Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሀገራችን ፈጣን እድገት

0 276

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሀገራችን ፈጣን እድገት

ዳዊት ምትኩ

መንግስትና ህዝብ ባካሄዱት ከፍተኛ ጥረት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች። በዚህም ከሰሃራ በታች ግዙፍ የነዳጅ ምርት ከሌላቸው ሀገሮች ደግሞ ከሰሃራ በታች ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ኢትዮጵያ የበርካታ ኢንቬስተሮችን ቀልብ በመሳብ ላይ ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ የኢፌዴሪ መንግስት በሀገራችን የተፋጠነ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፉም ባሻገር፤ በተግባር መተርጎም መቻሉ እንደሆነ ከማንም ከማንም የሚሰወር ጉዳይ አይመስለኝም።

በእርግጥ በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ለውጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ የጠራ መስመር የያዘ፣ ሀገራዊውን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ በተግባር ላይ የሚያውል አመራርና በህዝባዊ ተሳትፎ የተደገፈ አቅጣጫን የሚከተል የልማታዊ መንግስት አካሄድ የመኖሩ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።

ታዲያ የኢፌዴሪ መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የውጪው አለም እየመሰከረለት በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፤ ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም በስም ማጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩ ሃይሎች አልታጡም፡፡  

ይሁንና አንዳንድ የተቃውሞ ጎራ አባላትና የውጭ አጋሮቻቸው በሀገሪቱ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከመጥቀስ ይልቅ፤ የኢፌዴሪ መንግስት በባንክ፣ በቴሌኮምዩኒኬሽንና በኤሌክትሪክ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ያለማድረጉ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ አስመስለው ይናገራሉ።

እርግጥም የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱ ከገባችበት የድህነትና ኋላቀርነት ማጥ ለማውጣት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፤ የራሳቸውን ርዕዩተ-ዓለማዊ አጀንዳን ለማስጠበቅ ሲሉ የትችት ናዳን ሲያወርዱ የቆዩ ሃይሎች ስለመኖራቸው ለውድ አንባቢዎቼ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው። በዚህም ባንኮችን፣ ቴሌን፣ መብራት ሃይልን፣ አየር መንገድን፣ የከተማ ውኃና የመሳሰሉትን በፕራይቬታይዜሽን ማዕቀፍ ወደ ግል ሴክተር በርካሽ ለማሸጋገር አስገዳጅ ጫና እና ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። መሬት የህዝብ ሃብት ሆኖ ሳለ፣ እንዲሸጥና እንዲለወጥ የመገፋፋቱና የማስገደዱ ሁኔታም እንዲሁ።

ከዚህም አልፎ ተርፎ ሀገራችን የእነዚህን ሃይሎች ፍላጎት ማሟላት ካልቻለች የብድርና የዕርዳታ ተጠቃሚ እንደማትሆን በግልፅ በመጠቆም የልማት ግስጋሴያችንን በተቻላቸው መጠን ሊያደናቅፉ ሞክረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በእነርሱ የኒዮ ሊበራሊዝም ፖለቲካል-ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ካልተመራችና እርሱንም ተግባራዊ ካላደረገች ዕድገት ብሎ ነገር እንደማይታሰብ ሲያሳስቡና ሲያስታውቁ መቆየታቸው ዛሬም ድረስ የምናስታውሰው ነው። ጉዳዩ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ሀገፈራችን ራሷ በመረጠችው መንገድ የልማት አብነት ሆነች እንጂ።

እንደሚታወቀው ባለፉት 26 ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ተአምራዊ የለውጥ ጉዞ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ‘መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም’ የሚለውን የኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የማያስኬድ መሆኑን በተግባር በማስመስከር ችሏል፡፡

ለዚህም ነው በኒዮ- ሊበራሊዝም ጥላ ስር የተሰባሰቡ የርዕዮቱ አራማጆች በምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ ሲዘፈቁ ሀገራችን ግን የጀመረችውን የፈጣን ልማትና የዕድገት ጉዞ በአስተማማኝ ሁኔታ በማስቀጠል ላይ የምትገኘው፡፡

ታዲያ ከዚህ እውነታ እንደምንረዳው ነገር ቢኖር፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው ልማታዊ አቅጣጫ ሌሎች የአለማችን ሀገሮች ከኒዮ- ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ውጭ ማደግ እንደሚቻል እንዳፍታ ቆም ብለው ማሰብ እንደለባቸውና ተጨባጭ ሁኔታቸውን ያገናዘበ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ ለዕድገት መብቃት የሚችሉ መሆናቸውን ነው፡፡ እናም ሃቁ ይሄ ሆኖ ሳለ፤ የተቃውሞው ጎራና የውጭ አጫፋሪዎቻቸው በሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን የኢንቨስትመንት ተጨባጭ ሁኔታ የሚያደበዝዝ ዘገባ በስተጀርባው የተደበቀ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን መመልከት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው።

ሀገራችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል። በመሆኑም ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ምን ያህል ሁሉም ሀገር የሚፈልጋት መሆኗን ያረጋግጣል።

ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራዊው ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ሀገሪቱ ለዘመናት ከምትታወቅበት የድህነትና የኋላቀርነት ታሪክ በሂደት እየቀየረ ከመሆኑም በላይ፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባሰገኘው ልማታዊ እመርታ ለአለም ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡

እንደሚታወቀው የአንድ ሀገር ህዝብ በምግብ ሰብል ራሱን ችሏል የሚባለው በሀገሪቱ ከተመረተው አጠቃላይ ምርት የሚኖረው የነፍስ ወፍ ድርሻ ተሰልቶ ነው። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ህዝብ የነፍስ ወከፍ የምግብ ሰብል ድርሻ ሲሰላ በወር ሶስት ኩንታል መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም በምግብ ሰብል በአብዛኛው ራሳችንን መቻላችንን የሚያመላት ነው። በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የድርቅና የረሃብ አደጋ ማንም ሰው እንዳይሞት ዋስትና ሆኗል ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው  የበለጸጉት  ሀገሮች  ለመልማት  ባደረጉት  እንቅስቃሴ  በዓለማችን  ሥነ – ምህዳር  ላይ በፈጠሩት  ቀውስ  ሳቢያ  በሚፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የተለያዩ አህጉሮች  በድርቅ  አደጋ ይጠቃሉ፡፡  ከእነዚህም ውስጥ  እንደ አፍሪካ  ያሉ ያላደጉ አህጉሮች ባልፈጠሩት ችግር ግንባር ቀደም ሰለባ ይሆናሉ፡፡  በተለይም  የምስራቅ አፍሪካ  ሀገሮች  የችግሩ  ተጠቂዎች  ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህ የበለጸጉት ሀገሮች  በፈጠሩት የአየር መዛባት  ምክንያት  በድርቅ  የምትጠቃው  ሀገራችን፤ ከድህነት ገና ሙሉ ለሙሉ ያልተላቀቀች  በመሆና የአየር ንብረቱ  የተለየ ክስተት  ሲያሳይ  በአንዳንዱ ዝናብ  አጠር  አካባቢዎች የምግብ  እጥረት  መከሰቱ የግድ ነው፡፡

ምንም  እንኳን  ድርቅና  ረሃብ  በአመዛኙ  በተፈጥሮ  የአየር  መዛባት  ምክንያት  የሚፈጠሩ  ቢሆኑም፤ ድርቅ በዝናብ  እጥረት   ሳቢያ  የሚፈጠርና  ጊዜያዊ  የምርትና  ምርታማነት  መስተጓጎልን  ሊያስከትል  የሚችል  ችግር ነው፡፡  ረሃብ ግን በተከታታይ  በሚፈጠር ድርቅ ሳቢያ በሚከሰት  የምግብ  እጥረት  ህብረተሰቡ  የሚላስና  የሚቀመስ  ሳይኖረው  በመቅረቱ  ለሞት  የሚያበቃ  ችግር  መሆኑ  ይታወቃል፡፡

እርግጥ ከሀገራችን ተጨባጭ  ሁኔታ  አኳያ  ድርቅ  እንጂ፤ ረሃብ  አለመኖሩ ከዚህ አንፃር ከሚያቀነቅኑ ወገኖች  የተሰወረ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ይሁንና  ጉዳዩን  የፖለቲካ  ማራገቢያ  ለማድረግ  ሲሉ ድርቁን ሆን ብለው ወደ ረሃብነት ቀይረውታል፡፡

እውነታው ይህ አይደለም፡፡ አሁን  ባለው  የኢትዮጵያ  ሁኔታ የተከሰተው ድርቅ ሊኖር ካልቻለ በስተቀር ረሃብ ግን የለም፡፡ በሀገሪቱ  በረሃብ  ሳቢያ  የሞተም  ሆነ  የሚሞት  አንድም ሰው የለም፡፡ ምክንያቱም  መንግስት  ረሃብ እንዳይከሰት ከፍተኛ  ስራዎችን  በማከናወኑ ነው፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆይቷል፡፡ መንግስት ከአጭር ጊዜ  አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ  እንዲሁም  ድጋፉ ልማታዊ  በሆነ አኳሃን  ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርቁ ወደ ረሃብነት እንዳይሸጋገር የሚያደርጉ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ይህም አንድም ሰው እንዳይሞት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ መንግስት ለዜጎቹ ያለውን ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት  ያመላክታል፡፡

በአጠቃላይ የሀገራችን ልማት ፈጣን ባለፉት 26 ዓመታት ውጤታማ ነበር፡፡ ይህ ውጤትም ህዝቦችን በየደረጃው በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡ በቀጣይም የኢትዮጵያ ህዝቦች በሚያደርጉት ጥረት ማደጉ አይቀርም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy