Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ“ሳይቃጠል በቅጠል” ተምሳሌት

0 274

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ“ሳይቃጠል በቅጠል” ተምሳሌት

                                                      ዘአማን በላይ

ሰሞኑን ተጎራባች በሆኑት የጋምቤላና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት መካከል ቀደም ሲል ያልተካለሉ የድንበር አካባቢዎችን ለማካለል መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል። የሁለቱ ክልላዊ መንግስታት ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የክልሎቹ ድንበር ተጋሪ ነዋሪዎች ከፌዴራልና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሰጡት መግለጫ ይህን የሚያመለክት ነው። ታዲያ ምናልባትም በተፈጥሮ ሃብት እጥረት (Natural Resource Scarcity) ምክንያት ሊፈጠር የሚችል ግጭትን ከወዲሁ እልባት ለመስጠት ሁለቱ ክልሎችና የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዩች በቁርጠኝነት መንቀሳቀሳቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። ይህን መሰሉ ስጋትን ለመከላከል አስቀድሞ የሚሰራ ተግባር “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ በቀጣይ ሊፈጠሩ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ግጭቶች እንዳይከሰቱ በእንጭጩ የሚያስቀር ነው።

ርግጥ የተፈጥሮ ሃብት እጥረት እስካለ ድረስ ግጭቶች በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች መከሰታቸው አይቀርም። ትናንትም ነበሩ፣ ዛሬም አሉ፣ ነገና ከነገ ወዲያም ቢሆን ይኖራሉ። በአንድ አካባቢ የሚገኝ የተፈጥሮ ሃብት በሌላኛው ውስጥ ላይኖር ይችላል። እናም ምናልባትም ያ የተፈጥሮ ሃብት ‘በይገባኛል’ ስሜት የግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል።

ዳሩ ግን ድንበር ከተካለለና አንደኛው በተፈጥሮ ሃብቱ ማግኘት የሚገባው ጥቅም ተሰጥቶት በጋራ መጠቀም ከተቻለ ግጭት ሊኖር የሚችልበት ምንም ዓይነት አመክንዮ የሚኖር አይመስለኝም። በቅድሚያ ግን የትኛው ቦታ የማን እንደሆነ በግልፅ መታወቅ ይኖርበታል። ለዚህም ይመስለኛል— የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዩች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን በተገኙበት ሁለቱ ክልሎችና የሚጎራበቱት ህዝቦች በጋራ በመሆን ያልተካለሉ አካባቢዎችን ለማካለል መስማማታቸው። እናም ለእኔ ይህ ሁሉንም የጉዳዩን ተዋንያን ያሳተፈ አስቀድሞ የመከላከል ስራ የ“ሳይቃጠል በቅጠል” ሁነኛ ተምሳሌት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

እንደ እውነቱ ከሆነ በተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ የትም ቦታ ግጭት ሊኖር ይችላል። ስጋና ደም ለብሶ ህይወቱን ለመግፋት በምድር ላይ ደፋ ቀና የሚለውና ፍላጎቱ ገደብ የሌለው የሰው ልጅ ቀርቶ፤ ለሰው ልጅ መገልገያነት በቁስነት የፈጠሩት ግዑዛን ነገሮች እንኳን በተፈጥሮአዊ ሂደት ሳቢያ ይጋጫሉ። የሰው ልጅ በምድር ላይ እስካለ ድረስ በቅድሚያ ከራሱ ጋር፣ ለጥቆም በዙሪያው ካሉት ነገሮች እንዲሁም ከአካባቢውና ከተፈጥሮ ጋር ሊጋጭ ይችላል። ይህ ነባራዊ ዕውነታ ነው። አንዱ ስለፈለገው የሚሆን፣ ሌላው ደግሞ ስላልፈለገው የሚቀር ጉዳይ አይደለም— ክስተቱ ነባራዊ የተፈጥሮ ግዴታ ነውና። ዓለማችን ላይ የምናያቸው የተለያዩ ግጭቶች መነሻቸው ምንም ይሁን ምን፤ በአንድም ይሁን በሌላ መልካቸው ይህ እውነታ ይፈፀም ዘንድ ገቢራዊ የሚሆኑ ይመስለኛል።

ታዲያ የግጭቶች መኖር ነባራዊ የተፈጥሮ ክስተት መሆኑን ከተረዳን ዘንዳ፤ ዋናው ቁም ነገር ግጭቶቹን ለመፍታት የሚሄድበት መንገድና የአፈታት ስርዓቱ ሁኔታ ነው። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነባ ያለው ስርዓት ራሱን በራሱ የሚያርምና የተዛቡ ቀደምት ግንኙነቶችን በማረቅ ለህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት የቆመ ነው። አዎ! ላለፉት 26 ዓመታት እዚህ ሀገር ውስጥ የተከናወነው ወደፊትም የሚከናወን ትግል አለ—ቀና ብለን እንዳንራመድ ባደረገን ድህነት ላይ።

ታዲያ ይህ ትግል ያለ አንዳች ሳንካ የተከናወነና በመከናወን ላይ ያለ አይደለም። ውጣ ውረዶችና አባጣ ጎባጣዎች የታለፈበትና የሚታለፍበት ነው። በትግል ሂደቱ ላይ የታዩት ችግሮች አነስተኛ ቢሆኑም መፈጠራቸው ግን የግድ ነበር። ስራውን የሚያከናውነው በሂደት ከተሞክሮው እየተማረ የሚያሻሽለው የሰው ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፤ ወደፊትም ችግሮች አይፈጠሩም ብሎ መናገር አይቻልም። በየትኛውም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ፍፁምነት ይኖራል ተብሎ አይታሰብምና።

ያም ሆኖ ፌዴራላዊ ስርዓቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ አማካኝነት በፀረ-ድህነት ትግሉ የተፈጠሩ ችግሮች እየተፈቱ አሁን ለምንገኝበት የሁለንተናዊ ለውጥ ቁመና ስርዓቱ ራሱ ምክንያት መሆኑን መዘንጋት የሚገባ አይመስለኝም። ይህም ፌዴራላዊ ስርዓቱ ችግሮች ሲፈጠሩ ከህዝቡ ጋር በመሆን ራሱን በራሱ ማረምና ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሸጋገር ሁነኛ መገለጫው መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።  

ለነገሩ የዛሬ ችግሮች መነሻቸው ትላንት ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ባለፉት ስርዓቶች የህዝብን ጥቅም ያላማከሉና የገዥ መደቦችን ፍላጎት ብቻ ለማስፈፀም የተከናወኑ አያሌ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባሮች ነበሩ። እነዚህ ተግባሮች ከስርዓቶቹ ሲንከባበሉ መጥተው ዛሬም ድረስ የችግር መገለጫ እየሆኑ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የሚፃረሩትና እንደ ትምክህተኝነትና ጠባብነት የመሳሰሉ ጉዳዩች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። ስርዓቶቹ ስልጣናቸውን ለማደላደል ሲሉ የፈጠሯቸው የማህበራዊ ግንኙነት ቀውሶችም ቀላል አይደሉም። ለዚህም ነው—የሀገራችን ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ስርዓት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እምነትና ፈቃድ የዛሬ 22 ዓመት ገደማ ሲመሰረት አንዱ መሰረታዊ አስተሳሰብ ያለፉት ስርዓቶች የፈጠሯቸውን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶች ማስተካከል እንዲሆን የተደረገው።

የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማስተካከል ሂደትም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዜጎች ቋንቋቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸውና የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው እኩል እድል መፍጠር ተችሏል። ዛሬ ጋምቤላው፣ ቤኒሻንጉሉ፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው፣ የኢትዮጵያ ሶማሌው…ወዘተ. በእኩልነት የሚነጋገሩበትና ችግራቸውን በጋራ የሚፈቱበት መድረክ ተፈጥሯል። ያለፉት ስርዓቶች በሕዝቦች መካከል የፈጠሩት ጥርጣሬና መራራቅን በማስወገድ ኢትዮጵያ ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገዱባት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቤተሰብ እንድትሆን በዓይነቱ የተለየ ግንኙነት እንዲፈጠርም ማድረግ ተችሏል። በዚህም ሳቢያ ስርዓቱ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ቦታ እንዳይኖረው አድርጓል።   

ፌዴራላዊ ስርዓቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በክልላቸውና በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነት እንዲኖራቸው በማድረግ በኢትዮጵያ ዕድገትና ስልጣኔ ላይ እንዲረባረቡ የሚያደርጋቸው እንጂ በድንበር መካለል ሰበብ ወደ ግጭት እንዲያመሩ የሚያደርጋቸው አይደለም። ስርዓቱ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የጋራ ማህበረሰብ በመፍጠር አዲስ የግንኙነት ምዕራፍን ከፍቶ ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ አቅምና ጠንካራ ጉልበት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንጂ ለግጭት የሚሆን አንድም ስንዝር ምህዳር የለውም።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእለት ተእለት አኗኗራቸውንና የወደፊት ህይወታቸውን በሚወስኑ አጀንዳዎች ላይ የሚወስንላቸው ከላይ የሚጫን ኃይል እንዳይኖር እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ከአጎራባቾቻቸው ጋር የሚያደርጉት ሁለንተናዊ መስተጋብሮች እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ ለማደግ የሚያስችል ሁኔታን የፈጠረ ነው። በህገ መንግስቱ ላይ አንድ የጋራ ፖሊቲካል ኢኮኖሚን እንገነባለን ብለው በቃል ኪዳን ያሰፈሩት የሀገራችን ህዘቦች በምንም ዓይነት ቀመር ሊጋጩ አይችሉም። ምንም እንኳን በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ከተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ በግጦሽ መሬት፣ በውሃና በመሰል ጉዳዩች ሊጋጩ ቢችሉም፤ ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የስርዓቱን ህጋዊ አሰራሮች መከተል ይገባል።

አዎ! ፌዴራላዊ ስርዓቱ ችግሮችን የሚፈታበት የራሱ አሰራሮች በመኖራቸው ሁሌም ቢሆን ወደ ግጭት ከማምራት በፊት በስርዓቱ ውስጥ ያሉትን አሰራሮች መከተል ያስፈልጋል። ግጭት የየትኛውም ዓይነት ችግር መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል፤ በጋምቤላና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት መካከል ከመሰንበቻው ድንበርን ለማካለል የተደረሰው ስምምነት የስርዓቱን ለግጭት ቦታ የማይሰጥ መንገድ መከተል በመሆኑ “ይበል” የሚያሰኝ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የ“ሳይቃጠል በቅጠል” ተምሳሌታዊ ተግባራት ወደፊትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።  

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy