Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ፣

0 1,622

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም
አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ፣
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰፊ ውይይት ካካሄዱበት በኋላ በተወካዮቻቸው አማካይነት ያፀደቁት ህገ-መንግሥት የሁሉንም ሕዝቦች መብቶችና ጥቅምች የሚያስጠብቅ ነው፡፡
ህገ-መንግሥቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቃል-ኪዳን ሰነድ ሲሆን ዓላማውም በሕዝቦች መፈቃቀድና ፍላጎት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጎልበት እንዲቻል በጋራ ያፈሯቸው እሴቶችና ሃብቶች እንዲሁም ትስስሮች እንዳሏቸው በማመን- በታሪካቸው ሂደት ውስጥ ያጎለበቷቸውን የጋራ ጉዳዮች ይበልጥ ለማበልፀግና የተዛቡ ግንኙነቶችንም በማረም አንድ ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እና የጋራ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባትና ለማጠናከር የታለመ ነው፡፡
ይህንን በማድረግም በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሠፍንና ፈጣንና ህዝቡ በየደረጀው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን በራሳቸው ፈቃድና በፍላጎታቸው የመረጡት መሆኑን በፅኑ የሚያምኑበት ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ልዩ ጥቅም በህገ-መንግሥቱ እንዲሰፍር ያደረጉት የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ መላው የሀገራችን ሕዝቦች ናቸው፡፡ የመረጡት የፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የፌደራል መንግሥትና የክልሎች መንግስታት እንደሚኖሩ የሚደነግግ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነች ከተማ መመረጥ ስለነበረበትም የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ መላው የሀገራችን ህዝባች በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ ያለችውን አዲስ አበባ ከተማን የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ አድርጎ መርጧታል፡፡ ይህም በህገ መንግሥቱ እንዲሰፍር አድርገዋል፡፡
ይህንን ውሣኔያቸውን መሠረት በማድረግም በህገ-መንግቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀስ 5 ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፡-
“ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” በማለት ደንግጓል፡፡
ይህንን የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ የቃል-ኪዳን ሠነዳቸው ያሰፈሩትን ጉዳይ በዝርዝር ሕግ መመለስ የሚያስፈልግ በመሆኑ የሕገ-መንግሥቱን መንፈስ ተከትሎ ዝርዝሩ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ ዝርዝሩን ለመሥራት ግብዓት እንዲሆን በክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድና በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በፌዴራል ደረጃ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተው በመጨረሻ በኢህአዴግ ሥራ-አስፈጻሚ ደረጃ በዝርዝር ታይቶ የመንግሥት ህጋዊ ተቋማት መክረውባቸው ህግ-ሆኖ እንዲወጣ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በዚህም መሠረት የኢፌዲሪ የሚንስትሮች ም/ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት የሚከተሉትን ጉዳዮች ተመልክቶ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መክሮበት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ አስተላልፉዋል፡፡
ህገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5 ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች
1ኛ/ ከአገልግሎት አቅርቦት ልዩ ጥቅም አኳያ፣
2ኛ/ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ልዩ ጥቅሞች አኳያ፣
3ኛ/ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ
የኦሮሚያ ክልል ያለው ልዩ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲቀረፁና እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
የህገ-መንግሥቱ ዋና ማነሻም አንድ ጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው ጥረት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ የምትገኝ ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሦስተኛ ማዕከል የሆነች፣ የአፍሪካውያን የፖለቲካና ዲፕለማሲ መዲና የሆነች መሆኗንም ታሣቢ በማድረግና እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሐሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው ፈቃድና በፍላጎታቸው የመሠረቱት የፌዴራል ስርዓት ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫና ሕገ-መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በሽግግር ወቅትም የክልል 4 ዋና መዲና እንዲሁም ህገ-መንግሥቱ ከፀደቀም በኋላ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ሆና እየገለገለች ያለች ናት፡፡
ከዚህም ተነስቶ አዲስ አበባ እነዚህን የዓለምአቀፍ፣ የአህጉራዊ እንዲሁም የሀገራዊ ከዚያም አልፎ በፌዴራል ሥርዓታችን መሠረት የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም አካቶ የያዙ ሃላፊነቶችን መወጣት ያለባት ከተማ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅ የሚወጣው ህግም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪያዎችን መብቶችና ጠቅሞች በምንም መልኩ የማይሸራርፍ ይልቁንም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በመጠበቁ ምክንያት የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕዝብና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ትስስርና መስተጋብር ይበልጥ ህጋዊ መሥመር ይዞ እንዲጠናከር የሚያደርግና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ይሆናል፡፡ የከተማዋና የክልሉ የመንግሥት አካላትና ነዋሪ ሕዝቦችም ዘላቂ ያለው ሰላም እንዲሰፍን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት እንዲሁም ፈጣንና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል፡፡

1ኛ/ የአገልግሎት አቅርቦት ጉዳዮችን በተመለከተ በማህበራዊ አገልግሎቶች ልዩ ጥቅም ማለትም ከትምህርት አኳያ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የአርሦአደሩ ልጆችን እንዲሁም አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ ምክንያት ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ ዜጎች የከተማ አስተዳደሩ በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ማደራጀት እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ላይ ያለው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ አብዛኛውን አገልግሎቱን በተለይም የሆስፒታል አገልግሎቶችን ከከተማዋ የሚያገኝ በመሆኑ በኦሮሚያ እምብርት ላይ የተቆረቆረች ይህች ከተማ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በእቅዷ ውስጥ ማካተት ይኖርባታል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ከማህበራዊ አገልግሎቶች የሚመደበው ሌላው የባሕል፣ የቋንቋና የሥነጥበብ አገልግሎቶች ሲሆን ከዚህ አኳያም የማህበራዊም ሆነ የኢኮኖሚ አገልግሎቶች ለማቅረብ እንዲቻል ልዩ ጥቅሙን ለማስጠበቅ በዚህ አዋጅ መሠረት አገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በቋንቋቸው አገልግሎቱ እንዲቀርብ አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ የሚያገልግል ይሆናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy