NEWS

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ2ኛ ጊዜ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማት ተበረከተለት

By Admin

June 04, 2017

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ መርጥ አየር መንገድ በመባል በአፍሪካ አቪዬሽን ባለስልጣን ተሸልሟል።

አየር መንገዱ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 26ኛው ዓመታዊ የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ፋይናንስ ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ላይ ነው ሽልማቱ የተበረከተለት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላምሰዘገበው ተከታታይ እድገት፣ የትርፋማነት እና በአፍሪካ አቪዬሽን እድገት ውስጥ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ተብሎ ሽልማቱ እንደተበረከተለት ተገልጿል።

ሽልማቱን የተቀበሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፋይናንስ ተጠባባቂ ኦፊሰር አቶ መሰረት ቢተው፥ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማትን ለሁለተኛ ጊዜ በመሸለማችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።

ሽልማቱ የአየር መንገዱ አስተዳደር እና በሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞቹ ውጤት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘው ሽልማት አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ለማስተሳሰር የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሸለሙን ያበሰሩት የአፍሪካ አቪዬሽን ስራ አስፈጻሚ ኒክ ፋዱግባ፥ ባለፉት 12 ወራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻዎችን በማስፋት፣ በረራዎቹን ዘመናዊ በማድረግ፣ ሶስት አዳዲስ የአውሮፕላን መጠገኛ ማእከላትን በመክፈት እና የራሱ የምግብ ማዘጋጃ በመክፈት አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ ትርፋማ መሆን መቻሉን የገለጹት ስራ አስፈጻሚው፥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2025 ለማሳካት ያስቀመጠውን እቅድ በጥሩ ሁኔታ እያስፈጸመ መሆኑን አስታውቃል።fbc