Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በውይይት ይጎለብታል!

0 1,216

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በውይይት ይጎለብታል!

                              ታዬ ከበደ

17 የሚሆኑ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተወያዩና እየተደራደሩ ነው። ሰሞኑን በተወያዩት ለ13ኛ ዙር የመደራደሪያ አጀንዳዎችንም መርጠዋል። ይህን መሰሉ ውይይትና ድርድር የአገርን ሁለንተናዊ ለውጥ ከማሳደግ አኳያ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በጠረዼዛ ዙሪያ መወያየትና መከራከር ባህሪያዊ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበትና የአገርን ዕድገት በአገር ልጅ ለማሳለጥ ጠቀሜታ አለው።

በውይይቱ ላይ በድርድር አጀንዳነት ከተቀመጡት ውስጥ የምርጫ ህጎች እና ተያያዥ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። በዚህ አጀንዳ ስርም የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ፣  የ1999 ዓ.ም የምርጫ ህግ፣ የ2002 ዓ.ም የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተካትተዋል።

አዋጆችና ተያያዥ ህጎች የሚለው ዓብይ የድርድር አጀንዳም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር እንዲካሄድበት ፀድቋል። ታዲያ በዚህ አጀንዳ ስር በንዑስ አጀንዳነት የፀረ ሽር ህግ፣  የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት ህግ፣ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ፣ የታክስ አዋጅ፣ የመሬት ሊዝ አዋጅና የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታ ተይዘዋል።

ከእነዚህ አጀንዳዎች በተጨማሪም  የዴሞክራሲና ሰብዓዊ ተቋማት አደረጃጃት፣ ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብት ከክልል መንግስታት ህጎች አንጻር፣ ወቅታዊና ኢኮኖሚ ወለድ የህዝብ ጥያቄዎች፣ ብሄራዊ መግባባት፣ የፍትህ ተቋማት አደረጃጀት እና አፈጻጸም አዋጆችም በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የፀደቁ አጀንዳዎች ናቸው።

እነዚህ አጀንዳዎች በጋራ ስምምነት የተደረገባቸው ሲሆኑ፤ በተቃዋሚዎች ቀርበው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ውድቅ ያደረጋቸው የህገ መንግስት ማሻሻያ በሚለው ስር በተለይም በአንቀፅ 39፣ በአንቀፅ 46 እና በአንቀፅ 72 እንደማይደራደር አስታውቋል። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በመሬት ስሪት ፖሊሲውና በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የድንበር ወሰን እንዲሁም የህግ እንጂ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የሉም በማለት ለመደራደር እንደማይፈልግ አቋሙን ግልፅ አድርጓል። ይህ የፓርቲዎቹ ውይይትና ድርድር የኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያለበትን ቁመናን አመላካች ይመስለኛል። የሀገራችን አዲስ ምዕራፍ አመላካችም ነው።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝቦች መብታቸውን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩባት፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያልታየበት፣ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ ያልታሰበባት ሀገር፤ ዛሬ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘርግታ ይህን የመሰለ የውይይት መድረክ ማየቷ ማንኛውንም ዜጋ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው ምርጫ ነው። የምርጫ ጠቀሜታም ህዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ፣ በተጨባጭ በምረጡኝ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፖርቲዎች ያከናወኑትን ወይም የሚያከናውኑትን ተግባር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የእገሌ ፖርቲ በቀጣይ ለውጥ ያመጣልናል ብለው ያመኑበት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላንዳች ተፅዕኖ ካርዳቸውን በመስጠት ተመራጩን ፓርቲ ለስልጣን ማብቃት ነው፡፡ ይህም በህገ መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በሌላ መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ያስረዳናል።

ታዲያ በዚህ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ባለፋት ጊዜያት የተከናወኑ አምስት ሀገራዊና በርካታ ክልላዊ እንዲሁም የአካባቢና የአዲስ አበባ የምክር ቤቶች የሟሟያ ምርጫዎች የላቀ ሚና ተጫውተዋል። በእነዚህ የምርጫ ሂደቶች የሕዝቡ ተሳትፎና ዴሞክራሲውን ወደፊት ለማራመድ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንዘነጋውም። የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ረገድም የተካሄዱት ምርጫዎች የላቀ ሚና ነበራቸው።

የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቢሆኑ በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ግና እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ገና 26 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ለጋ መሆኑን ነው። ያም ሆኖ ምንም እንኳን የተሟላ ባይሆንም፤ ገዥውም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድ የተቻላቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል። ሰሞኑን በምርጫና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች እያካሄዱት ያሉት ድርድርና ውይይት የዚህ ጥረታቸው አካል ነው ማለት ይቻላል። ይህም ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባለፋት ዓመታት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በሂደት እየገነባች መጥታ፣ ድህነትን ለማሸነፍ ባደረገችው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት አግኝታለች። ሆኖም ሁሌም ልዩነታችን አንድነታችን ሆኖ ሳይቀጥል ቀርቶ በመነቋቆርና በመነካከስ እንዲሁም የሌሎች አጀንዳ አስፈፃሚዎች ከሆንን እንደዚህ ቀደሙ ለዘመናት ወደ መጣንበት የድህነት አረንቋላ መመለሳችን የሚቀር አይመስለኝም። ይህ እንዳይሆን ሁሉም ፓርቲዎች ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለአተገባበሩ መትጋት ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል። ተቃዋሚዎችም ይህን ተስፋ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳይከታቸው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል።

እናም ከተቃዋሚዎቹ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች መነሻቸውና መድረሻቸው በግልፅ ተለይተው ሊገለፁና የጋራ ድምዳሜ ሊያዝባቸው ይገባል። ይህ ሲሆንም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ይበልጥ በመግለፅ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል። አሊያ ግን በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የምንሰማቸው እንደ ‘ስልጣን እንጋራ’ ዓይነት የተሳሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመፍጠር በአጠቃላይ ህዝቡ ውስጥ የማይገባ ምስል ሊያሲዙ ይችላሉ። በመሆኑም ለእኔ ከዚህ አኳያ ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ተገቢ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀቱን ለመጨመር በተያዘው ቁርጠኝነት ላይ አንድ ርምጃ መሄድ ጭምርም ነው።

በአንፃሩም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር፤ ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ።

ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል። በፓርላማ ደረጃ የሚኖረው የአሳታፊነት ዴሞክራሲም መንፈስና ተግባርም ይጎለብታል። መድብለ ፓርቲ ስርዓቱም ያድጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy