Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትምህርቱ ዘርፍ ጉዟችን

0 400

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትምህርቱ ዘርፍ ጉዟችን

                                               ደስታ ኃይሉ

መንግስት ድህነትን እንደ ዋነኛ ጠላት ቆጥሮ መንቀሳቀስ ጀምሮ በልማት የታጀቡ ተከታታይ ውጤቶችን ማስመዝገብ ከቻለ 15 ዓመታትን አስቆጠረ። ይሁንና መንግስት ልማትን ዋነኛው ከድህነት አረንቋ የመላቀቂያ መንገድ በማድረግ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ የያዘው ቁርጠኛ ትግል ገና ከጅምሩ ጀምሮ አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ከእነዚህ ልማታዊ ተግባራት ውስጥ የትምህርቱ ዘርፍ አንዱ ነው። እርግጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ባልተደፈቀበት ሀገር ውስጥ ልማታዊውን ተግባር ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። ከዚህ አኳያ ሰሞኑን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና መሰረቅም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የዚህ ነባራዊ ሁኔታ መገለጫ ይመስለኛል።

የፈተና መሰረቅ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሊያጋጥም ይችላል። እንዲህ እንደ አሁኑ በይፋ አይውጣ እንጂ በተለያዩ ወቅቶች ‘ፈተና ተሰረቀ’ ሲባል የሰማሁባቸው አጋጣሚዎችን አስታውሳለሁ። ታዲያ ፈተናን መስረቅ ወንጀል አይደለም እያልኩ አለመሆኔ ይታወቅልኝ። በትምህርት ላይ የሚካሄድ ማንኛውም ዓይነት ሸፍጥ የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል መሆኑን እገነዘባለሁ፤ ሀገር ተረካቢ በሆነው ትውልድ ላይ የሚረጭ አደገኛ መርዝ ነውና።

እናም በጥብቅ ሊኮነንና ሊወገዝ ብሎም የድርጊቱን ፈፃሚዎች መንግስት ተከታትሎ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል። ይሁንና ይህ ጊዜያዊ ችግር መፍትሔ የሚያገኝ ብቻ ሳይሆን፤ በዘላቂው የትምህርት ዘርፍ ጉዟችን ላይ የጎላ ችግር የሚፈጥር አይመስለኝም። በመሆኑም ወደዚያው ማምራት ተገቢ ነው።

በቅድሚያ ከፍላጎታችን ልነሳ። ባለፉት ጊዜያት ህዝቡ ከውጭው ዓለም እንዲቸረው ይጠብቅ የነበረው የእህል አሊያም የገንዘብ ድጋፍና ዕርዳታን ብቻ አለመሆኑን ነው። በሀገራችን በተለያዩ ደረጃዎች በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ውስጥ የእውቀት ድጋፎችንም የሚሻ ነበር። የዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ በእውቀትና ክህሎት የታነፀ በቂ የሰው ሃይል ሊፈራ አለመቻሉ እንደሆነ አያከራክርም።

እዚህ ላይ በልማቱ መስክ ላይ ተሰማርቶ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል በጥራትና በበቂ ሁኔታ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ባለፉት ጊዜያት በህብረተሰባችን ውስጥ ይንፀባረቅ ስለነበረው አንድ እውነታ በማሳያነት ላንሳ።

ባለፉት ጊዜያት በሃገራችን በተለያዩ ደረጃዎች ይካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተን አሊያም በመገናኛ ብዙሃን ተከታትለናቸው ይሆናል። ከእነዚህም መካከል በግዙፍነታቸው አልያም በዘመናዊነታቸው እንግዳ የሆኑብን የሚታጡ አይመስለኝም።

እዚህ ላይ ለማንሳት የምፈልገው ጥያቄ ታዲያ “እነዚህ ስራዎች የኢትዮጵያዊያን ዕውቀት አርፎባቸው ለውጤት የበቁ ናቸው” ብለን የምናስብ ስንቶቻችን ነበርን? የሚለውን ነው። …እርግጠኛ ነኝ በርካቶቻችን እንደነዚህ ዓይነቶቹን ስራዎች ስንመለከት ቀድመን የምናስበው የውጭ ሙያተኞች እውቀት የፈሰሰባቸው እንደሆኑ ስንገምት ኖረናል።

እርግጥ ዓይነቱ አመለካከት መኖሩ ተገቢ አልነበረም የሚል ግምት የለኝም— ለረጅም ጊዜያት በልማቱ መስክ ላይ ውጤት ማምጣት የሚችል በእውቀትና በክህሎት የዳበረ በቂ የሰው ሃይል ሳይገነባ ቆይቷልና። በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ  የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ ለመሆን የተገደድነውም በዚሁ ሳቢያ እንጂ፤ ሀገሪቱ ከዓለም ገበያ ዕውቀት ለመግዛት የምታፈሰው የገንዘብ አቅም ስለነበራት አልነበረም።

ይሁን እንጂ ይህ ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ገና ገቢራዊ በመሆን ላይ በመሆኑ፤ በተጨማጭ ማሳያነት የማነሳው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትምህርት ዘርፍ ትግበራን ነው።

እንደሚታወቀው በትምህርት ዘርፍ የተያዘው ግብ የትምህርት ጥራትን የማሳደግ እና የአገልግሎት ሽፋኑም የማጠናከር ዕቅድ ነበር። እናም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መንግስትና ህዝቡ ባረደጉት ከፍተኛ ጥረት የአንደኛ ደረጃ (ከ1-8 ) ንጥር ተሳትፎ ምጣኔ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 82 በመቶ በ2007 ወደ 92 በመቶ ከፍ ለማድረግ ተችሏል። የወንድና ሴት ሕፃናት ተሳትፎ ምጥጥን 0.94 ገደማ ደርሷል፡፡ ይኸም አፈፃፀም የምዕተ – ዓመቱ የትምህርት ግብ ለማሳካት ያስቻለ ነው።

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። በትምህርት ጥራቱ ዙሪያ ዛሬም ልክ እንደ ፈተናው መሰረቅ ዓይነት ያሉ ተግዳሮቶችን ማስወገድ ይገባልና።

የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (ከ9-10) ጥቅል ተሳትፎ ምጣኔ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 39.7 በመቶ ወደ 62 በመቶ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙም ለውጥ ሳያሳይ ባለበት መቆሙን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት እየጐረፈ ያለውን ተማሪ ለማስተናገድና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ለማሳደግ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታን ማስፋፋት የግድ ይላል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርት (ከ11-12) ጥቅል ተሳትፎ በ2002 ከነበረበት 7 በመቶ በ2007 ወደ 20 በመቶ ገደማ በማሳደግ ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን ያገኘኋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የቅበላ አቅም ከፍ ያለ ሲሆን፤ የባለሙያዎች የብቃት ምዘና በስፋት ተከናውኗል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የጥራትና አግባብነት ችግር አሁንም ጐልቶ የሚታይ በመሆኑ በቀጣይ በዚህ ዙሪያ መሠረታዊ መሻሻል ለማምጣት ከፍተኛ ርብርብ መጠየቁ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡

ዛሬ ላይ በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ በተከናወነው የማስፋፋት ሥራ በቅድመ ምረቃ የቅበላ አቅምን ወደ 400 ሺህ እንዲጠጋ አድርጎታል። በድህረ ምረቃም በኩል የቅበላ አቅም ወደ 28 ሺህ ገደማ ከፍ ብሏል። የሴት ተማሪዎች ድርሻ በቅድመ ምረቃ 32 በመቶ፣ በድህረ ምረቃ 19 በመቶ ደርሷል።

እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በዕናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ምን ያህል ርቀት እንደተየጓዘች የሚያሳዩ ናቸው።

እርግጥ ከዚህ የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች እንደሚኖሩና በችግሮቹ ሳቢያ የሚፈጠሩ የትምህርት ሥርዓቱ አጠቃላይ መገለጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው።

በመሆኑም ሀገራችን “ዕውቀት ሁሉ ከውጭ የሚገባ ነው” ከሚባልበት ዘመን ወጥታ፣ ዛሬ ላይ በራሷ አቅም የትምህርትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። በዚህም በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉ መስች የቅበላ አቅሟን አሳድጋለች። የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ለማረጋገጥም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኗ እየተረባረበች ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy