Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ህወሓትና ደኢህዴን የተመሰረቱባቸውን ታሪካዊ ሥፍራዎች ጎበኙ

0 317

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የተመሰረቱባቸውን ታሪካዊ ሥፍራዎች ጎበኙ።

የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ታሪካዊ ቦታዎቹን የጎበኙት በየዓመቱ ሰኔ 15 ቀን የሚከበረውን የትግራይ የሰማዕታት ቀን ምክንያት በማድረግ ነው።

የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎቹ ህወሓት ከ42 ዓመት በፊት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን የደደቢት በርሃ እንዲሁም ደኢህዴን ከ26 ዓመት በፊት በይፋ የተመሰረተበትን ‘‘ማይ ዒባራ‘‘ በመባል የሚጠራውን ታሪካዊ ስፍራ ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች እንዳሉት በጉብኝታቸው ወቅት ባዩት ነገር የቀድሞ ታጋዮች የዓላማ ጽናትና ቆራጥነት ከፍተኛ እንደነበረና ለድል ያበቃቸው መሆኑን ግንዛቤ አግኝተዋል።

ከጎብኚዎቹ መካከል ከደቡብ ክልል የመጡት አቶ በቀለ ሌሌ እንዳሉት፣ ታሪካዊ ሥፍራዎቹ የድርጅቶቹና የታጋዮችን የዓላማ ጽናት ከማሳየት ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲጠናከር መሰረት ሆነዋል።

አባገዳ አብዱልራህማን ደቀቤ በበኩላቸው፣ ድርጅቶቹ የተመሰረቱባቸው አካባቢዎች ለሰው ልጅ መኖሪያ ይቅርና ለዱር እንስሳትም አስቸጋሪ እንደሆኑ በጉብኝቱ ወቅት መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

“ታጋዮቹ ችግሩን በጽናት ተቋቁመው አላማቸውን ማሳካታቸው የሚያስደንቅ ነው” ያሉት አባገዳ አብዱልራህማን፣ ታሪካዊ ስፍራዎች ለድሉ መሰረት መሆናቸውንና ወጣቱም ከታጋዮች ጽናት ብዙ መማር እንዳለበት ተናግረዋል።

ድርጅቶቹ የተመሰረቱባቸውን ቦታዎች በአካል ተገኝተው ለመጎብኘት በመብቃታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ተወክለው የመጡት ወይዘሮ ትዕግስት ሱባኬ ናቸው።

ውድ ታጋዮች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሳይበገሩ ራዕያቸውን ማሳካት መቻላቸው በተለይ ዛሬ ላለው ወጣት ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን አስረድተዋል።

“ታሪካዊ ሥፍራዎቹ ሁሌም የጽናትና የአይበገሬነት ምሳሌ ናቸው” ያሉት ወይዘሮ ተዕግስት፣ ሁሉም ሰው ሥፍራዎቹን በቀላሉ መጎብኘት እንዲችል ወደአካባቢው የሚያደርሱ መንገዶች መስተካከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአገር ሽማግሌዎቹና አባ ገዳዎቹ ከእዚህ በተጨማሪ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እና የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራስያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የተመሰረቱባቸውን ታሪካዊ ቦታዎችና የአክሱም ኃውልት መጎብኘታቸው ተመልክቷል።

በጉብኝቱ ላይ 165 የአገር ሽማግሌዎቹና አባ ገዳዎቹ የተሳተፉ ሲሆን በየደረሱባቸው አካባቢዎች ከሕብረተሰቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ጎብኚዎቹ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የተውጣጡ ናቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy