Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህግ የበላይነትና የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ

0 371

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህግ የበላይነትና የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ

ዳዊት ምትኩ

በማንኛውም ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው፤ ሀገሪቱ የሚያጋጥማትን በወቅቱ የሚያጋጥማትን ችግሮች ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ ነው። በስራ ላይ ያሉት መደበኛ አሰራሮች የተፈጠረውን ችግር መቋቋም ሲያቅታቸው አዋጁ እውን እንዲሆን ይደረጋል። በዚህም የተፈጠረውን ችግር ተቆጣጥሮ  ሀገሪቱ ከተደቀነባት ግልፅና ወቅታዊ አደጋ ለማውጣትና ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስ እንዲቻል ነው።

አንድ አዋጅ የሚወጣው ተፈፃሚ እንዲሆን በመሆኑ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተለያዩ አካባቢዎች በይፋም ሆነ በድብቅ በህዝቦች መካከል መቃቃር፣ ጥርጣሬንና ግጭትን የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ይከለክላል። እንዲሁም በህዝቦችና ሃይማኖቶች መካከል ግጭትና መቃቃር የሚፈጥሩ ፅሑፎችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት ብሎም ትዕይንቶችንና ምልክቶችን ማሳየትና መተግበርንም ያግዳል። የህዝብንና የሀገርን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚጥሉ በኮማንድ ፖስቱ የታመነባቸው ማናቸውም የመገናኛ ዘዴዎች ሊዘጉ ይችላሉ።

እርግጥ አዋጁ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈፃሚነት ያለው ቢሆንም፤ እንደየአስፈላጊነቱ በልዩ ሁኔታ አዋጁ እንዲተገበርባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የመሰብሰብ፣ የመሰለፍና፣ የመደራጀት መብቶችም ሊታገዱ ይችላሉ። በሁከት ብጥብጥ ተግባር መሳተፉ የተጠረጠረና የተሳተፈ ማንኛውም ግለሰብ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር እንዲውል ይደረጋል። እነዚህ ግለሰቦች ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ በህግ አግባብ መጠየቅ ያለባቸውም እንዲጠየቁ ይደረጋል።

ዜጎች በህገ-መንግስተ የተጎናፀፏቸው ሰብዓዊ መብቶችና በቪየና ኮንቬንሽን ላይ የሰፈሩት የዲፕሎማቲክ መብቶች የሚጣሱ አይደሉም። ለዚህም የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተል አካል እንደሚቋቋም አስታውቀዋል። ይህ ዕውነታ የሚያሳየን ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ብትሆንም በተቻለ መጠን የዜጎቿን ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅና ለዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የምትገዛ መሆኑን ነው። እናም ሀገራችን አዋጁ በሚቆይባቸው ጊዜያት ውስጥ ወደ ነበረችበትና በዓላም አቀፉ ማህበረሰብ ወደምትታወቅበት የሰላም ተምሳሌትነት እንድትመለስ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ትብብር አድርጓል።

እርግጥ አዋጁ በህዝብ በህዝብ የነቃ ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው። ህዝቡ የሰላሙ ጠባቂ ነው። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል። ርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ከሀገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ላለፉት 26 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የሀገራችን ሀዝብ ይመስለኛል።

ርግጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ሃይሎችና በሀገራችን የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሰላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበረ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። የሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖችም የተሃድሶ ትምህርት ወስደው በሁለት ዙሮች ተመርቀዋል። በሁከቱ ወቅት የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቃል በመግባትም ወደየመጡበት አካባቢዎች ተመልሰዋል።

በቅድሚያ እነዚህን አጥፊ ዜጎች በመጠቆምና ለእርምት ወደ ተሃድሶ ማዕከሎች እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የህዝቡ የማይተካ ሚና እዚህ ላይ ሊደነቅ የሚገባው ይመስለኛል። ይህም ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው። በዚህም ሳቢያ ህዝቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው ሰላም ሙሉ ለሙሉ ስላልተረጋገጠ እንዲራዘም ፈልጓል።

ለዚህ የራሱ ምክንያት አለው። ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ በሁከት እና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም ቀሪዎች አሉ።

ከዚህ በተጨማሪ በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች በጥቂት ቦታዎች ላይ በመታየታቸው አዋጁን ማራዘም አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪም የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ሙሉ ለሙሉ እውን ለማድረግና ሰላማችን ዳግም የማይቀለበስበት ደረጃ እንዲደርስ አዋጁ እንዲራዘም ምክንያት ሆነዋል።

ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ ፍላጎት እውን ሊሆን አይችልም። ይሁንና ሁሌም እዚህ ሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የማይሹ ሁከትና ብጥብጥ ናፋቂ ፅንፈኞች አዋጁ የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ የገደበ አስመስለው ሲናገሩ ይደመጣል። በእኔ እምነት ይህ ፍፁም ሐሰት ነው። ሁከትና ብጥብጥ ናፋቂዎች ይህ ቅጥፈት የሚያስወሩት እንደለመዱት ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዳይኖርና የተጀመረው የልማት ዕድገት እንዲስተጓጎል ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ነው።

እንደ አውነቱ ከሆነ የአዋጁ መተግበር ኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎች ላይ እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ አላሳደረም። በየጊዜው እንደ ሁኔታው እየተነሳ የመጣና የዜጎች መብትና ግዴታዎች በመሰረታዊ የህግ ማዕቀፎች እንዲታዩ አድርጓል።

ይህ ሁኔታም አዋጁ ተገድበው የነበሩ አንዳንድ የዜጎች መብቶችን ምን ያህል በፍጥነት ወደ ቦታው እንደመለሰ የሚያሳይ ነው። እንዲያውም በአሁኑ ወቅት በሁሉም ሊባል በሚችል የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ ዜጎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር መሆናቸውን እንኳን የሚያውቁ አይመስለኝም። ምክንያቱም በየቦታው የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗን የማያመላክቱ ስለሆኑ ነው።

እናም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩት ሌሎች አካላትን ለማስደሰት ሲባል አይደለም። እነዚህ መብቶች ዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚጎናፀፉት መብቶች እንጂ በአዋጅ የሚነጠቋቸው ቁሳቁሶች አይደሉም። እነዚህ መብቶች በህገ መንግስቱ ውስጥ የተካተቱና ላለፉት 26 ዓመታት ዕውን እየሆኑ የመጡ ናቸው። ይህን ሃቅ ፅንፈኞች ሊያጣምሙት ቢችሉም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ በሚገባ ይገነዘበዋል።

ለነገሩ አንድ አዋጅ ሲታወጅ ለአጠቃላዩ ህዝብ ደህንነትና መብቶች በመከበር ብሎም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማሰብ እንጂ ሌላ የተለየ ዓላማን በመያዝ አይደለም። ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል በመሆናቸው የየትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል እንቅስቃሴን ለመገደብ ተብሎም አይወጣም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም መታየት ያለበትም ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ አኳያ ነው።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy