Artcles

የኢንቨስትመንት ምቹ ሀገር

By Admin

June 20, 2017

የኢንቨስትመንት ምቹ ሀገር

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ፍሰት ሰንሰለት ውስጥ ትገኛለች። ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት የኢፌዴሪ መንግስት በሀገራችን የተፋጠነ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፉም ባሻገር፤ በተግባር መተርጎም መቻሉም ነው፡፡

ዛሬ ላይ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል፡፡ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት የማሳየታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል።

በእኔ እምነት ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በግሉ ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ተደርጓል።

የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ ሐገራዊ ባለሃብቶች ተፈጥረዋል፡፡ እነአዚህ ባለሃብቶች በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች እየተደረገላቸው ነው።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ባለሃብቶቹ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። ብዙዎቹ ሀብት እንዲያፈሩ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ችለዋል።

የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ከማበረታታት አንፃር ለንፅፅር ይረዳን ዘንድ፤ በደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት ከነበሩት ጥቂት የግል ነጋዴዎችና የመንግስት ልማት ድርጅቶች እንደነበሩ እናስታውሳለን። ባለፉት 26 ዓመታት ግን ለግሉ ባለሃብት በተሰጠው ትኩረት ሚሊዩን ነጋዴዎች በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ነው። እጅግ በርካታ አስመጪ እና ላኪዎችም ተፈጥረዋል።

የሀገር ውስጥን ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት ለመፍጠር የተቻለው የገበያ ትስስርም ምቹ የኢንቨስትመንት መሰረትን ጥሏል ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፣ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው።

የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል ዕቃዎችና ግብዓቶች ያለ ቅድመ- ሁኔታ የሚገቡበትን ዕድል የመፍጠር ብሎም ባለሃብቶቹ ለስራቸው የሚሆን መሬት በሊዝ እንዲያገኙ መደረጉ ተጨማሪ አመቺ መደላድሎች ነበሩ። እነዚህ በመንግስት በኩል አቨስትመንትን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች የቅጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ላይ ዓይናቸውን እንዲጥሉ ያደረጉ ተግባራት ናቸው።

እዚህ ላይ አንድ ዕውነታን ማንሳት አግባብነት ያለው ይመስለኛል። ይኸውም ሀገራችን የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ-ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ያልተሟሉባት በመሆኗ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከሀገራዊው ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ግንባታዎች ለማካሄድ በመንግስት በኩል እንደሚካሄደው በተመሳሳይ ሁኔታ የግሉ ባለሃብት ሊከናወን አለመቻሉ ነው። የግሉ ዘርፍ የኦኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሃገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ ቢደረግም፤ ባለሃብቱ ሊሰማራባቸው በማይችላቸው ዘርፎች መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ልማቱን በዋነኝነት በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

እነዚህ ድምር ውጤቶች የሀገራችን መፃዒ ዕድል አመላካች ይመስሉኛል። መንግስት የሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ያሳደገና የስራ ዕድል የፈጠረ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት እንደ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ሁሉ ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማምጣት የሚችሉ የውጭ ባለሃብቶችም ወደ ሀገራችን እንዲተሙ አድርጓቸዋል።

ታዲያ ይህ በጎ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳይደናቀፍ በመንግስት ፈፃሚዎች በኩል ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። በተለያዩ ወቅቶች የውጭ ባለሃብቶች የሚያሰሙትና ሆን ተብሎ በአስፈፃሚዎች የሚፈፀም የሚመስሉ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን ማስቀረት ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎንም በኢንቬስትመንት ስም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ምንም ዓይነት እሴት መጨመር ያልቻሉ ባላሀብቶችን ሚዛኑን በጠበቀና ፍሰቱን በማያስተጓጉል መልኩ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል።

በአጠቃላይ የሚመለከታቸው አካላትና ሥርዓቱ ያፈራቸው ባለሃብቶች በአሁኑ ወቅት የውጭ ኢንቨስትመንትንና የኢንቬስተሮችን ቀልብ መሳብ የቻለውን የሀገራችንን ተመራጭ የኢንቨስትመንት ፖሊሲን በመከተል ተጨማሪ ፍሰት በመፍጠር ያለባቸው ይመስለኛል።

በአሁኑ ወቅት መንግስትና ህዝብ ባካሄዱት ከፍተኛ ጥረት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡ በዚህም ከሰሃራ በታች ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት በአምስተኛ ደረጃ፣ የነዳጅ ምርት ከሌላቸው ሀገሮች ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ኢትዮጵያ፤ የበርካታ ኢንቬስተሮችን ቀልብ በመሳብ ላይ ትገኛለች።

ይህን አባባሌን ሊደግፉ የሚችሉ ቀደም ያሉና የቅርብ ተጠቃሾችን ላንሳ። ባለፉት ጊዜያት የሀገራችንን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙት የቻይና፣ የቱርክ፣ የህንድ፣ የአውሮፓ፣ የአረብ ሀገሮች ትልልቅ ኩባንያዎችና ባለ ሃብቶች ይገኛሉ።

ኢትዮጰያ ውስጥ እንደ እነ ሳምሰንግ፣ በጂኦተርማል ሃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ላይ ለመሰማራት በዝግጅት ላይ የሚገኘው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ፣ በማዕድን ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት የካናዳና የአወስትራሊያ ኩባንያዎችና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ኢንቨስተሮች በመበራከታቸው አሳማኝ አስረጅ ናቸው።  ይህም ኢትዮጵያ የኢንቬስተሮች መዳረሻ መሆኗን ያሳያል።

የሀገራችን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳርና ፖሊሲ አብዛኛዎች የዓለማችን ሀገራት ዓይናቸውን እንዲጥሉባት ያደረገ ነው። ይህ ፖሊሲ ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ወደፊትም ባላሃብቶችን ይበልጥ መሳብ ይኖርብናል።