NEWS

የኦሮሚያ ክልል ከ 1 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ

By Admin

June 22, 2017

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የታየባቸው ከ1 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለጸ፡፡

በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከቢሮው ጀምሮ እስከ ወረዳ ባሉ የጤና ተቋማት፥ በተደረገ ግምገማ ችግር ያለባቸውን አመራሮችና ባለሙያዎች በመለየት እርምጃ ተወስዷል።

ባለፉት አራት ወራት ከ1 ሺህ የሚበልጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና የጤና ባለሙያዎች ላይ፥ ከቦታ ማንሳት ጀምሮ የሙያ ዲሲፕሊን ቅጣት፣ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የየክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስታውቀዋል።

እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት፥ በአገልግሎት አሰጣጥ ህዝብን ያማረሩ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት፣ የሙያዊ የስነ ምግባር ጉድለት፣ የመድሃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አቅርቦትና የጥራት ችግሮች የክልሉ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ የሚፈለገውን ያህል እንዳይሆን ማድረጋቸውን ዶክተር ደረጀ ጠቁመዋል፡፡

እየተወሰደ ካለው የማስተካከያ እርምጃ ጎን ለጎን በነባር የጤና ተቋማት የሚታየውን የቁሳቁስ ችግር ለመፍታትና አዳዲሶቹን ስራ ለማስጀመር ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ ተግባራት ተከናውኗል፡፡

በተለይ 10 አዲስ የመጀመሪያ ደረጃና ሪፈራል ሆስፒታሎችን በውስጥ ቁሳቁስና በሰው ሃይል በማደራጀት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ነባር ጤና ተቋማትንም በመድሃኒት፣ በህክምና መሳሪያና የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ምንጭ፡-ኢዜአ