Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሳዑዲ ዓረቢያ የውጡልኝ አዋጅ እና ስደት

0 452

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሳዑዲ አረቢያ የወጣውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ 500ሺ ኢትዮጵያዊ ተመላሾች ይኖራሉ ተብሎ ተጠብቋል፡፡ ሆኖም ከተሰጠው ሦስት ወር የጊዜ ገደብ ውስጥ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ቢቀርም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሰዎች ከ30 ሺ በታች ናቸው፡፡ ወደ አገራቸው ለመግባት የተመዘገቡትም ቢሆኑ ከ80 ሺ አይበልጡም›› የሚሉት በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ አስተባባሪ አቶ አስመላሽ ገብረህይወት ናቸው፡፡

ሰሞኑን ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ስደትን አስመልክቶ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ አቶ አስመላሽ እንደተናገሩት፤ ሳዑዲ ዓረቢያ ሉአላዊት አገር ናት፡፡ ህገወጥ የውጭ አገር ዜጎችን ከአገሯ ማባረሯና ማሰሯ መብቷ ነው፡፡ ለምን አወጀች ማለት አይቻልም፡፡ የሚያስፈልገው ፈጣን ምለሽ መስጠት ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ዝም ብሎ እያየ አይደለም፡፡ አሁንም ጊዜውን አራዝሙልን የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡትን በአውሮፕላን ለማመላለስ አስቸጋሪ በመሆኑ በመርከብ ወደ አገራቸው ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራም ምንም እንኳ ወደ ሳዑዲ ሲሄድ ተሳፋሪ ባይኖርም በቀን ስምንት ጊዜ እንዲመላለስ ማድረግ ተችሏል፡፡ ሳዑዲዎችም መንግሥት ላቀረበላቸው የጊዜውን አራዝሙልን ጥያቄ መልሳቸው «እናስብበታለን» የሚል ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

መንግሥታቸው በአዋጁ የምህረት ጊዜው ካለፈ ንብረት እወርሳለሁ፤ እንደፈለግኩ አስራለሁ ማለት 16ሺ እስረኞችን የሚይዙ 90 አዳዲስ እስር ቤቶችን አዘጋጅተዋል፡፡ ለሁለት ዓመት የሰለጠኑ ልዩ ኃይሎችንም እናሰማራለን ብለዋል፡፡ ስለዚህ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን ችላ ማለት የለባቸውም፡፡ እዚህ ያለው ቤተሰብም በስልክም ሆነ በማንኛውም መንገድ ለቤተሰቡ ጥሪ ማቅረብ አለበት በማለት ነው አቶ አስመላሽ ያሳሰቡት፡፡

የሌሎቹ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አገር ዜጎች የሥራ ፍቃድ የሌላቸው በሙሉ ሙልጭ ብለው ወጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ግን አልወጡም፡፡አሁን የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ተደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የአዋጁን አሳሳቢነት በመረዳት የሊሴ ፓሴ ምዝገባ እያደረገ ነው፡፡ አቅም ያላቸው ቀድመው ወደ አገራቸው ቢገቡም የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከስደት ጋር ተያይዞ የሚሰሩ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስብሰባው የተሳተፉ ሲሆን፤ የመንግሥትን ተጨማሪ ጥረት አስመልክቶ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አቶ አስመላሽም ረጅም ጊዜ በሳዑዲ የቆዩ ክልስ ልጆችን አስመልክቶ ሳዑዲዎች የዘረመል ምርመራን አካሂደን ወደ አገራቸው እንልካለን ቢሉም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን በመነጋገር መፍትሄ የሚያበጅበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ አቶ ይበልጣል ዋለልኝ በኢትዮጵያ ሰዎች ስደትን የሚመርጡት በሥራ አጥነትና በኢኮኖሚው ችግር ሳቢያ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢነገርም አንዳንድ ጊዜ እንደ ባህል የሚታይበት ሁኔታ ይስተዋላል፤ በማለት በደቡብ አካባቢ ባህል እስኪመስል ድረስ ስደት መስፋፋቱን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡

ጉዳዩን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አውቆት በህጋዊ መንገድ ከሚወጣው ይልቅ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው ይበዛል፡፡በዚህም በርካታዎች ለጉዳት ተጋልጠዋል፡፡ህገወጥ ሆነው መጓዛቸው ደግሞ እንደ ሳዑዲ ያሉ አገሮች እንዲወጡ የሚያስገድዱበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ሰዎች አገራዊ ጥቅምንና ደህንነትን ለማስከበር ሲባል እንዳይወጡ የሚከለከልበት ሁኔታ ቢኖርም፤ ከዚህ ውጪ ከአገር የመውጣት መብት አላቸው፡፡ ስለዚህ ስደትን ማስቆምም ሆነ መከልከል አይቻልም፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ማስተዳደሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሳዑዲ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞችን በሚመለከትም ‹‹አንዳንዶች በፊት የሳዑዲ መንግሥት ውጡልኝ ብሎ ባልወጡት ላይ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ተዘናግተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በቅርቡ የሄዱና ምንም ገንዘብ የሌላቸው፤ ምናልባትም በብድር ገንዘብ ከፍለው የሄዱት ገንዘቡን ለመክፈል ወይም ቤተሰብ ለመርዳት ያልቻሉት ‹ምን እባላለሁ› በሚል የስነልቦና ጫና ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፈቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል›› በማለት ምንም እንኳ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ሁሉንም ማድረግ የሚቻለው ህይወት ሲኖርና ተንቀሳቅሶ መስራት ሲቻል በመሆኑ ወደ አገራቸው መግባትን በአንደኛ አማራጭነት መጠቀም እንዳለባቸውም ነው አቶ ይበልጣል ያሳሰቡት፡፡

ሰዎች ጥቂት ገንዘብ ለማግኘት ብለው 10 ዓመታት እስር ቤት የመታጎርን ክስረት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን የለባቸውም፡፡ ምናልባትም ያለምንም የህግ ጥበቃ የሚታሰሩ በመሆኑ መደፈርና ትልልቅ ሰብዓዊ ጥሰቶች ሊፈፀምባቸው ስለሚችል ከወዲሁ አስበው ባገኙት አማራጭ ወደ አገር መግባት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ተክሌ ተስፋ በበኩላቸው፤ መንግሥት በተቻለ አቅም አዋጁን ተከትሎ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዜጎቹን ለማስወጣት ጥረት አድርጓል፡፡ ክፍተቱ እዛው ያሉ ኢትዮጵያውያን ለመውጣት የነበራቸው ዝግጁነት ላይ ነው ይላሉ፡፡ በአገር ውስጥም ስደትን አስመልክቶ የሚሰራው ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መሆኑን ገልፀው፤ አዋጅ ከማፅደቅ ባሻገር ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ህገወጥ ስደት የሚቀንስበት ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ተወያዮቹ እንደገለፀት፤ ስደት በየትኛውም ዓለም ያለ በመሆኑ እንደመጥፎ ጉዳይ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ በአግባቡ ማስተዳደር ከተቻለ ጠቃሚ መሆኑ አይካድም፡፡ ህገወጥነቱን ለመከላከል በህጋዊነት የመሄድ ዕድሉን ማስፋትና የድንበር ጥበቃን ማጠናከር እንዲሁም ስደትን ብቻ የሚመለከትና ኃላፊነቱን የሚወስድ ተቋም ማቋቋም፤ ከወረዳ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና እስከ አገራቱ ኤምባሲዎች ድረስ ግንኙነቱን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምህረት ሞገስ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy