CURRENT

የሆሊውድ ኮከቧ አንጀሊና ጆሊ ከቤተሰቦቿ ጋር ኢትዮጵያን ልትጎበኝ ነው

By Admin

June 11, 2017

የሆሊውድ ኮከቧ አንጀሊና ጆሊ ከ12 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ በማደጎ የወሰደቻትን ዘሃራ ጆሊ ፒትና ሌሎች ልጆቿን በመያዝ ኢትዮጵያን ልትጎበኝ መሆኑን ሆሊውድላይፍ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

አንጀሊና ጆሊና ከቀድሞ ባለቤቷ ከብራድ ፒት ጋር ሰኔ 29 ቀን 1997 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በመምጣት፣ የዘሃራ እናትና አባትነትን ሲያገኙ ዘሃራ የስድስት ወር ጨቅላ ነበረች፡፡

አንጀሊና የዘሃራ እናት የሆነችበትን ቀን ለማክበርና ለዘሃራም አገሯን ለማስተዋወቅ የምትመጣ ሲሆን፣ አባቷ ብራድ ፒት ግን የማይመጣ መሆኑን ሰለብሪቲ ኢንሳይደር ጽፏል፡፡

የትዳራቸውን ውዝግብ ተከትሎ በአንጀሊና በኩል የጉዞ ጥሪ ያልተደረገለት ብራድ ፒት፣ በዘሃራ ዕድሜ ሙሉ ዘሃራን አባት ሆኖ ማሳደጉ ተገልጿል፡፡

የአንጀሊናና የብራድ ልጆች ከሆኑት ዘሃራና ሺሎህ አባታቸው አብሯቸው ቢጓዝ ደስተኛ እንደሚሆኑ መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡

አንጀሊና ከሦስት አገሮች በመውሰድ የምታሳድጋቸውን ሦስት ልጆቿ አገራቸውን እንዲያውቁ የማድረግ ልምድ ያላት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም የ15 ዓመት ልጇን ማዶክሰን ካምቦዲያ ወስዳ አገሩን አስጎብኝታዋለች፡፡

ዘሃራን ይዛ የምትመጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ዘሃራን አገሯን  ባለማስጎብኘቷ ተወቅሳ ነበር፡፡ አንጀሊና በማደጎ ልጇን ዘሃራን ያገኘችበትን ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማክበር ቀድማ ኢትዮጵያ የምትመጣ መሆኑ ተነግሯል፡፡

አንጀሊናና ብራድፒት ሦስት የአብራክ ክፋይ ልጆች ያላቸው ሲሆን ሁለቱ መንታዎች ናቸው፡፡ ከካምቦዲያ፣ ከኢትዮጵያና ከቬትናም የወሰዷቸው ሦስት የማደጎ ልጆችም አሏቸው፡፡reporter