የተፋሰሱ አገራት ህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት
የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት
ስሜነህ
ከኤስያ “ሜኮንግ” የተባለውን ወንዝ ታይላንድና ላኦስ የሚባሉ ሀገራት በጋራ ይጠቀሙበታል:: ታይላንድ ለኃይል ማመንጫ ግንባታ የሚውለውን ገንዘብ ለመደገፍ፣ ላኦስ ደግሞ ከሚመነጨው ኃይል ለታይላንድ ልታካፍል ስምምነት አደረጉ፤ ግንባታውም ተካሂዶ በጋራ እየተጠቀሙ ነው:: በ1986 እ.ኤ.አ ሌሴቶና ደቡብ አፍሪካም ተስማምተው በጋራ እየተጠቀሙ ነው:: በስምምነቱ ደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ድጋፍ ልታደርግ፣ ሌሴቶ ደግሞ ለመጠጥ አገልግሎትና ለኢንዱስትሪ መንደር ግብዓት የሚሆን ውሃ ልታቀርብ ውል ገብተዋል፤ በዚህም ተጠቃሚም ሆነዋል:: የኡዝቤኪስታንና የካዛኪስታንን የጋራ ተጠቃሚነት ስምምነትንም በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል:: ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሀገራት በትብብር መሥራት ከቻሉ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል ነው:: በተለይ በዚህ ዘመን ጥሩ ሀሳብ የሚሆነው ከውሃው ይልቅ የውሃውን ጥቅም መከፋፈል ነው:: ይህም የውሃውን ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ ሁለትና ከዚያ በላይ ሀገራትን ፍላጎት የበለጠ ያረካል ተብሎ ይታሰባል:: በተለይ የእርስ በእርስ ግንኙነቱ የዳበረና መተማመን ያለበት ከሆነ ውሃውን የበለጠ ለጋራ መጠቀም የሚያስችል አካሄድ ነው:: ስለሆነም የድንበር ተሻጋሪ (ዓለም አቀፍ) ወንዞች ተጠቃሚ ሀገራት ውሃውን ለመካፈል ከመሞከር ይልቅ ከውሃው የሚገኘውን ጥቅም ለመከፋፈል ቢጥሩ መልካም ነው፤ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ሀገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ ነው::
የኢፌዴሪ መንግስት የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት ሲያቅድ ጀምሮ ያራምደው የነበረው መርህ “በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ሊኖር ይገባል” የሚለውን መርህ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አቋም ሁሉም የሚጠቀምበትን መንገድ መከተል እንጂ አንዱ ተጠቅሞ ሌላው የሚጎዳበት አካሄድ ለቀጠናው አገራት ሰላም ማምጣት እንደማያስችል ይረዳሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አካሄድ ተግብራለች።
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!” ብለን ተነስተን ይሄው
ለሴኮንድ እንኳን ሳናቋርጥ እያገባደድነው እንገኛለን:: እንደብረት የጋለው ወኔያችን ሳይቀዘቅዝ ያጋመስነውን ጨርሰን ሌላ ለመጀመርም በግስጋሴ ላይ ነን:: ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ ለጋራ ጉዳያችን በጋራ መቆም እንደምንችል ያሳየንበት ተምሳሌት ሆኗል:: ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ “አይቻልም!” የሚለው የድህነት አጋር በ“ይቻላል!” እንዲተካ ያደረገ የህዳሴ መሰረት ሆኗል::
የህዳሴውን ግድብ ስንጀምር “. . አናፂዎች እኛው!፣ ግንበኞችም እኛው!፣ የሀብት ምንጮችም
እኛው!፣…” ብለን እንደተነሳን ሁሉ ወደ ተግባር ቀይረነዋል:: ለዚህ ስኬት ደግሞ የህዝቡን የልብ ትርታ አዳምጦ፣ ወኔና ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ተረድቶ፣ ከሁሉም በላይ የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ ተገንዝቦ “አባይን መገደብ አሁን ነው!” ብሎ ለተነሳው መንግሥታችን አሁን በደረስንበት ላይ ሆነን ቆመን ልናጨበጭብ ይገባል::
በአባይ ላይ ለሚነሳ “የመጠቀም” ጥያቄ ዛሬ ምላሹ ማስፈራሪያ ሳይሆን “እንደራደር” ሆኗል:: ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት የበሰለ አመራርና ዲፕሎማሲ ውጤት ነውና አድናቆት ሊቸረው ግድ ይላል:: የኢትዮጵያ መንግሥት የአባይ ተፋሰስ ሀገራት አንዱ አንዱን በኃይል በማስፈራራት ለመጠቀም የሚያደርጉትን ኋላቀር አስተሳሰብ እርግፍ አድርጐ ጥሎ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ በማድረጉም ምስጋና ይገባዋል:: ህዝቡን አስተባብሮ በመምራት የኢትዮጵያ ህዝብ በስራው ከድህነት ሊወጣ እንደሚችል በማሳየቱም መንግሥት ሊወደስ ይገባል::
ከምንም በላይ መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተቀብሎ በመተግበር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ ያበቃው የኢትዮጵያ ህዝብም ለሰጠው ፈጣንና የተሟላ ምላሽ ምስጋና ይገባዋል:: ወትሮውንም ቢሆን ንቁና በሳል መሪ እስካገኘ ድረስ በሀገር ለመጣ ማንኛውም ጉዳይ ህይወቱን እስከመገበር የማይሳሳው የኢትዮጵያ ህዝብ ያንን ወርቃማ ልማድ ዛሬም በህዳሴው ግድብ ላይ እየተገበረው ይገኛልና የልማት አርበኛ እየሆነ ላለው ለዚህ ትውልድ ክብርና ምስጋና ቢያንሰው እንጂ፤ አይበዛበትም::
ከሁሉም በላይ ደግሞ በየዓመቱ የወር ደመወዙን መቶ በመቶ ለቦንድ ግዢ እያዋለ የሚገኘው የመንግሥት ሠራተኛ ከወርሃዊ ገቢና ወጪው ንጽጽር አኳያ አስተዋጽኦው ከእለት ጉርስ ላይ እየተቀነሰ የለገሰው በመሆኑ ለኢትዮጵያችን ህዳሴ ያስቀመጠው አሻራ የሚያኮራና መቼውንም የማይዘነጋ ነው:: ከዚሁ ባልተናነሰ በቀን ሥራ የተሰማራውን እና አነስተኛ ገቢ ያለውን ዜጋ ጨምሮ ተማሪው ሳይቀር መላው የሀገራችን አርሶ አደሮች እና የከተማ ነዋሪው ያደረገው ርብርብም አኩርቶናል፤ ሲያኮራንም ይኖራል:: ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ ሰሞንኛ ክንውኖች ጥቂቶቹን ለአብነት እንመልከት።
ከሰሞኑ በዳውሮ ዞን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በቆየባቸው ቀናት ብቻ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ገቢው የተሰበሰበው ዋንጫው ወደ ዞኑ ከሄደበት ከግንቦት 29 ጀምሮ እስካሁን ባሉት ከ10 ያልበለጡ ቀናት ውስጥ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ በገንዘብ ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ 220 የቀንድና የጋማ ከብት፣ 423 ኪሎ ግራም ማርና ቅቤ አበርክቷል። የግድቡ ግንባታ ከሀገራዊ ጠቀሜታው ባለፈ በግላቸው የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ ኣስተዋጽኦ ማድረጉን መነሻ በማድረግ እስከ 110 ሺህ ብር ቦንድ በነፍስ ወከፍ የገዙ ግለሰቦች መኖራቸውንም መረጃዎች አመልክተዋል።
በዚህ ዞን የሆነው ይህ ብቻ አይደለም። በዳውሮ ዞን ተርጫ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ያደረጉት ተሳትፎም ትልቁን ድርሻ ወስዷል፡፡ ታራሚዎቹ ከቀለባቸው በመቀነስና በማረሚያ ተቋሙ በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው ከሚያገኙት ገቢ የቦንድ ግዥውን ፈፅመዋል።
ታራሚዎቹ ከቦንድ ግዥው በተጨማሪ በየማህበሮቻቸው የሰሯቸውን የእደ ጥበብ ስራዎች በስጦታ አበርክተዋል።
ይህ ህዝባዊ ርብርብ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን በሚገባው መጠን ያልተጠቀምንበት ሰፊ የሀብት ምንጭ አለና ዛሬም ትኩረት ይሻል:: በተለይ ከሀይል ማመንጫዎች የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀምበት የንግዱ ማህበረሰብ ሆኖ እያለ ከቦንድ ግዥ አኳያ አሁን ያለው ተሳትፎ ግን በሚጠበቀው ደረጃ እንዳልሆነ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው:: ስለሆነም የንግዱ ማህበረሰብ የቦንድ ግዢ ተሳትፎ እንደመንግሥት ሠራተኛው ሁሉ በላቀ ደረጃ ሊፈፀም ይገባዋል:: ለዚህ ስኬት ደግሞ ከአስፈፃሚው ጥረት ባሻገር የንግዱ ማህበረሰብ የግል ተነሳሽነትና ርብርብም ወሳኝ ነው::እንዲህ ያለጐትጓች በተረባረብን ቁጥር የህዳሴው ግድብ ይፋጠናል፤ የኢትዮጵያችን ህዳሴም እውን ይሆናልና።
ታላቁ የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያ ህዝቦች ወጪ እየተገነባ ያለ፣ የተፋሰሱ አገራት ህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትን፤ በአገራቱም መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ውድ ፕሮጀክታችን ነው። በመሆኑም ለአፈፃፀሙ ሁላችንም ልንተባበር ይገባል፤ የሚመለከታቸው ሀገራትም እንዲሁ።