Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሚሰራ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር ተችሏል

0 416

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሚሰራ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር ተችሏል

አባ መላኩ

የዛሬው  ሰላም   የአስርት ሺዎች  ህይወትንና የአካል መሰዋትነት ተከፍሎበታል። በርካቶች ለህዝባዊ ዓላማ  ስኬት መስዋዕትነት ከፍለዋል።  እነዛ እውነተኛ  የህዝብ ልጆች ትግል ውጤታማ ሆኖ በአገራችን በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሰረት ያደረገ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መገንባት በመቻሉ ዘላቂ ሰላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ጭምር ማስፈን ተችሏል። ሰሞኑን የሰማዕታት ዕለትን ዘክረናል። የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነት መሆን ያለበት ሰማዕቶቻችንን ማሰብ ብቻ ሳይሆን የእነዛ የህዝብ ልጆች ዓላማ ስኬት የሆነውን የአገራችንን ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት  መጠበቅ መሆን  መቻል አለበት።     

 

ውድ ህይወታቸውንና  አካላቸውን  መስዋዕት  ላደረጉ  ለእነዚያ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ምስጋና ይግባቸውና  ዛሬ  አገራችን  ዘላቂ ሰላምና  ፈጣን ልማት ባለቤት ለመሆን ችላለች። የእነዚያን የህዝብ ልጆች ዓላማ በማስቀጠል አገራችንን ከዋንኛ ጠላቷ  ማላቀቅ ይኖርብናል። ደርግ ነብሰጡሮችን፣ ህጻናትን፣ አዛውንትን፣ ሴቶችን በጠራራ ጸሃይ በቦንብ ደብድቧል። ደርግ በራሱ ዜጎች ላይ ከፋሽስት ያልተናነሰ  በደል ፈጽሟል።  ያ ትውልድ ይህን ግፈኛና ሰው በላ መንግስት በትግላቸው በማስወገድ በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ መንግስት መስርተዋል። የአሁኑ ትውልድ  እንደቀድሞው ትውልድ  የህይወትና የአካል መስዋዕትነት መክፈል ሳይጠበቅበት የአገርና የህዝብ አጋርነቱን ማሳየት ይችላል።  አሁን ላይ  የአገራችን ትልቅ ጠላት የሆነውን  “ድህነት” ነው። የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን የሚያስከፍለው የነጻነት ትግልን በድል ተደምድሟል። ዛሬ የጭቆና ምዕራፍ ተወግዶ በዕኩልነትና ነጻነት የምንኖርባት አዲሲቷ  ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ሆናለች።

 

ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  እኩልነታቸው ህገመንግስታዊ እውቅና አገኝቷል።   ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ነጻነት ለማግኘት እንደተከፈለው የ17 ዓመታት መራራ ትግል የድህነት ትግል የህይወት መሰዋትነትም ሆነ የአካል መጉደልን አይጠይቅም። አሁን ያለው የድህነት የትግል መንገድ መራብ መጠማትን፣ ተራራ መውጣትና ቁልቁለት መውረድን፣  በቦንብ  መደብደብን፣ በጥይት መቆላትን  በአጠቃላይ ስቃይና መከራን የሚጠይቅ ሳይሆን ማንም በተሰማራበት የስራ መስክ ህዝብን በቅንነትና ታማኝነት ማገልገል ብቻ ነው። እነዛ የህዝብ ልጆች የሞት፣ የመከራና የስቃይ  ጊዜውን ተወጥተውልናል።  አገሪቱ የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ፈጣን ልማት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የዛሬው ትውልድ  በተሰማራንበት የስራ መስክ  በታማኝነት  ማገልገል  ይጠበቅበታል።

 

ታላቁ መሪ  መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር።  “ደርግን በጋራ ታግለን ጥለነዋል።  አሁንም የድህነት ተራራንም በጋራ መታገል ይኖርብናል።”  የአገራችን ቀንደኛ ጠላት  የሆነውን ድህነት ማስወገድ  የሚቻለው ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ ሲችል ብቻ ነው። ድህነት ቀንደኛ የአገራችን ጠላት ነው። ድህነት አሁን በአገራችን ለምንመለከታቸው በርካታ ችግሮች ዓይነተኛ ምክንያት ነው። ድህነትን ማሸነፍ ከቻልን ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ አገኘን ማለት ነው።  ድህነትን በመዋጋት ረገድ ሁላችንም ራሳችንን ማየትና  የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ማመዛዘን ተገቢ ይመስለኛል።  ለድህነታችን መንስኤዎቹም ሆነ መፍትሄ አምጪዎቹ እኛው ራሳችን መሆን እንደሚገባን መገንዘብ ተገቢ ነው። አገሬን እወዳለሁ በወሬ ሳይሆን በተግባር ማስመስከር ይገባል።  ድህነትን መዋጋት በተመለከተ  ለታላቁ  መሪያችን መለስ ዜናዊ ምስጋና ይግባቸውና  የአገራችን ችግሮች ሁሉ ምንጭ ድህነት መሆኑን አመላክተውናል፤ ከዚህ ችግር  የመውጫ መንገዱንም አሲዘውናል። የጀመርነውን  መንገድ አጥብቀን መያዝ ከቻልን በአጭር ጊዜ ከድህነት መውጣት እንደምንችል በተግበር አረጋግጠናል።

 

ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የድህነት መውጪያው መንገድን ፈንጥቀውልናል።  አገራችን ባለፉት 14 ተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነች።  አገራችን ትላንት ትታወቅበት የነበረው መጥፎ ገጽታ ዛሬ  በመለወጥ ላይ ነው። የአገራችን ገጽታ እጅጉን ተሻሽሏል። ዛሬ ላይ አገራችን አስተማማኝ ሰላም አለ። በረሃብ የሚሞት አንድም ዜጋ የለም። ስራ የማማረጥ አባዜና  የክፍያ  ማነስ  ካልሆነ በስተቀር ስራ አለ። ማንም መስራት የሚችልና የሚፈልግ ዜጋ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር ተችሏል። ይህ በአትኩሮት ለተመለከተው ትልቅ ጥንካሬ ነው።

 

መንግስት ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ  የምስራቁ ዓለም ከታይዋነና ደቡብ ኮሪያ ልምድ በመቅሰም ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመቀመር የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን በመተግበር ላይ ይገኛል። መንግስት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ በአገራችን ዘላቂ ሰላም ማረጋገገጥ በመቻሉ የበርካታ የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ  መግዛት ችሏል። መንግስት ቀደምት የልማታዊ መንግስት  አካሄድን ይከተሉ ከነበሩ  ከምስራቅ ኤዥያ አገራት ከታይዋንንና ደቡብ ኮሪያን መልካም መልካም ልምዶች በመቅሰምና  ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በመደረጉ አገራችን ባለፉተ አስራ ሁለት አመታት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለምንም የተፈጥሮ ሃብት ማስመዝገብ ችሏል።

ኢትዮጵያ መንግስት ልማትን ለማስመዝገብ ብሎ እንደታይዋንና ኮሪያ የህዝቦችን መብት አልደፈጠጠም። የታይዋንና ኮሪያ ነባራዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ፍጹም የተለያዩ ናቸው። የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የእኩልነት ጥያቄ እጅግ አንገብጋቢ ዋንኛ የህዝብ ጥያቄዎች በመሆናቸው እነዘህን ጥያቄዎች ልደፍጥጥ ማለት የሚያስከትለውን አደጋ ሌላ ቀውስ የሚያስከትል ነው። ለዚህ ነው የፈጣን የኢኮኖሚ ልማት መንገድን ከታይዋንና ከደቡብ ኮርያ እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓቱን ደግሞ አገር በቀል ማድረግ ያስፈለገው። ይህ በመሆኑም በሁሉም መስክ አገራችን ስኬታማ መሆን ችላለች።   ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በኢትዮጵያ ሊተገበር አይቻልም። ለመተግበር መሞከርም ትርፉ ጦርነትና እልቂት እንደሚሆን ካለፈው ስርዓት ጥሩ ትምህርት ተቀስሟል። በመሆኑም ከታይዋንና ከደቡብ ኮሪያ የሚበጀንን ልምድ በመቅሰም ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣማችን አገራችን ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ዓለምን ያስደመመ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የድርቅና ረሃብ ተምሳሌት ተደርጋ ትጠቀስ የነበረች አገር ዛሬ ላይ ባለ ብዙ ቢሊዬን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሳይቀር በራስ አቅም የመገንባት አቅም መፍጠር የቻለች በለተስፋ አገር መሆን ችላለች። ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በተባበሩት መንግስታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረከኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን አገራችን ማስመዝገብ በቻለችው የኤኮኖሚ እድገትና በመሰረተችው ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሳቢያ  የተገኘ መሆኑን ማመን ተገቢ ይመስለኛል።

 

የተጀመረውን የዕኩልነትና የዴሞክራሲ ስርዓት ማስቀጠል የሁሉም ሃላፊነት መሆን ይገባዋል። የዛሬው  ሰላም የአስርት ሺዎች  ህይወትንና የአካል መሰዋትነት ተከፍሎበታል።  ያ ትግል ውጤታማ ሆኖ በአገራችን በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሰረት ያደረገ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መገንባት  ተችሏል።  በአገራችን ዴሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት በመቻሉ ዘላቂ ሰላም  በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው  ጭምር ማስፈን ተችሏል።  የሰማዕታት ዕለትን ስናከብር  የእነዛ እውነተኛ  የህዝብ ልጆች ዓላማ ስኬት የሆነውን የአገራችንን የዴሞክራሲና የልማት  ስርዓት   በመጠበቅና በመንከባከብ  መሆን አለበት።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy