Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴው ግድብ በመርህ እንጂ በዘፈቀደ የሚመራ አይደለም!

0 393

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴው ግድብ በመርህ እንጂ በዘፈቀደ የሚመራ አይደለም!

                                                         ቶሎሳ ኡርጌሳ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም። የቀጣናው፣ የተፋሰሱ ብሎም የአፍሪካ ኩራት ጭምርም ነው። ግድቡን በላባቸው ወዝ እየገነቡት ያሉት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይህን ግድብ ከጀመሩ ስድስት ዓመታት አልፏቸዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ድሎችን ተጎናፅፈዋል። በዚህም ራዕያቸውን በማሳካት ላይ ይገኛሉ።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በህዝቦች ተሳትፎና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዟል። በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል። በዚህም ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በተግባሩም ከስድስት ዓመት በላይ ዘልቀናል።

በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ይህም ሀገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ዘውግ በመፍጠርም የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት በአመዛኙ ወደ እኛ እሳቤ ማቅረብ የቻለ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

እርግጥም ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል። ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች ቢሆኑ አሁን ለደረሱበት ካለፈው ጊዜ የተለሳለሰ የአቋም ለውጥ መሰረት ምክንያት የሆነ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ስትገልፅ ቆይታለች፡፡ እርግጥ ሀገራችን የኢንቴቤውን ስምምነት ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው።

በዚህ የግንዛቤ መነሻዋም የተፋሰሱ ሀገራት የኢንቴቤውን ስምምነት እንዲፈርሙ ለዓመታት ያላሰለሰ ጥረቶችን አድርጋለች። ይህ ጥረቷም ቀደም ሲል ስምምነቱን ላለመቀበል ስታንገራግር የነበረችውን ግብፅን ጭምር በቅርቡ ‘ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ስምምነት ልመለስ’ የሚል ጥያቄ እንድታነሳ ጭምር አድርጓታል። ይህም ሀገራችን በግድቡ ዙሪያ በፊትም ይሁን አሁን የያዘችው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

የሀገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መሰረቱ የተጣለውና የሀገራች ህዝቦች ችቦውን እየተቀባበበሉ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉትና ለፍፃሜው እንደሚያበቁት እየገለፁት ያለው ይህ ግድብ፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም፤ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል።

አዎ! ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የ“ይቻላል” መንፈስን መፍጠር የቻለና ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “ኑ አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን።

ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች።

ታዲያ ይህን የኢፌዴሪ መንግስት በጋራ የመልማት መርህን ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ የመጡ ይመስላል—ብቅ ጥልም የሚለው አቋማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚገነባ ፕሮጀክት በመርህ ላይ የተመሰረተ እንጂ በዘፈቀደ የሚመራ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝቦች የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ዓላማ የላቸውም።

የህዳሴው ግድብ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመርኩዞ ሁሉም ሀገራት እንዲጠቀሙ ከማለም የመነጨ ነው። ይህን የትኛውም ሀገር ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም የሀገራችን ህዝቦችም ይሁኑ መንግስት ለህዝብ የሚያስቡ እንጂ የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች ተጠቃሚነትን የሚጋፉ አይደሉም። የትኛውም የተፋሰሱ ሀገር ከዚህ ቀደም አድርጎት በማያውቀው መልኩ ህዳሴው ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ለማስጠናት በራቸውን ክፍት ያደረጉትም ለዚሁ ነው። ታዲያ ይህ የጋራ ተጠቃሚነት መርሆዋቸው መቼም ቢሆን የሚቀለበስ አይሆንም።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy