Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የነገ ሰውነታችን” በዛሬ ተግባራችን ላይ ይመሰረታል!

0 486

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የነገ ሰውነታችን” በዛሬ ተግባራችን ላይ ይመሰረታል!

                                                      ዘአማን በላይ

ኢትዮጵያ ከ26 ዓመታት በፊት የነበረችበት አስከፊ ሁኔታ ከማንም የሚሰወር አይደለም። ይህ ሀገርና ህዝብ እጅግ በመረረ የስቃይና የሰቆቃ አገዛዞች ውስጥ ሲማቅቅ እንደነበር ይታወቃል። የቅርብ ጊዜውን ብናስታውስ እንኳን፤ ደርግ ወጣቱን መግቢያና መውጫ አሳጥቶት በግዳጅ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አሳራቸውን ሲበሉ ነበር። ይህ ብዙም ምርምር የማይጠይቀን የቅርብ ጊዜያችን ታሪክ ነው። ታዲያ ሁሌም ስናስታውሰው የምንኖረው ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዳግም ላይመለስ ምዕራፉ ተዘግቷል—በአሁን ወቅት ሀገራችን እየተከተለች ያለችውን ስርዓት ለማምጣት ሲሉ ህይወታቸውን ቤዛ ላደረጉ፣ አካላቸውን ላጎደሉና ንብረታቸውን መስዋዕት ላደረጉ የህዝብ ልጆች ምስጋና ይግባቸውና።

በዚህ ሁለንተናዊ መስዕዋትነት በተገኘ ድል ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀለሙ በማይደበዝዝ ብዕር ደማቅ ታሪክ እየፃፉ ነው። ትናንት አንገት ያስደፋቸውን ድህነት ድል እየነሱ ይገኛሉ። ወጣቱ ትናንት በየጥሻው እየተሽሎከሎከ ራሱን ከብሔራዊ ውትድርና ማሸሽን ዳግም አያስበውም። ዛሬ ላይ እውን እየሆነ ያለው ስርዓት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ የሚጋብዘው ጦርነትንና ስደትን ሳይሆን፤ ልማትንና በሀገር ውስጥ ሰርቶ የማደግ መብትን ነው። እናም መንግስት ወጣቱን ‘በሀገርህ ሰርተህ ተለወጥ’ በማለትም ካለችው አነስተኛ በጀት ላይ ቀንሶ ወጣቱን “የነገ ሰው” ለማድረግ ርብርብ እያደረገ ነው። ወጣቱን ሀገር ገንቢና ተረካቢ ለማድረግ ዛሬ የሚከናወነው መንግስታዊ ጥረት “የነገ ሰውነታችንን” ይወስነዋል። ከሀገራችን የህዝብ ቁጥር ውስጥ ግማሹን ያህል ይሆናል ተብሎ የሚገመተው ወጣት አፍላና ትኩስ ኃይል ነው። ወጣቱ ጉልበቱን፣ አቅሙንና ክህሎቱን ካስተባበረ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መድን መሆኑ አይቀሬ ነው። ተስፋ የሚጣልበትም የሀገር ሃብት ነው—“ወጣት የነብር ጣት” እንዲል ብሂሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ለወጣቱም ቢሆን ከዚህች ሀገር ውጭ ሌላ ሁለተኛ ሀገር የለውም። የነገ ተስፋው በዚህችው ሀገር ላይ ጥሮ ግሮ በሚያፈራው ጥሪት የሚወሰን ነው። ዛሬ ያልተቦካ ሊጥ ነገና ከነገ በስቲያ ሊጋገር እንደማይችል ሁሉ፤ በአሁኑ ወቅት ያልተሰራ ጉዳይ በተአምር ካልሆነ በስተቀር ነገ ሊኖረን አይችልም። እናም ነገን ለማለም ዛሬን ተግቶ መስራት የግድ ይላል። በአሁኑ ወቅት በጠባቂነት መንፈስ ብቻ የምንኖር ከሆነ፤ ለነገ የምናሳድረው ነገር አይኖርም። ለነገ ምንም ማሳደር ካልቻልን ደግሞ፤ ራዕይ አልባ የመሆን ዕጣ ፈንታ ይጋረጥብናል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ያለንንና ያገኘነውን ዕድል አሟጠን በመጠቀም ነገን ብሩህ ማድረግ እንደሚቻል ሁሌም በአንክሮ ማሰብ ያስፈልጋል።

መንግስት የወጣቱ “ነገ” ብሩህ ይሆን ዘንድ ፓኬጆችን ከመቅረፅና ወደ መሬት ከማውረድ ባሻገር፤ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ካለው ውስን ባጀት በመቀነስ የ10 ቢሊዮን ተንቀሳቃሽ ፈንድ መድቦ ወጣቱ በስራ ፈጠራ ላይ እንዲሰማራ የተመቻቸ ዕድል ፈጥሯል። ታዲያ ወጣቱ ይህን ዕድል በሚገባ ሊጠቀምበት ይገባል። ርግጥ ዕድሉን በአግባቡ ለመጠቀም አንዳንድ የተዛቡ አስተሳሰቦችን መቅረፍ ተገቢ ይመስለኛል።

በመጀመሪያ ደረጃ የስራ ክቡርነትን ማመን ያስፈልጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ስራን አክብሮ ያለመያዝ ችግር በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ መቀረፍ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል። ለነገሩ ዛሬ ሁሉንም ገንዘብ አመንጭ ስራዎችን አክብረን እንዳንይዝ ያለፉት ስርዓቶች ለተለያዩ የሙያ ስራዎች በስድብ የታጀበ ስያሜ በመስጠት ህብረተሰቡ ለአነስተኛ ስራዎች ግምት እንዳይሰጥ ማድረጋቸው ርግጥ ነው። ታዲያ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ዛሬ ላይ በሂደት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፤ አሁንም ይበልጥ ሊያድግና ሊጎለብት ይገባዋል። ባደጉት ሀገሮች ውስጥ ማንኛውም ሰው ‘ስራ አለህ?’ ተብሎ እንጂ ‘ስራህ ምንድነው?’ ተብሎ አይጠየቅም። ምክንያቱም የሰው ልጅ ምንም ዓይነት ስራ ቢሆን መስራት ይኖርበታል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ይህም ስራው ምንም ይሁን ምን ክቡር መሆኑን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ማናቸውንም ስራ ባለመናቅና አክብሮ በመያዝ ማደግና መበልፀግ እንደሚቻል ጠንካራ እምነት ሊይዙ ይገባል እላለሁ።

ርግጥ የሀገራችን ወጣቶች የስራ ባህል የላቸውም እያልኩ አይደለም። ማለትም አልችልም። ምናልባትም ለማለት የምችለው የስራ ባህላቸው አልዳበረም ነው። ምክንያቱም ወጣቶቻችን ሌላው ቀርቶ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ውስጥ በኮብል ስቶን፣ በቤቶች ኮንስትራክሽን፣ በንብ ማነብ፣ በቆዳ ምርት ስራዎችና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው ስራን በማክበር አክብረው እየሰሩና ጥሪት እየቋጠሩ መሆናቸውን ማንኛውም ዜጋ በሚገባ ስለሚያውቀው ነው። ያም ሆኖ ወጣቶቻችን የስራ ባህላቸውን ያጎልብቱት፤ ይበልጥም ያደርጁት ለማለት እወዳለሁ። በዚያው ልክም ስራ ላይ የነበሩት ወጣቶች በአዲስ መልክ ወደ ስራው ለሚገቡት አቻዎቻቸው አርአያ በመሆን የስራን ክቡርነት ባህል ሊያሳዩዋቸው ይገባል ብዬም አምናለሁ።

ወጣቶቻችን የስራ ባህላቸውን ሲያዳብሩም ማንኛውም ተግባር መነሻ ያለው መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። እዚህ ላይ ነገሩን በደንብ ለማብራራት “እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል” የሚለው ሀገራዊ ብሂል አሊያም “ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም” የሚለው ጥቅል አባባል ገላጮች ይመስለኛል። አንድን ስራ ስንከውን መነሻችን ብድር ሊሆን ይችላል—ልክ መንግስት እንዳዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ፈንድ ዓይነት ማለቴ ነው። ታዲያ በቅድሚያ ‘ይህን የብድር ገንዘብ እንዴት አድርጌ ባንቀሳቅሰው ነው ውጤታማ ልሆን የምችለው?’ ብሎ በሰከነ አዕምሮ ማሰብ ያስፈልጋል። እንዲሁም ስራውን ‘እኔ ማን ነኝ?፣ መነሻዬ ምንድነው?፣ ምን መስራት አለብኝ?፣ ወደፊትስ ምን ደረጃ ላይ ለመድረስ ነው ስራዬን የምከውነው?፣…ወዘተ.’ የሚሉ ጥያቄዎችን ራስን ደጋግሞ መጠየቅ ይገባል።

ታዲያ ጥያቄዎቹን ረጋ ብሎ ለመመለስ የአንድን ስራ መነሻና መድረሻ ከማወቅ ባሻገር የብድር ገንዘብ በጊዜ ዑደት ውስጥ (ወለድ ካለው) ከነ ወለዱ የሚመለስ መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በአጭሩ የብድሩ ገንዘብ ዕዳ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ይህ ደግሞ በተበዳሪዎች ላይ ዕዳን ሰርቶ የመክፈል የኃላፊነት መንፈስን ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪ ገንዘቡን ሌሎች ወጣቶች ስራን እንደ አዲስ ለመጀመርም ይሁን የነበራቸውን ለማስፋፋት መልሰው እንዲወስዱት ዕድል ይፈጥራል። እናም ወጣቶች የወሰዱትን ገንዘብ ብልህነት በተሞላበት ሁኔታ መጠቀማቸው፤ አንድም ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሊያግዙ፣ ሁለትም የኃላፊነት ስሜት በውስጣቸው እንዲሰርፅ የሚያደርግ ይመስለኛል።

ለነገሩ አንዳንድ ወጣቶች ገና ከጅምሩ ‘እንዴት ይህን ስራ ሰርቼ ያልፍልኛል?’ በማለት በአንዴ ሁሉንም ነገር የማግኘት የተሳሳተ እሳቤ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ—በአቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎትን አንግበው ማለቴ ነው። ዳሩ ግን ሁሉም ነገር በጊዜ ሂደት ውስጥ እንጂ በአንዴ የሚገኝ አይደለም። የሎተሪ እጣ አሊያም የቤተሰብ ለዘመናት የተከማቸ ሃብት እስካልሆነ ድረስ በአንዴ መበልፀግ አይቻልም። ማንኛውም ስራ ልፋትን፣ ጊዜንና በዕቅድ መመራትን ይጠይቃል። ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው አባባሎች ውስጥ እንቁላል በአንዴ ጫጩት ሆኖ በእግር እንደማይሄደው ሁሉ ወይም ውቢቷ ሮም በአንድ ጀንበር እንዳልታነፀች ሁሉ፤ በስራ ላይ በአንዴ ሰርቶ በአንዴ መበልፀግ አይቻልም። ሰርቶ ማደግ፣ መለወጥና መበልፀግ ከጊዜ ጋር የሚሄዱ እውነታዎች ናቸው። ከዚህ ውጭ በአቋራጭ የመበልፀግ አስተሳሰብና ተግባር ለራስም ይሁን ለሀገር የሚበጅ አይሆንም።

በአቋራጭ ለመበልፀግ ማሰብና በተግባሩ ላይ ለመሰለፍ መሞከር ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከሙስና ጋር የሚያያዝ አስተሳሰብ ነው። አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ ገና ለገና በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልፍልኛል ብሎ በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና ላይ ከተሰለፈ የግንኙነት ሰንሰለቱ ሲታወቅ በወንጀል ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። በህጋዊ መንገድ ስራን መከወን እየተቻለ፤ በወንጀል ሊያስጠይቅ በሚችል ተግባር ላይ ውሎ መገኘት ቡድኑን ወይም ግለሰቡን ዋጋ ያስከፍላል።

በአቋራጭ ለመበልፀግ መሞከር ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን እንደ ማሳለጫ መንገድ የሚወስድ በመሆኑም በሀገር ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ደግሞ አንድ ሰው በሰራው ስራ ልክ እንዳያገኝ የሚያደርግ ‘የእከክልኝ ልከክልህ’ ሰንሰለታዊ ስብስብ የሚፈጥረው ድርጊት በመሆኑ ውጤቱ አደገኛ ነው። በተለይም እንደ እኛ በማደግ ላይ በሚገኝና “የነገ” ተስፋ ላለው ሀገር፤ ኢኮኖሚን በማሽመድመድ የቁልቁለት ጉዞ እንድንጀምር የሚያደርግ ክፉ በሽታ ነው። ወጣቶቻችንም ይህን ክፉ ደዌ ሊፀየፉት ይገባል። እናም የዚህች ሀገር የነገ ተስፋዎች የሆኑት ወጣቶች በጎ ምግባሮችን በመማርና ራሳቸውም ፋባ ወጊ ሆነው በማስተማር የተምሳሌነትን ችቦ ከፍ ሊያደርጉ ይገባል።

በስራ ላይ ያለንን ያልዳበረ ምልከታ ዛሬ ላይ ካላጎለበትን፣ በአቋራጭ ለመበልፀግ አስተሳሰብ ሊዳርጉን የሚችሉትን የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙስናን እሳቤና ትግበራን ካልተፀየፍን “የነገ ሰው” ልንሆን አንችልም። አሁን ላይ ያሉትን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን እንደ ግለሰብም ይሁን ቡድን ማረቅ ካልቻልን፤ የነገን ብሩህነት ልናስብ አይገባም። እናም የነገ ደማቅ የብልፅግና ፀሐይን መመልከቻ መነፅራችን ዛሬ የምንተገብረው ሰናይ ምግባራችን ውጤት ስለሆነ፤ ለግለሰብና ለቡድን የማይበጁ አሊያም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የዕድገት ጉዞ ሊያደናቅፉ የሚችሉ እኩይ ተግባሮችን ልናወግዛቸውና ልንፀየፋቸው ይገባል እላለሁ።                 

 

                   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy