Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኤርትራ መንግስትና ወላዋይ ባህሪው

0 464

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኤርትራ መንግስትና ወላዋይ ባህሪው

                                                        ቶሎሳ ኡርጌሳ

የባህረ ሰላጤው ሀገራት ውዝግብ ሻዕቢያ በተፈጥሮው “የታደለውን” የወላዋይነት ባህሪውን ለዓለም አጋልጦበታል። ርግጥ የኤርትራ መንግስት ትናንት ያልነበረውን ባህሪ ዛሬ መሬት ምሶና ተራራ ገምሶ ሊያመጣው አይችልም። ወትሮም ቢሆን ወላዋይነት፣ ሐሰት መናገር፣ ጥገኝነትና ጦረኝነት የሻዕቢያ አንጡራ ሐብቶች ናቸው። ዛሬም እኚህ ባህሪዎቹ አብረውት አሉ። አንዴ በምስራቅ፣ ሌላ ጊዜ በምዕራብ፣ በል ሲለው ደግሞ በደቡብ በኩል አሊያም፤ በመሰለው ጊዜና ቦታ በአንቀልባ አዝሏቸው ይዞራል። ከራሱ አይነጥላቸውም።

የአቶ ኢሳያስ መንግስት ወጥ አቋም የሌለው በመሆኑ መርህን ሳይሆን ጥቅም ወዳለበት ቦታ ይሮጣል። የትም ቢሆን ጊዜያዊ የጥገኝነት ሱሱን እስከተወጣለት ድረስ ከማንም ጋር ሽርክ ይሆናል። ሰይጣንም ከቀይ ባህር ወጥቶ ‘አብረን እንስራ’ ቢለውም የሁከት ፅዋውን አንስቶ “ቺርስ” ብሎ ስምምነቱን የሚገልፅ ይመስለኛል። በአጭሩ ሻዕቢያ ለሰጠው ሁሉ አፋሽ አጎንባሽ ነው ማለት ይቻላል።

የኤርትራ መንግስት ቀደም ሲል ከኳታር መንግስት ጋር የነበረውን ግንኙነት ዛሬ ላይ የሚያስታውሰው አይመስልም። ኧረ እንዲያውም ከአዕምሮው ጓዳ ፍቆ ሳያወጣው የቀረ አይመስለኝም። ግና ታሪክ ነውና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግስትና የኳታርን ግንኙነት መናገር የግድ ይለኛል። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ይህን የምለው የኤርትራ መንግስት ሰናይ ስብዕና ያለው ሆኖ ሲያበቃ፤ እኔ በመጥፎነቱ እየሳልኩት አይደለም። በሌላው ዘውግም የምቀባባው ነገር አይኖርም። የነበረውንና ያለውን ዕውነታ በመረጃ እያስደገፍኩ ብቻ ነው የምገልፀው። ሲጀመር የአስመራው አስተዳደር ምንም ዓይነት ሰናይ ምግባር የለውም እንጂ ቢኖረው እዚህ ላይ ማስፈሬም አይቀርም ነበር።

ግና ትናንት ከዶሃ መንግስት ጋር እፍ…ክንፍ ሲል የነበረው ሻዕቢያ፣ ዛሬ ደግሞ አዲስ ለምድ ለብሶ ከሳዑዲ አረቢያና ከአረብ ኢምሬትስና ከግብፅ ጋር የ“አንለያይም” ነጠላ ዜማን እየዘፈነ ነው። “ቤቴ ቤታችሁ ነው” በማለት የጦር ሰፈር ሰጥቶ “አሸሼ ገዳሜ…መቼ ነው ቅዳሜ” እያለም ነው። “ቅዳሜውም” ከመሰንበቻው ሆኖ ነው መሰል፤ ከስምንት ዓመት በፊት የኳታርን መንግስትና ልዑሉን ሃሚድ ቢን ጃስሚንን “አፈር አይንካችሁ” እንዳላለ፣ በተለይም ልዑል ቢን ጃስሚንን “ወንድማችን ያውቃሉ” እያለ የችግሩ ሁሉ መፍቻ ቁልፍ እንዳላደረጋቸው፤ ዛሬ በሚታወቀው የማይጨበጥ ተለዋዋጭ ባህሪው እየተመራ ፊቱን ወደ ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው ሀገራት አዙሯል። በአፍላ ስሜታዊ ፍቅር ከንፎም ከኳታር ጋር የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ አቋርጧል። ርግጥ በመርህ አሰራር መመራት ምኑም ላልሆነው ሻዕቢያ፤ በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ዥዋዥዌ ውስጥ መገኘቱ የሚገርም አይደለም። ነገ ደግሞ ወደ ኳታር ፊቱን አዙሮ እነ ሳዑዲ አረቢያን ‘ዞር በሉ’ እንደማይል ማንም ማረጋገጫ ሊሰጥ አይችልምና።

ያም ሆኖ ግን በእኔ እምነት ሻዕቢያ ትናንትን መዘንጋት አልነበረበትም። ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት እንዲህ ሆነ።…110 ኪሎ ሜትር ከኤርትራ ጋር ድንበር የምትጋራው ጂቡቲ በአንድ ምሽት እንዲህ አለች—“ኤርትራ ሉዓላዊ ግዛቴን ጥሳ በመግባት ወረረችኝ”።…ለሊቱ ሳይነጋ በዚያው ምሽት የሻዕቢያ ወታደሮች የጅቡቲ ግዛት የሆነውን የራስ ዱሜራ ኮረብታዎችና ሐይቆችን እንደያዙ ተሰማ። ይህ የራስ ዱሜራ የጠረፍ ግዛት መላውን የባብኤል መንደብን እንዲሁም በቀይ ባህር ላይ የሚመላለሱ መርከቦችን ለማየት የሚያስችል ስትራቴጂክ ቦታ መሆኑ ይነገርለታል። ይህን ቦታ መያዝ ምናልባትም የሻዕቢያ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም።

ያም ሆኖ ወዲያውኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኤርትራ መንግስት ቀጥተኛ ወረራ የተካሄደባቸውን ሀገራት ሲቆጥር በርከት አሉበት። በሃኒሽ ደሴት ይገባኛል የመንን፣ በባድመና አካባቢዋ “የእኔ ነው” ባይነት ኢትዮጵያን፣ በራስ ዱሜራ ጉዳይም ጂቡቲን እንደወረረ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድ ወሳኝ ጥያቄ አነሳ — “የኤርትራ ወታደሮች በራስ ዱሜራ ኮረብታዎች ላይ ምን እየሰሩ ነው?” የሚል። ተወራሪዋ ሀገርም “የኤርትራ ወታደሮች ‘ለመንገድ መስሪያ የሚሆን አሸዋ ለመውሰድ ነው’ በሚል ራስ ዱሜራ ከገቡ በኋላ አንወጣም አሉ” ስትል ምላሽ ሰጠች።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ሐሰት መናገር በኤርትራ መንግስት አሰራር በመርህ ደረጃ “ትክክል” ስለሆነ፤ የአስመራው አስተዳደር ወዲያውኑ መግለጫ አወጣ። ኤርትራ የወረረችው መሬት እንደሌለና “ይህን የሚያስወሩት ጠላቶቻችን ናቸው” ሲሉም ገለፁ። እንዳልኩት ተለዋዋጭ በሆነ ስሜት እንጂ በመርህ የማይመራው የኤርትራ መንግስት ለአንድ ቀን ፍጆታ የሚጠቅመው ቢሆንም እንኳን መዋሸትን እንደ ነውር የሚቆጥር አይደለም። ታዲያ በወቅቱ ከሳምንት ቆይታ በኋላ የአስመራው አስተዳደር “ከጅቡቲ ጋር ባለው ግንኙነት የኤርትራ አቋም” በሚል ርዕስ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት “በሁለቱ ሀገራት መካከል የድንበር ችግር መኖሩን አናውቅም” ሲል ምላሽ ሰጠ። የፀጥታው ምክር ቤት ለኤርትራ መንግስት ደብዳቤ የሰጠው ምላሽ ግን ማሳሰቢያ ነበር— በውሳኔ ቁጥር 1862 ‘ኤርትራ ከጅቡቲ ግዛት በአስቸኳይ እንድትወጣ’ አሳሰበ። ሻዕቢያ ግን ከራስ ዱሜራ ግዛት አልወጣም ብሎ ቀረ። የኋላ ኋላም የኤርትራ መንግስት ጅቡቲን ወርሮ በመያዙ፣ ሶማሊያ ውስጥ ጽንፈኛ ኃይሎችን በመደገፉና ለአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት መንስኤ በመሆኑ የፀጥታው ምክር ቤት በውሣኔ ቁጥር 19ዐ7 የጉዞ እንዲሁም የገንዘብ ማዕቀብና እገዳ ጥሎበታል።  

ይህም ሆኖ ዲፕሎማሲው ተጠናከሮ ነበር። እውነታውን የሚያውቁት ኢጋድ፣ አረብ ሊግና አፍሪካ ህብረት የኤርትራን መንግስት ቢመክሩና ቢዘክሩ ሰሚ አላገኙም። በተለያዩ ቀጣናዊ ትርምሶች ተግባሩ የሚታወቀውና ቀደም ሲል የሁለት ወረራዎች የስራ ልምድ ተሞክሮ ያሉት የአስመራው አስተዳደር በምክር የሚመለስ ሆኖ አልተገኘም። እንዲያውም ከቁብ አልቆጠረውም ማለት ይቻላል። የኤርትራ መንግስት በጦር ሰባቂ ባህሪው እየተመራም በአስገራሚ ሁኔታ “ራስ ዱሜራ የሚባል ቦታን አናውቅም” አለ። ይህም በጂቡቲና በኤርትራ መካከል ጦርነት እንዲካሄድና በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰው ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል።

ታዲያ በዚያ ወቅት ለኤርትራ ችግር የነበረውን ሁኔታ የቀለበሰችው የዛሬዋ በባላንጣነት የተፈረጀችው ኳታር ነበረች። ኳታር ጂቡቲንና ኤርትራን የሚያጨቃጭቀውን የራስ ዱሜራ ኮረብታዎችንና ሐይቆችን የራሷን 400 ወታደሮች በማሰገባት “አንተም ተው፣ አንቺም ተይ” ስትል አሸማጋይ ሆነች። አንዳንድ ወገኖች የኳታር መንግስት “የቼክ ዲፕሎማሲ”ን (Check diplomacy) በመጠቀም ለተከራካሪ ወገኖች ገንዘብ በመስጠት ቦታውን ይዟል ይላሉ። በአንዳንድ ተንታኞች “የጦርነት ኢኮኖሚን መርህን ይከተላል” ለሚባለው የኤርትራ መንግስት ይህ የኳታር መንገድ ጮቤ የሚያስረግጥ ነበር። የጥገኝነት ፍላጎቱን ለማሟላትም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት የሚገልፁት በርካታ ናቸው። እናም ኳታር ከራሷ ፍላጎት አኳያ ራስ ዱሜራ ላይ ብትቆይም፣ በወቅቱ የሻዕቢያን ኢኮኖሚ የቁልቁለት ጉዞን በጠጠር የመደገፍ ያህል ቢሆንም ድጋፍ ማድረጉ የሚካድ አይደለም።

ርግጥ የአስመራው አስተዳደር መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ከኳታር ጋር የነበራቸው ግንኙነት ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ ጉንፋን እንኳን ሲይዛቸው ለህክምና ቅድሚያ የሚመርጧት ሀገር ኳታርን ነበር—የዛሬን አያድርገውና። ዛሬማ… ሻዕቢያ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው፣ ከኳታር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን የገለፁትና በአሁኑ ወቅት ‘ለሌላ ማዕቀብ ተዘጋጅተናል’ እያሉ ከሚገኙት የአረብ ሀገራት ጋር እጅና ጓንት ሆነዋል። አቶ ኢሳያስና አስተዳደራቸው ፊታቸውን አዙረው ሀገራቱ ሲያስነጥሳቸው መሃረብ ይዘው በመቅረብ ‘እኔን!…እኔን!…አላህ ይማራችሁ!’ ባይ ሆነዋል። ይገርማል! ያስደንቃል!

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ አፍሪካ ህብረትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በባህረ ሰላጤው ሀገራት መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ ውዝግብ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ እያቀረቡ ባሉበት በዚህ ወቅት፤ የኤርትራ መንግስት የአንድ ጎራ ዘማሪ ሆኖ መታየቱ ሻዕቢያ ዛሬም ከሁከትና ከብጥብጥ ለማትረፍ ያለውን ፍላጎት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሆኗል። ምን ያህል ጥሬ በሆነ የፖለቲካ መንገድ ላይ እየተራመደ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑም እንዲሁ።

ያም ሆኖ ላለፉት ስምንት ዓመታት ራስ ዱሜራ ላይ ወታደሮቹን አስፍሮ የነበረው የዶሃ መንግስት ሻዕቢያ ከሀገሪቱ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እስካቋረጠበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እዚያው ከትሞ ነበር። ሳዑዲ አረቢያ ከምትመራው የባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር በገባው እሰጥ-አገባና የኤርትራ መንግስት ባለው ወላዋይ ባህሪው ፊቱን ስላዞረበት ለስምንት ዓመት የነበረበትን ራስ ዱሜራን ሰሞኑን ለቆ ለመውጣት ተገድዷል። በአሁኑ ወቅት ቦታውን የኤርትራ መንግስት ወታደሮች ተቆጣጥረውታል።  

ታዲያ አሁንም እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር ውሸትን በመደበኛ አሰራር የሚጠቀመው ሻዕቢያ “ኳታር ለምን ወታደሮቿን ከራስ ዱሜራ እንዳስወጣች አላወቅንም” ማለቱ ነው። ይህም የኤርትራ መንግስት ለየትኛውም ዓይነት ተግባሮቹ የሚሰጠው ምላሽ አንድና ተመሳሳይ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ቀልድ ቢባልም የሚያስኬድ ይመስለኛል። ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት ልዑካኑን ወደ ራስ ዱሜራ በቅርቡ ልዑካኖቹን ይልካል ተብሎ ስለሚጠበቅ እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅትም በጉዳዩ ዙሪያ እየመከረበት መሆኑ የሚያሳየው ነገር በሁለቱ ሀገራት መካከል ውዝግብ መኖሩን የሚያሳይ ስለሆነ ነው።  ያም ሆኖ ግን በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የምትመራው ኤርትራ ለሁሉም ችግሮቿ የምትሰጠው ምላሽ አንድ ዓይነት መሆኑ እምብዛም የሚገርም አይደለም።

እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ አመራር የሚመራ በመሆኑ ሁሉም ነገሮች በእርሳቸው ፍላጎት የሚመራ ነው። ተደጋግሞ እንደሚገለፀው እርሳቸው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከመሆናቸውም በላይ የሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ስራ የሚሰሩ ናቸው። ምናልባትም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳያውቁት እርሳቸው በጎረቤት ሀገር ላይ ወረራ ሊያካሂዱም ይችላሉ። በቃ! በዚያች ትንሽዬና የህዝብ ብዛቷ ስድስት ሚሊዮን ህዝብ እንደሆነ በሚነገርላት ሀገር ውስጥ አቶ ኢሳያስ ሁሉም ነገር ናቸው። መሪውም፣ ፖሊሱም፣ ዳኛውም፣ የጦር አዛዡም፣ የማስታወቂያውም ይሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣…ሌላ… ሌላውም አቶ ኢሳያስ ናቸው። የእርሳቸው ባህሪ የመንግስታቸውን ተግባራት እየወሰነ ላለፉት 26 ዓመታት ዘልቀዋል። የእርሳቸው: የድርጅታቸው ህግደፍና የመንግስታቸው እሳቤዎች የአንድ ሳንቲም ሶስት ገፅታዎች ሆነው ከባቢውን እያተረማመሱት ነው።

የሻዕቢያ ወላዋይ ባህሪ በፖለቲካው መስክ እንደሚታየው ዓይነት አይደለም። የኤርትራ መንግስት በባህሪው ሁሉንም ሀገራት በጥርጣሬ የሚፈርጅ ነው። የሚመራበት ወጥ አሰራርና መርህ ባለመኖሩ ዛሬ ወዳጁ የነበረውን ነገ ጠላቱ ለማድረግ ምንም ዓይነት ጊዜ አይፈጅበትም። መንግስት ከሆነ በኋላ ከኢትዮጵያ: ከየመንና ከጂቡቲ ጋር በወዳጅነት መዝለቅ የቻለው ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነው። እናም የኤርትራ መንግስት ወላዋይ ባህሪውን መቼም ቢሆን ይተዋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ባህሪውም ‘ነገ ይህን ሊፈፅም ይችላል’ ተብሎ እንዲገመት የሚያስችል ባለመሆኑ፤ የቀጣናው ሀገራት: የአፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቅርብ ክትትል ሊያደርጉ የሚገባ ይመስለኛል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy