Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ሠላም ማስፈን ነው

1 264

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ሠላም ማስፈን ነው

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት ስርአትን የሚቃወሙ  እና/ወይም በህዝብ ውክልና ስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካል ኢኮኖሚ መርህ የሚጎረብጣቸው የውስጥም የውጭም ቡድኖች አንድ ከአፋቸው አልወርድ ያለ የመቃወሚያ አጀንዳ አላቸው። ይህም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2001 ዓ/ም አጽድቆ ያወጣው የበጎ አድራጎቶችና ሲቪክ ማህበራት አዋጅ መነሻ ያደረገ ነው። አዋጁ በሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ ላይ የሚሰሩ የሲቪክ ማህበራትን እንቅስቃሴ ይገድባል ባይ ናቸው። አዋጁን በቅንነት ጠለቅ ብሎ የመረመረ ሰው ግን የተቃውሞው መነሻ የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴ ከመገደብ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ መረዳት ይችላል።

ምክንያቱም፤ በቅድሚያ የሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ኢትዮጵያውያን በህገመንግስት በተረጋገጠላቸው የመደራጀት ነጻነት መሰረት ሲቪክ ማህበር አደራጀተው በማንኛውም ሃገራዊ ጉዳይ ላይ – ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የመስራት መብታቸው ላይ ምንም አይነት ገደብ አያስቀምጥም። በሌላ በኩል የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ነጻነት ያላቸው መሆኑን አረጋግጧል። በማንኛውም ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ሃገር በቀል ሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ምንጫቸው ከውጭ ሃገር መሆን እንደሚችልም ፈቅዷል። ከ10 በመቶ በላይ የገንዘብ ምንጫቸው ከውጭ ሃገር የሆኑ ሃገር በቀል መንግስታዊ ማህበራትና ድርጅቶች እንደውጭ ማህበር ወይም ድርጅት እንዲመዘገቡ ይጠየቃሉ እንጂ መንቀሳቀስ አይገድባቸውም።

አዋጁ የሚከለክለው አንድ ነገር ብቻ ነው። ይህም በአዋጁ መሰረት የውጭ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማህበራት በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መስራት የማይችሉ መሆኑ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ሃገር በቀል ድርጅቶችና ማህበራት የውጭ የገንዘብ ምንጫቸው ከ10 በመቶ መብለጥ አይችልም። ይህ እንዲሆን የተደረገው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ጉዳይ የሆነው የሃገሪቱ ፖለቲካ ከውጭ ተጽእኖ ነጻ መሆኑ እንዲረጋገጥ ነው። ይህ መሆኑ ሃገር በቀል ማህበራትና ድርጅቶች ከምንም የውጭ ተጽእኖ ነጻ ሆነው በሃገራቸው ዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ እንዲሰሩ ያግዛቸዋል። ይህ ሃገር በቀል ሲቪክ ማህበራትንና ድርጅቶችን ከውጭ ተጽእኖ ውጭ በማድረግ ምሉዕ እንዲሆን ያደርጋል እንጂ በምንም አግባብ አንቅስቃሴያቸውን አይገድብም።

በሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች አዋጅ ላይ የሚነሳውን ተቃውሞ ከላይ ከተገለጸው እውነታ አኳያ ስናይ፣ ጉዳዩ የሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ይጥላል ከሚል ስጋት የመነጨ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ብቻ የሆነው የሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ገብተን እናቡካ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። የሚያስገርመው ይህን የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ የመፈተፈት የውጭ ሃይሎች ፍላጎት አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም የሚደግፉት መሆኑ ነው። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ይህን የሚያደርጉት በየዋህነት ነው። አንዳንዶቹ ግን፣ የውጭ ሃይሎች የሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው መፈትፈታቸው ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ወደስልጣን መውጣት የሚያስችል እድል ያስገኝልን ይሆናል ከሚል ባንዳዊ ስሌት የመነጨ ነው፤ ለነጭ አድረው፣ በእጅ አዙር ነጮቹ የሚመሩት ሃገር መፍጠር።

ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖ እንጂ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ከበቂ በላይ ምላሽ የተሰጠበትን የሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅ መመልከት አልነበረም። የዚሀ ጽሁፍ ዓላማ  “የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)” የተሰኘው በሃገሪቱ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ሃገር በቀል የበጎ ድራጎት ማህበር ያለውጭ ድጋፍ መንቀሳቀስ እንደሚቻል በማሳያነት አንስቼ፣ በማያያዝ ማህበሩ በቅርቡ 142ኛ መገለጫ ያወጣበትን በሃገሪቱ የታወጀውና እስካሁንም በስራ ላይ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ምን እንደሚመስል መዳሰስ ነው።

የሰብአዊ መብት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መበቶች ጉባኤ በሚል ስያሜ የደርግ መንግስት ተወግዶ የሽግግር መንግስት በተመሰረተ ሶስተኛ ወር ላይ መስከረም 1984 ዓ/ም ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የተመሰረተ ሃገር በቀል ማህበር ነው። ሰመጉ አሁንም በበጎ አድራጎት ማህበራትና ድርጅቶች አዋጅ መሰረት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሃገር በቀል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማህበር ነው። ማህበሩ በኢትዮጵያ የመደራጀት መብት በተረጋገጠባቸው ያለፉ ሃያስድስት አመታት በስራ ላይ ቆይቷል። ሰመጉ በአዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ በተጨማሪ በመላ ሃገሪቱ ለመስራት እንዲያመቸው በስድስት የሃገሪቱ ከተሞች ማለትም፤ በሃዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ድሬደዋ፣ ነቀምት፣ ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለመክፈት በቅቷል።  ሰመጉ፣ ሃገር በቀል ሲቪክ ማህበራት በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ያለገደብ የመስራት ነጻነት የሚያሳይ፣ ችግሮች እንኳን ቢኖሩ ማለፍ እንደሚቻል የሚያረጋገጥ ህያው አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ማህበር ነው። ማህበሩ አልፎ አልፎ የውጭዎቹን ዶላር መጎምጀቱ ባይቀርም፣ ከ10 በመቶ ያልዘለለ የውጭ ድጋፍ እያገኙ በአግባቡ መስራት እንደሚቻል በማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑ ግን እርግጥ ነው።

ሰመጉ ሰሞኑን 142ኛ የኢትዮጵያ የሰበአዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮረ መግለጫ አውጥቷል። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ (ከመስከረም 28፣ 2009 ዓ/ም) ጀምሮ በዜጎች ላይ የሚፈጸም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአሰቸኳይ ይቁም!” በሚል ርዕስ የወጣው መግለጫ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በመንግስት ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚመለከት ዝርዝር ጉዳይ ይዟል።

ሰመጉ በመግለጫው የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚል የዘረዘራቸው ድርጊቶች በትክክል ተፈጽመው ይሁን አይሁን የሚያወቀው ማህበሩ ራሱ ነው። ሃሰተኛና በህሊና ዳኝነት በአግባቡ ተመርምረው ያልተረጋገጡ መረጃዎች፣ ቁልጭ ያለ እውነታን ከማሳየት ይልቅ የራስ ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ መልዕክት ለማስተላለፍ ተጋኖ የሚቀረበ ጉዳይ  የሚጠቀሙትና የሚጎዱት ወገን ሊኖር ቢችልም ጥቅማቸውም ጉዳታቸውም ዘላቂ አይደለም። የዚህ አይነት ይዘት ያላቸው ይፋዊ መግለጫዎች ዞሮ ዞሮ መግለጫ አውጭውን የታሪክ ተወቃሽ ማድረጋቸው አይቀሬ መሆኑ እርግጥ ነው። እናም ሰመጉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ብሎ በመግለጫው ላይ ያሰፈራቸው ጉዳዮች ሃሰተኛና የተለየ ፍላጎትን ለማስተላለፍ ዓላማ ያለወጉ የተጋነኑ ቢሆኑ፣ ከዚህ ሊጠቀም የሚፈልገውም ቡድን ዘለቄታዊ ጥቅም አያገኝም፤ እንዲጎዳ የታሰበውም ዘለቄታዊ ጉዳት አይጎዳም። በመሆኑም የመግለጫውን ትክክለኝነት ጉዳይ ለራሱ ለሰመጉ እተወዋለሁ።

ይሁን እንጂ ሰመጉ መስሰከረም 28፣ 2009 ዓ/ም ላይ ለስድስት ወር የታወጀውና መጋቢት 21፣ 2009 ዓ/ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ ጥያቄ ለአራት ወራት እንዲራዘም የተወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ መነሻውንም መድረሻውንም አፈና አስመስሎ ያቀረበበት ሁኔታ አልተመሸችም። ይህ ተገቢ ስላልመሰለኝ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ላይ ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጀውና በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓላማ የህዝብን ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ጥያቄዎች ማፈን አይደለም። ሁላችንም እንደምናስታውሰው የህዝብ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የቀሰቀሱት ቅሬታ በይፋ ተቃወሞ የተገለጸበት ሁኔታ ነበር። ይህ የህዝብ ተገቢ ቅሬታ የቀሰቀሰው ተቃውሞ ግን ህገመንግስታዊ ስርአቱን በመናድ ሃገሪቱ ዳግም ሃገር መሆን በማትችልበት ሁኔታ ለማፍረስና ለመገነጣጣል በሚፈልጉ ሃይሎች ተጠልፎ ወደአውዳሚ ሁከትነት ተለውጦ ነበረ። በዚህ ሁከት ህዝቡ አነሱኝ፣ ይጨመሩልኝ የሚል ጥያቄ ያነሳባቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ተቋማት እንዲወድሙ ተደርጓል። የብሄር ጥላቻ በመቀስቀስ አንዱን ሌላወ ላይ የማስነሳት ተግባር ተፈጽሟል። ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ ተደርገዋል። ሰዎችን በአመለካካታቸው ብቻ እሰከመግደል የሚደርስ ጥቃት ተፈጽሟል። እነዚህ ድርጊቶች ወንጀሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ናቸው። ሰመጉ ይህን ገሃድ እውነት ይክዳል የሚል ግምት የለኝም።

ህዝቡ ላይ ጫን ያለ ቅሬታ አሳድረው የነበሩት የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በዚህ የሁከት ሁኔታ ውስጥ ምላሽ ሊያገኙ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዚሀ ሁከት ለህዝቡ የልማትና የዴሞከራሲ ጥያቄዎቸ ምላሽ የሚሰጥ የመንግስት ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር ብሎ የሚያስብ ካለም እጅግ ተሳስቷል። የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) መሪዎችም ይህን መገንዘብ ይሳናቸዋል የሚል ግምት የለኝም። ሁከቱ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ባላጋራዎች ጭምር እጃቸውን አስገብተውበት ስለነበረ ሃገሪቱን አፈራርሶ የእልቂትና የስቃይ አውድማ ወደማደረግ መወሰዱ አይቀሬ ነበር። በመሆኑም ይህ ሁኔታ ተቀልብሶ ለህዝቡ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ መሰጠት የሚያስችል የተረጋጋና የሃገሪቱን ዘላቂ ህልውና የሚያረጋግጥ ሁኔታ መፈጠር ነበረበት። የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የታወጀው፣ ለህዝቡ አጣዳፊ የልማትና ዘላቂ የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው የተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ በተለመደው ህግን የማስከበር ስርአት ማስፈን ስላልተቻለ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው በዘፈቀደ ሳይሆን ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት የታወጀ መሆኑም መታሰበ አለበት። ከቁጥጥር እየወጣ የነበረው የሃገሪቱን ህልውና ለአደጋ ያገለጠው ሁከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሲደርስ መንግስት ይህን የሚቀለብስ እርምጃ እንዲወስድ ህዝቡ መወትወት ጀምሮ እንደነበረም መታወስ አለበት።

እንግዲህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ በሁከት የተተረማመሰውን ሁኔታ በመቀልበስ፣ የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ መመለስ የሚያስችል የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠር ነው። በተጨባጭ እንደምናየው ይህ እየተሳካ ነው። ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሷል። ያላግባብ ግንባታቸው የተቋረጠና በብልሽት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የልማት ፕሮጀከቶችን አገልግሎት በሚሰጡበት ደረጃ ለማስተካካል እየተሰራ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በመንግስት ውስጥ ድምጹን የሚያሰማበት ውክልና እንዲያገኝ ለማድረግ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የተጀመረው ድርድር እስካሁን በስኬት እየተከናወነ ነው። እነዚህ ውጤቶች ሊገኙ የቻሉት በሃገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመታገዝ ወደነበረበት መረጋጋት በመመለሱ ነው።

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ዓላማ ሰመጉ ሊነግረን እንደሞከረው አፈና ሳይሆን፣ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱ ሲረጋጋጥ ይነሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብቻውን ያሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም አያረጋግጥም። ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በዋነኝነት በህዝቡ ተሳትፎ ነው። እስካሁን የተገኘውም ሰላምና መረጋጋት የህዝቡ ተሳትፎ ውጤት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በሰላም የሚጠቀመው፣ በሰላም እጦትም የሚጎዳው ህዝብ ነው። እናም አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው የሰላም ተጠቀሚና ባለቤት በሆነው ህዝብ ብቻ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ መድረሻ ከህዝቡ እጅ ሊያፈተልክ ተቃርቦ የነበረው ሰላም ህዝቡ መልሶ እንዲረከብ ከማገዝ ያለፈ አይደለም።

  1. Norton Finance says

    በዕዳ መዳሰስ ወይም አስተዳዳሪ ውስጥ ነህ? የተከለከሉ ዝርዝር ውስጥ ነዎት? ወርሃዊ ክፍያዎችዎን ለመክፈል ይታገላሉ? ቤት, መኪና ወይም የንግድ ብድር ለመግዛት ፈልገሃል, ግን በዕዳ ክለሳ ወይም አስተዳደር ስር ነህ? ለጥያቄዬ መልስ አዎ ከሆነ መልስ አለዎት? በበለጠ በኢሜል ያግኙን: nortonfinance2017@gmail.com

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy