Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሽብርተኝነት ታናሽ ወንድም

0 522

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሽብርተኝነት ታናሽ ወንድም

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

ዓለማችን አክራሪነት በወለደው የሽብርተኝነት አደጋ እየተናጠች ነው። የዓለም መሪዎች ከድርጊቱ ተለዋዋጭ ባህሪ አኳያ ይህን ጅምላ ጨራሽ አደጋ መቋቋም የቻሉ አይመስልም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሽብርተኝነት ሰይፍ ፊቱን ወደ አውሮፓ ልሳነ-ምድር ያዞረ ይመስላል። ቀደም ሲል የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ላይ በድርጊቱ የደረሰው ዘግናኝ አደጋ እንዲሁም ከመሰንበቻው የታላቋ ብሪታንያ (እንግሊዝ) መዲና የሆነችው ለንደን ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቴ በሽብር ጥቃት መመታቷ ይህን ሃቅ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።

ታዲያ ፓሪስም ትሁን ለንደን በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ በርካታ ንፀሃን ዜጎቻቸውን አጥተዋል። በጥቃቶቹ የዜጎቻቸው አካላት ጎድሏል፣ የከተማዎቹም ንብረቶች ወድመዋል። ክስተቶቹ እጅግ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና ሁሉንም የዓለም ህዝብ ያስቆጡ ናቸው። በሰሜንም ይሁን በደቡብ፣ በምስራቅም ይሁን በምዕራብ ክፍለ-አህጉር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦችን አንድ ዓይነት ቋንቋ እንዲናገሩ ያደረጉም ጭምር ናቸው—ሽብርተኝነት የዓለማችን ወቅታዊ ችግር መሆኑን።

ርግጥ ዛሬ የሽብርተኝነት አደጋ በዓለማችን ላይ እንዲህ በስፋት ከመስተዋሉ በፊት፤ ኢትዮጵያ የዚህ ዘግናኝ ድርጊት ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ እንደነበረች የሚዘነጋ አይመስለኝም። አዎ! ከድህነትና ከኋላቀርነት የመውጣት ዓላማን አንግበው ለስኬታማነቱ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ለአስተማማኝ ሰላም፣ ለፈጣንና ተከታታይ ልማት ቀጣይነት እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በመረባረብ ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ሽብርተኝነት በተለያዩ ጊዜያት ተፈታትኗታል።

በሽግግር መንግስቱ ወቅት በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ፣ ራሳቸውን “አል-ኢትሃድ አል ኢስላሚያ” እንዲሁም “የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” እያሉ በሚጠሩ አክራሪ ቡድኖችና በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ሀገሮችና ዓለም እየተዋጋው የሚገኘው “አልሸባብ” የተሰኘው የሽብር ቡድን ከተፈታተኗት ውስጥ ዋነኛዎቹ ናቸው። ግና እነዚህ የሽብር ተግባሮች ሀገራችንን ሊያንበረክኳት አልቻሉም። በእኔ እምነት ምክንያቱ ለተግባሩ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የማይፈጥሩት ህዝባችንና መንግስት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ነው።

ያም ሆኖ ግን ዛሬም ቢሆን የአሸባሪነት ችግር እኛም ሀገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ብሎ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል አይመስለኝም። “ለምን?” ቢሉ፤ በተለያዩ ወቅቶች በፍርድ ቤት እየተከሰሱ የሚቀርቡት ተጠርጣሪ አሸባሪዎች የሚሰጡት የእምነት ክህደት ቃል የሚያሳየው፤ ግለሰቦቹ “አልሸባብ” በተሰኘው የሽብር ቡድን አማካኝነት ሰልጥነው ጥቃት ለማድረስ ሲሉ በህበረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ስለሚገለፁ ነው። በሀገራችን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየሙት ኃይሎችም እንዲሁ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን በማሰማራት ጥቃት ሳያደርሱ በህዝብና በፀጥታ ሃይሎች ትብብር መያዛቸው አሁንም ቢሆን የአደጋውን ሙሉ ለሙሉ መክሰም የሚያሳዩ አይደሉም።

እናም እስካሁን ድረስ ሰላም ወዳዱ የሀገራችን መንግስትና ህዝብ የሽብርተኝነትን አደጋ በጋራ በመከላከል ያስገኙት ውጤት አድናቆትና ከበሬታ የሚቸረው እንዲሁም እንደ ዜጋ ማንንም የሚያኮራ ቢሆንም፤ ይህ ጠንካራ ውጤት ይበልጥ ይጠናከር ዘንድ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ የሚጠይቅ ይመስለኛል።

ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ የአሸባሪነት ታናሽ ወንድም የሆነውን የአክራሪነትን ዝንባሌዎችን መሰረት ማሳጣት የሚገባ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው አክራሪነት በአንድ ሀገር ውስጥ እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ራሱን የሚገልፀው በአሸባሪነት መንገድ ነው። ይህም አክራሪነት በጊዜ ቆይታ ሂደት ውስጥ ሽብርተኝነትን የሚወልድ መሆኑን ያሳያል። አክራሪነት መነሻው በአብዛኛው ሃይማኖት ቢሆንም ግቡ ፖለቲካዊ ነው። የአክራሪነት ዝንባሌና ተግባር ሃይማኖትን ተጠለሎ የመጨረሻው ግቡ ግን ፖለቲካዊ መሆኑን ቀደም ባሉት ጊዜያት በገልፅ የታየ ነው።

በእስልምናው እምነት ውሰጥ የተሸሸጉ አክራሪዎች ሃይማኖቱን በታዛነት ቢጠለሉበትም፤ ተግባራቸው ከሃይማኖቱ ፍላጎት ውጭ የሆነና ፖለቲካን መሰረት ያደረገ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ዓለም አቀፉ “እስላማዊ መንግስት” (IS) እና አል-ቃዒዳ ጥሩ መገለጫዎች ናቸው። ግባቸው ግን ፖለቲካዊ መሆኑን በሶሪያ፣ በኢራቅና በአፍጋኒስታን ከሚያደርጓቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ለመረዳት አይከብድም። በክርስትናው እምነት ውስጥም “መንግስታዊ ሃይማኖትን” የሚናፈቁ አክራሪዎች እየታዩ ነው። የሌላውን እምነት በደፈጠጥ የእነርሱን አምልኮ በሃይል በለሌሎች ላይ የመጫን የሚጭኑ የሐሰት ክርስቲያኖችም እየተፈጠሩ ነው። የሁሉም ማጠንጠኛ ግን ፖለቲካዊ ነው።

የአክራሪነትን ሁኔታ ከእኛ ሀገር አኳያ ስንመለከተው፤ ብቅ ጥልም የሚሉ ጉዳዩች የሉም ማለት አይቻልም። በእኛ ሀገርም አክራሪዎች ተግባራቸው ለእኩይ ዓላማቸው የሚሆን አዲስ ክስተት ከተፈጠረ እርሱን አንጠልጥሎ መሮጥ ነው። የፖለቲካ ቅኝታቸው ሃይማኖትን በመሸሸጊያነት የሚጠቀም ስለሆነ አማኞችን ለማምታታት ይሽቀዳደማሉ። የእሽቅድድማቸው ልኬት የሚለካውም ምን ያህል የሃይማኖቱን ተከታዩች ከመንግስት አሊያም ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ባጋጩት መጠን ይመስላቸዋል።

እስልምናንም ይሁን ክርስትናን የማይወክሉ፣ ግን እምነቶቹን በመሸሸጊያ ዋሻነት የሚጠቀሙ እነዚህ ወገኖች በአክራሪነት ዝማሬ ተነስተው በስተመጨረሻ ላይ “እስላማዊ መንግስት መመስረት” እንዲሁም “አንድ ጥምቀት አንድ ሀገር” ሲሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

አክራሪዎቹ ግባቸው ፖለቲካዊ በመሆኑ በህዝቡ ውስጥ ተቀባይነትን ሲያጡ ጣታቸውን መንግስት ላይ መቀሰራቸው የተለመደ ተግባራቸው ነው። ይህን ዕውነታ ለማሰረዳት አንድ ምሳሌ ላንሳ። የእስልምናው መጅሊስም ይሁን የክርስትናው ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶቹን በሚመርጥበት ወቅት የመንግስት ጣልቃ ገብነት በህገ መንግስቱ የተገደበ መሆኑ እየታወቀ፤ አክራሪዎቹ ህዝበ ሙስሊሙም ይሁን ህዝበ ክርስቲያኑ “ይመሩኛል” ያላቸውን ሃይማኖታዊ መሪዎች ሲመርጥ ተመራጮቹን ‘የመንግስት ካድሬዎች ናቸው፣ ሃይማኖታዊ ዕውቀትና ስብዕናም የላቸውም፣ ለሃይማኖት ክብርና ጥቅም የቆምነው ተሟጋቾች እኛ ነን’ የሚሉ የማደናገሪያ መልእክቶችን ያሰራጫሉ። ይህም የአክራሪነት ተግባር ምን ያህል ከፖለቲካ ፍላጎታቸው ጋር የተቆራኘ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ይሁንና በሀገራችን ውስጥ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው። መንህስታዊ ሃይማኖትም ይሁን ሃይማኖታዊ መንገስት አይኖርም። ይህን ህገ መንግስታዊ ድንበር የትኛውም ወገን ሊያልፍ አይችልም። በአንፃሩም የማንኛውም እምነት ተከታይ ያለማንም አስገዳጅነት በመረጠው ሃይማኖት እንዲመራ፣ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲፈጸም ህገ መንግስቱ ደንግጓል። የየትኛውም እምነት ተከታይ በየትኛውም እምነት ተከታይ ላይ እምነቱን በሃይል ሊጭን አይችልም። ከዚህ ውጭ የሚከናወኑ ድርጊቶች የሃይማኖት አክራሪነት ሲሆኑ፤ እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ የአሸባሪነት ድርጊትን የሚፈጥሩ ናቸው።

እናም በሀገራችን ውስጥ ብቅ ጥልም የሚለውን የአክራሪነት አስተሳሰብና ተግባር ማስወገድ ከተቻለ፤ የአክራሪነት ታላቅ ልጅ ለሆነው አሸባሪነት ምቹ ያልሆነ ምህዳር እንፈጥራለን ብዬ አምናለሁ። ከውጭ የሚመጣውን የአሸባሪነት አደጋን ለመቋቋም እስካሁን በመንግስትና በህዝቡ መካከል እውን እየሆነ ያለው ቅንጅታዊ ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዋናው ጉዳይ በሀገር ውስጥ ያለውን መነሻ ማክሰም ነውና በውስጥ ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ከተቆጣጠርን፤ ዓለምን እያነጋገረ ያለውን የሽብርተኝነት አደጋን በተገቢው ሁኔታ የማናስወግድበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። እናም የሽብርተኝነት ታናሽ ወንድም የሆነውን አክራሪነትን ሀገር ውስጥ ይበልጥ መሰረት እንዳይኖረው ከተደረገ አሸባሪነትን መዋጋት አይከብድም። ይህን ለመከወንም ሁሉም ዜጋ እንደ አንድ ሰው፣ አንድ ዜጋ እንደ ሁሉም በመሆን ከምንጊዜውም በላይ መንቀሳቀስ ይኖርበታል እላለሁ።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy