Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴያችን ፈር ቀዳጅ

0 257

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴያችን ፈር ቀዳጅ

                                                        ታዬ ከበደ

የኢትዮጵያ ህዝቦች በአዲስ የህዳሴ ጎዳና ላይ ይገኛሉ። በዚህ ጎዳና ላይ የህዳሴያቸውን ፈር ቀዳጅ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን እያደረጉ ነው። እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ከተደረገ ጀምሮ፤ ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉም እንደየ አቅሙ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ እንዲሁም ቦንድ በመግዛት እስካሁን ያበረከቱት አስተዋፅኦ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡

ሀገራችን ለዘመናት በድህነትና በኋላቀርነት የኖረች ናት፡፡ ህዝቦቿ ለዘመናት የልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ሳቢያም የረሃብና የድርቅ ሰለባ ሆነው ዘመናቸውን አሳልፈዋል። ይህን ዕውነታ ማንኛውም የዓለም ማህብረሰብ ሲናገረውና ህዝባችንን ሲያሸማቅቅ የኖረ ሃቅ ነው። እንዲያውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገራችን ስያሜ በመዝገበ ቃላት ላይ ሳይቀር የረሃብ ትርጓሜውን ለማስረዳት በምሳሌነት ይጠቀስ ነበር፡፡

ይሁንና ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ነባሩ የሽንፈትና የድህነት ካባ ቀስ በቀስ እየተቀየረ በመምጣት ላይ መሆኑ ከማንም በላይ ምስክር የሚሆነው የችግሩ ተቋዳሽ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡

በተለይም መንግስት ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሶ ምልዕዓተ ህዝቡን ባሳተፈ አኳኋን የጀመረው ያልተቋረጠው ርብርብ ባለፉት 15 ዓመታት ውጤታማ ፍሬ ማፍራት ታሪካችንን በአዲስ መልክ ቀይሮታል። ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ በአዲስ መዝገበ ቃላት ላይ መመዝገብ ችለናል—ከሰሃራ በታች ነዳጅ ከሌላቸው ሀገሮች ቀዳሚ የዕድገት ተምሳሌት በመባል።

ይህም የሀገራችን ህዝቦች ‘ድህነት በቃን’ በማለት ከዚሁ ቀደም አስሮ የያዛቸውን የ“አይቻልም” መንፈስን “በይቻላል” የቀየሩበት ታላቅ የልማት ፕሮጀክት አንዱና ዋነኛው የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስራውን ከተጀመረ እነሆ ድፍን አምስት ዓመታትን ሊያስቆጥር በጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ብቻ ይቀሩታል፡፡ የህዳሴያችን ፈር ቀዳጅ ከሆኑት የልማት ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ ፕሮጀክት፤ የዚህ ትውልድ አሻራ በመሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ የልማት ተቋም ነው፡፡

ከዘመናት በፊት ያለፈው ትውልድ ለእኛ አወርሶን የሄዱው የአክሱም፣ የጎንደርና የላሊበላ ስልጣኔ- ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ጥበብ በመሆኑ በኩራት ለቱሪስት መስህብነት እየተጠቀምንበት ያን ትውልድ እያስታወስነው ነው፡፡

የእኛው ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። ይህም ለመጪው ትውልድ ልማትን እንጂ ልመናን ያለማውረስ ራዕይን የሰነቀ ነው፡፡

የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት በታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ለግንባታው አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን መልካም ተግባራቸውን አሁንም በልበ ሙሉ አጠናክረው እየቀጠሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለግንባታው ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል መንግስት ያዘጋጀውን ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ተወጥቷል፤ በመወጣትም ላይ ይገኛል፡፡ የቦንድ ግዥውን እያከናወኑ ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ናቸው—ከህፃን እስከ አዋቂ ድረስ። ለዚህም ነው  ‘የህዳሴው ግድብ ግንባታ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ ፕሮጀክት ነው’ እየተባለ የሚነገረው፡፡

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈጸሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማነሳሳት ረገድ እየተጫወቱት ያለው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያውያን የትላንት ታሪክ ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር በአንድ ላይ በመዝመት ጠላት ላይ ድል መንሳት ነበር፡፡ ይሁንና ከዚህ ሀገርን ከጠላት መከላከል ተግባር በዘለለ ህዝቡ ለልማት የተባበረ ክንድ እንዳይኖረው ያለፉት መንግስታት ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ነገር ግን የኢፌዴሪ መንግስት የትኛውም የሀገራችን ቀደምት መንግስታት ደፍረው የማያውቁትን በአባይ ወንዝን የመጠቀም መብታችንን ካወጀ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በተገኘው የልማት አጋጣሚ ያለ ዕረፍት እየሰራ ነው። ወትሮም ቢሆን ይህ ድህነት ያንገሸገሸው ህዝብ እንስራና ሀገር በጋራ እንገንባ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና አይደለም፡፡

ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉት ወገኖቻችን ጭምር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉት ያለውን ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከምንም በላይ ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው ማልማት እንዲችሉና ድህነትን ታሪክ በማድረግ ዘመቻ ላይ በጋራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያነሳሳ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy