌሎች ሰዎች  የሏትም እንዴ እስኪያስብል ድረስ ይሄም ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ሌሎች ጋዜጠኞችን መቀየርም መሰላቸቱን ሊገታው ይችል ነበር፡፡ለውጥ ጥሩ ነው እንደ ተሀድሶው ሁሉ ሰዎችን መቀያየሩም አዲስ የውይይት መንፈስ እንዲፈጠር እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ሁሌም ቤተኞችን ከመጥራት አባዜና በሽታ ሊላቀቁ ይገባል፡፡

የሀገርም ሆነ የሕዝብ ችግር የሚፈታው በጥቂት ሰዎች በቡድን ወዳጆችን በመሰብሰብ መልካ መልካሙን ብቻ እንዲናገሩ በማድረግ አይደለም፡፡ይልቁንም እውነተኛውን ችግር በነቂስ አፍረጥርጦ አውጥቶ አሁን እንደተደረገው በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መወያየት ሰፊ ሀሳቦችን ማስተናገድ የተሻለውን ሀሳብ መውሰድ ለችግሮች ሁሉ ትልቅ መፍትሄ ያስገኛል ብሎ ማመንን ይጠይቃል፡፡ዲሞክራሲ ባሕሉና መስመሩም ይሄው ነው፡፡

መወያየት መነጋገር በሃሳብ መከራከር ልዩነትን ማክበር ብዝኃነትን መቀበል ሁሉም እኩል ነው ብሎ ማመን ለሁሉም የእኩል ሀገርነት የእኩል መብትና ተጠቃሚነት መቆም ልዩነት የውበትና የጥንካሬ እንጂ የመበታተን የመለያየት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል  እንደማይገባው መረዳትን ማወቅን ዲሞክራሲ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ወደድንም ጠላንም ተቀበልንም አልተቀበልንም ሁልጊዜም ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡በአግባቡ መያዝና ችግሮችን በሰላም መፍታት ነው ለሁሉም ወገን የሚበጀው፡፡

ይህንን ተፈጥሮአዊ አድርጎ በመያዝ መስራት ለውጥና እድገት ሊያመጣ ይችላል፡፡ልዩነትን በልዩነት ይዞና አቻችሎ በጋራ ሀገር ላይ የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ደግሞ በአንድነት ቆሞ መስራትን ዲሞክራሲ ይጠይቃል፡፡፡ውይይቱ በበለጠ ድምቀት ሊካሄድ ይችል የነበረ ቢሆንም ተሳትፎውና የሀሳብ ፍሰቱን በተመለከተ ሊበረታታ ሊቀጥልም የሚገባው ነው፡፡የዚህ አይነት ብዙ መድረኮች ያስፈልጋሉ፡፡

የፌደራል ስርአቱ ለኢትዮጵያ ጠቅሞአል አልጠቀመም፤የሕዝቡን አንድነት አጠናክሮአል አላጠናከረም፤የመበታተን አደጋን ቀርፎአል አልቀረፈም፤ፌደራሊዝሙ በቋንቋና በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በመልክአምድራዊ ሁኔታ ላይ አለመመስረቱ ያልታዩ ግጭቶች እንዲከሰቱ አድርጎአል፤አሁንም ችግሮቹ አልተፈቱም ለዚሕም መፍትሄ አላስቀመጠም ስለዚህም ዳግም የሕዝብ ውይይትና ይሁንታን ይጠይቃል የሚሉ ሀሳቦችም ተንሸራሽረዋል፡፡

ከደርግ ውድቀት በኃላ ኢትዮጵያ የመበታተንና የመገነጣጠል አደጋ ተጋርጦባት የነበረ ቢሆንም ይህንን ችግር የፈታው የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተከበረበት በራሳቸው ቋንቋ ባሕል ክልል አስተዳደር እንዲመሩ ሕገመንግስቱ ባስገኘው እውቅና ሁሉም አምነውና ወደው ተቀብለውት በመስማማት በመከባበር የትላንትዋ ኢትዮጵያ በአዲሰ መልክ በጸና መሰረት ላይ እንድትቀጥል አድርጓል፡፡

ሀገራዊ ልማትና እድገቱ ይሄንን መሰረት አደርጎ የመጣ ነው፡፡ይሄንን ማድረግ ባይቻል ኖሮ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የመገንጠል ጥያቄን ይዘው የተነሱበት ሁኔታ መከሰቱ አደጋውም የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር አንጋፋ የኢህአዴግ መሪዎች አስረድተዋል፡፡ ተከራክረዋል፡፡አሁንም ለሀገራችን ያለው አማራጭ ይሄው ብቻ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

በኢሕአዴግ ወገን አቶ አባይ ጸሀዪ፤አቶ ተፈራ ደርበው፤አቶ ስብሀት ነጋ፤አቶ ዛዲግ አብርሀ ይህንኑ ሀሳብ አጉልተው አሳይተዋል፡፡የፌደራሊዝም ስርአት ለኢትዮጵያ አዋጪ በመሆኑ ረገድ የቀረበ ክርክርና የጎላ የሀሳብ ልዩነት አልታየም፡፡

አከራካሪ የነበረው ምን አይነት የፌደራሊዝም ስርአት ይሁን የሚለው ነው፡፡በጂኦግራፊ ክልል እንጂ በቋንቋ ሊሆን አይገባም የሚሉትም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት መከፋፈልና የደም መፋሰስ ለማስከተሉ የሰርቪያና የዩጎዝላቪያን የሩሲያን ተሞክሮ በማንሳት ተከራክረዋል፡፡

የለም በስዊድን፣ በጃፓን፣ በቤልጂየምና በሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ገንብተው ኮሽ ሳይል ጦርነትም ውስጥ ሳይገቡ ይሄው ለዘመናት ኖረዋል፡፡ይህ እንደ ችግር ሊቆጠር አይገባም ሲሉ አቶ አባይ ጸሀዮ ገልጠዋል፡፡ፌደራሊዝሙ ለሀገራችን አዲስ ከመሆኑ አንጻር ሕገመንግስቱን ለማውጣት ከባልደረቦቻቸው ጋር ብዙ እንደደከሙና እንደሰሩ የገለጹት አቶ ማርቆስ ሕገመንግስቱን ለልጆቻችን ለተተኪው ትውልድ ለማስተዋወቅ ምንም አይነት ስር አለመሰራቱን ለመሆኑ ያውቁታል ወይ ብለው እስከ መጠየቅም ደርሰዋል፡፡

ማሳወቅ ማስተማር ጠቀሜታውን ማሳየት ይገባም ነበር፡፡በዚህ በኩል ትናንሽ ስራዎች ካልሆኑ በስተቀር በሰፊው ተሰርቶበታል ለማለት እንደማይቻል ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ሌላው ጎልቶ የተነሳው የፌደራሊዝም ስርአቱ በክልሎች ወሰንና ጉርብትና ላይ ሊነሱ የሚችሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አስቀድሞ ያስቀመጠው ነገር የለም፡ የሚለው ነው፡፡

ይህም በመሆኑ ዛሬም በአዋሳኝ ቦታዎች በጉርብትና በድንበር የሚነሱ ግጭቶችና ደም መፋሰስን እያስከተሉ መሆናቸውን በተለያዩ ክልሎች የተከሰቱትን ችግሮች በመጥቀስ አስተያየት ያቀረቡና መፍትሄ እንዲገኝለት የጠየቁም አሉ፡፡

ፌደራሊዝም በሀገር ደረጃ አብሮ ለመኖርና እንደሀገር ለመቀጠል የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበርን ስምምነትን ባሕልን ቋንቋን እምነትን ማክበርን በጽኑ የሚጠይቅ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ስርአት ነው፡፡ክልሎች ክልላቸውን የማልማት የማሳደግ የመምራት ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው ሲሆን አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡በመከባበር በመደማመጥ የሚደረግ የጋራ ጉዞ ነው፡፡

በፌደራል መንግስቱ የየክልሉ ወኪሎችና ተጠሪዎች ስላሉ የጋራ በሆነው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተመካክረው ይሰራሉ፡፡ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ማግኘት የሚገባቸውን ፍትሐዊ የገንዘብ መጠንና ድርሻም በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክርቤቱ ይወስናል፡፡

ሀገራችን የምትከተለው የፌደራሊዘም ስርአት ከፍተኛ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለ ነው፡፡የፌደራሊዝም ስርአት በመከባበር በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት እንዲገነባ መሰረት ጥሎአል፡፡የሰሞኑ ውይይት በጣም ሰፊ የሕዝብን ቀለብ ስቦ በንቃት ሲከታተለው የነበረ ነው፡፡ወይይቱ በሌሎች መድረኮች በስፋት ሊካሄድና ሊደጋገም ይገባዋል፡፡ለችግሮቻችን መፍትሔና የተሻሉ ሀሳቦችንም ያስገኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy