የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ያለህ የሚለው ዘርፍ
ስሜነህ
ኢትዮጵያ በግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ የምትመራ መሆኑ አያጠያይቅም። የግብርና ልማቱን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በማስተሳሰር በዘላቂነት ኢንዱስትሪውን በአስተማማኝ መንገድ ለማሳደግ በአንደኛውና ይበልጥ ደግሞ አሁን በተያያዝነው የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሚገባ እየተተጋ ነው።በእቅዱ መሠረት ግብርና መር የሆነውን የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት መሠረት በአገሪቱ ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት በማሳደግና በሂደት የምጣኔ ሀብቱ መሠረት እንዲሆን ለማድረግ የታለመ ነው።
ዘርፉ ኮንስትራክሽን፣ የኃይል ምንጭ፣ ማዕድንና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልልነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ የካፒታል ወጪ የጠየቁና ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው ወደ ማምረት ተግባር ተሸጋግረዋል። በርካታ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እያረጋገጡ ነው ። አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍና በአግባቡ በመተግበር ባለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት የሚያበረታታ የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ መቻሉንም እነዚሁ ተቋማት እየመሰከሩ ነው።
በሁለተኛው ዙር እቅድ በግልጽ እንደተቀመጠው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከ446 ነጥብ 5 ሚሊዮን እስከ 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚያስችል ነው።በእቅድ ዘመኑ መጨረሻም ዘርፉን እስከ 23 እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።እነዚህ መረጃዎች ጨምረው እንደሚገልጹትም የጨርቃጨርቅ አልባሣት፤ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች በ2003 ዓ.ም የነበረው የወጪ ንግድ አፈጻጸም 62 ነጥብ 22 እና 104 ነጥብ 34 ነበር። መረጃዎቹ በተመሣሣይ መልኩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች፤ የፋርማሲዩቲካልና የኬሚካል ውጤቶች 34 ነጥብ 45 እና 6 ነጥብ 91 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የሚገልጹ ቢሆንም ከታለመው አንጻር አሁንም እጅግ ወደኋላ የቀረን መሆኑን ያመላክታሉ ።
የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂው መነሻ እንደ አገራችን ባሉ ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት በመናድ በምትኩ የልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መገንባትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። የተቀየሰው ስትራቴጂ በአገሪቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችልና ህዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ ሊጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆን እንደለበት ታምኖበት ተግባራዊ ተደርጓል። ከዚህም ባለፈ በከተሞች ለዴሞክራሲ ማበብ የሚበጅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታን የሚፈጥር መሆን ያለበት መሆኑን በማመን ባለፉት 25 አመታት ርብርብ ተደርጓል።
በበርካታ የምጣኔ ሃብታዊ ምሁራን አስተያየት መሰረት ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ውድድር ላይ የመግዛት እንጂ የመሸጥ ተሳትፎዋ እጅግ አነስተኛ ነው ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የማኑፈክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ሚና አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ይጠቅሳል ። ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ስለሚሻ እና ጠንካራ የማኔጅመንት ክህሎትንም ስለሚጠይቅ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አልሚ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዳይሳተፉ ካደረጓቸው ምክንያቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ናቸው። ስለሆነም የባለሃብቶቻችን ትኩረት ትንሽ ጉልበትና ወጪ በሚጠይቁት ላይ፤ይልቁንም ኢምንት ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል በሚፈጥሩ የመዝናኛ እና የሆቴል አገልግሎት ስራ ላይ ተንጠልጥሎ አመታትን አስቆጥሯል።
ኢንቨስተሮች ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል በዋናነት የመሬት እና የባንክ ብድር ሲሆኑ ሌላው እና ግዙፉ ፈተና ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የነበረ መሆኑ ይታወቃል ። በተለይ መሬት ለማግኘት ስለኪራይ ሰብሳቢነት ያለው ውጣ ውረድ አሰልቺና ቋቅ የሚያደርግ መሆኑም የአደባባይ ሃቅ ሆኖ አመታትን ማስቆጠሩም ይታወቃል ።
መንግሥት በአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ኢንዱስትሪ ወሳኙ ዘርፍ መሆኑን በመገንዘብ ቢተጋም የሃገር ውስጥ ባለሃብቱን ጆሮ ለማግኘት እንዳልቻለ በርካታ አስረጂዎች ማቅረብ ይቻላል። በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ከውጭ ባለሃብቶች እጅግ በወረደ ደረጃ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ለዘርፉ ያላቸው ፍላጎት አንሶ መገኘቱ የመጀመሪያው ነው ።
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዓመታት ከማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ ከጠቅላላው የአገራዊ ኢኮኖሚ ድርሻው ከአምስት በመቶ በታች ሆኖ ለመመዝገቡ ምክንያቱ የሃገር ውስጥ ባለሃብቱ ከዚያ ሁሉ ማበረታቻም ጋር ፍላጎት ካለማሳየቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ዝቅተኛ አፈጻጸም ከግብርና ዘርፍ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማፋጠን የሚደረገው ርብርብ መስፋፋት እንዳለበት የሚጠቁም እና ዘርፉ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስመዘግብ የግል ባለሀብቱ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ የሚያጠይቅ ነው፡፡
የግል ባለሀብቶች ግን በሚፈለገው መጠን ወደ አምራች ዘርፉ እየመጡ አለመሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ እንደ ንግድ ምክር ቤት ያሉ የግሉ ዘርፍ ወኪል ተቋማትም አባሎቻቸውም ሆኑ ሌሎች አካላት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚያግዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደማይታዩ ይነገራል፡፡
በመንግሥት ውጥን በቀላል ማኑፋክቸሪንግ መስክ ኢትዮጵያን የአፍሪካ እምብርት ለማድረግ እንዲቻል የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ እንደጠበቀ ሆኖ ዘርፉን ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዳይመጣ ያላስቻሉ ምክንያቶች እንዳሉ፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል ለተለያዩ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኖች ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ችግር ሆነው ከሚታዩት አንዱ በቂ የግንዛቤ ሥራ አለመሠራቱ ዋነኛው እንደሆነ በምክር ቤቱ በኩል ተመልክቷል ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ትርዒትና ኩነት ዳይሬክተሮች ዳይሬክተር ወ/ሮ ባግናወርቅ ወልደ መድኅን እንደሚጠቅሱት፣ ለኢኮኖሚው ዋልታ በሆነው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ባለሀብቶች ገብተው እንዲሠሩ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም የሚያጠግብ ለውጥ አልመጣም፡፡ ስለዚህ በተለየ ዘዴ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ የቢዝነስ ሩጫ ለማሰናዳት ተነስተናል ይላሉ፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የግሉ ዘርፍ በሚጠበቀው መጠን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ያልገባበት አንዱ ችግር ግንዛቤ ማስጨበጥ ስላልተቻለ ነው፡፡