Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አመኔታ የጣለባት አገር!

0 751

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አመኔታ የጣለባት አገር!

ዳዊት ምትኩ

ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላም እንዲረጋጋ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ለሚያቀርባቸው ማናቸውም የሰላም ማስከበር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት፣ በአሁኑ ወቅትም የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ለዓለም ሰላም በመስራት እንዲሁም ከ850 ሺህ በላይ የቀጣናውን ስደተኞች በህዝባዊ መንፈስ በመያዝ እያበረከተች ያለችው ጉልህ ሚና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አመኔታን አትርፎላታል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለመጠበቅ ባደረጉት ጥረትና እያስገኙ ባሉት ውጤት የዓለም ህዝብ በሚገባ ያውቃቸዋል። ሀገሪቱን እየመራና በሰላም ጎዳና እያራመዳት ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የአካባቢያችን ሰላምና ልማት መረጋገጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሀገራችን ፈጣን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉ፤ በአካባቢያችን የተረጋጋ ሰላምና ልማት ያለመኖርም በሀገራችን ልማታዊ ጉዞ መሰናክል መሆኑ አንደማይቀር መንግስት ያውቃል።

የኢፌዴሪ መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ለምን ቢሉ የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በአካባቢያችንና በአህጉራችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት ስኬቶች መካከልም ረጅም ኪሎሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለማርገብ የተካሄደው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡

ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ሀገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታ ነበር። በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት፣ በዳርፉርና በአብዬ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት ሀገራችን የተጫወተችው ሚና እጅግ የላቀ ነው።

የኢፌደሪ መንግስት በጎረቤት ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ መሆኑ ለማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ምክንያቱም እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ እንደሆነ ይታወቃል። እርግጥም የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

በሀገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተጽዕኖ ያላት የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላሟን ዘላቂ ለማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኙ ነገር  በውስጥ የምታካሄደው የፀረ-ድህነትና ኋላ ቀርነት ትግል ሊሳካ የሚችለው ተጋላጭነታችን ሲወገድ ብቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጐረቤቶቻችን ላይ የሚያጋጥም ትርምስንና ቀውስን መፈታት ካልተቻለ ጦሱ ለእኛም መትረፉ የሚቀር አይደለም። ከዚህ አኳያ በፀጥታና በስደተኞች አማካኝነት በጋምቤላ አካባቢ በቅርቡ የተከሰቱ ችግሮችን ማስታወስ ዕውነታውን የሚያሳይ ይመስለኛል። በደቡብ ሱዳን በኩል ጥቃት ያደረሱት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎችና ሀገራችን በስደተኝነት የተቀበለቻቸው የደቡብ ሱዳን ዜጎች የሚፈጥሯቸው አለመግባባቶች የዕውነታውን ድባብ የሚያሰፉ ናቸው።

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በህዝበ-ውሳኔ ከተለያዩ በኋላ ቀጣናውን የተቀላቀለችው አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን፤ ለነፃነቷ የታገለችውን ያህል ሰለሟን ማስጠበቅ አልቻለችም። በዚያች አዲስ ሀገር ውስጥ በተቀናቃኞች መካከል በየወቅቱ እየተከሰተ ያለው ችግር ህዝቦቿ ከነፃነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ትሩፋቶች እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ፈጥሯል።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ሳቢያ እያሰለሱ የሚከሰቱት ግጭቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረጉና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ደግሞ የስደት ሰለባ ያደረጉ ናቸው።ይህ ደግሞ ሀገራችንን ጨምሮ ሰላም ወዳድ ኃይሎችን በአያሌው እያሳሰበ ነው። ሀገራችንም እስካሁን ድረስ እያካሄደች የነበረውን ብርቱ ጥረት በተጠናከረ ሁኔታ የሚጠይቅ ሆኗል።

ምንም እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት ከመነሻው ጀምሮ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ ይህን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ሁኔታ ላይ የሚገኝ ይመስለኛል። እናም የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ እየተጫወተ ላለው ሚና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ሰጥቶታል። አመኔታም ችሮታል።

በሶማሊያ ውስጥም አሸባሪዎች እንዳያቆጠቁጡ በአሚሶም ጥላ ስርም ይሁን ከአሚሶም ውጭ እያካሄዳቸው ያለው ሰላምን የማስጠበቅ ጥረት አድናቆትን ያስገኘለት ነው። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ተግባሯን በፍፁም ሰላም ወዳድነት እየተወጣች መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የሀገራችን መንግስትና ህዝብ የጎረቤት ሀገራትን ስደተኞች በመቀበል ረገድም ዓለም ያደነቀው ተግባርን እየከወኑ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ ባህሪውም የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚመለከት ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች እንደ ሁለተኛ ሀገር የምትቆጠር ሆናለች። የህዝቦችን ችግር የሚገነዘብ መንግስትና እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ ያለባት ሀገር በመሆኗ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች መጠለያ ሆናለች።

ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰ ማንኛውም መንግስት ከህዝብ ሰላምና ደህንነት ውጭ የሚያስበው ነገር የለውም። ይህ በመሆኑም የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች የራሱ ህዝቦች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ሳይቀር እንዲያገኙ እያደረገ ነው። ለዚህም የኤርትራ ስደተኞችን በምሳሌነት ማንሳት እችላለሁ። የኤርትራ ህዝብ አምባገነኑ የኤርትራ መንግስት በሚያደርስበት ከፍተኛ ጫና እንዲሁም በገዛ ሀገሩ ውስጥ የመኖር ዋስትና በማጣቱ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋል። ከእነዚህ ውስጥ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ ህፃናትና ወታደሮች ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጠባቸው በገዛ ህዝቡ ላይ “ተኩሰህ ግደል” የሚል ፖሊሲን የሚከተለውና የቀጣናውን ሀገራት የሚያሸብሩ ኃይሎችን በጉያው ውስጥ አቅፎ አካባቢውን ከሚያተራምሰው ከአስመራው አስተዳደር ጋር እንጂ፤  ወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ጠብ የለውም።

ይህ በመሆኑም ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማር እየተደረገ ነው። በእኔ እምነት ይህ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አቋም፤ ምን ያህል የህዝቦችን መከራና ስቃይ እንደሚገነዘቡ፣ ምን ያህል የጎረቤታቸው ህዝቦች የሰላም እጦት የራሳቸው ጭምር መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ምን ያህል ለጎረቤቶቻቸው መድህን ሆነውና የቀጣናው ህዝቦች ሀገራቸው ውስጥ ያላገኙትን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያገኙ በጋራ እናድጋለን ብለው በቁርጠኝነት እንደሚያምኑ የሚያሳይ ነው።         

ምዕራባውያን የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ አገራችን እንዳይገቡ በማለት በሚከለክሉበት ወቅት፤ ኢትዮጵያዊያን ምንም እንኳን እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ባይኖራቸውም ባላቸው አቅም የህዝቦችን ችግር እየተጋሩ መሆኑ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላት አድናቆት ቢቸራቸው የሚገርም አይደለም። ይህን ዓለም አቀፋዊ አመኔታ ያመጣው ህዝባዊና መንግስታዊ ባህሪይ በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy