Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን በመድፈቅ

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን በመድፈቅ

ወንድይራድ ኃብተየስ

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 26 ዓመታት የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ፈርጀ ብዙ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። መልካም አስተዳደርን ከማስፈን፣ ፍትህን ከማረጋገጥና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመድፈቅ አንፃር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የተመዘገበውን ልማት ለማስቀጠል እና የተጀመረውን የሠላምና የህዳሴ ጉዞ ለማቀጣጠል ከመቼውም በላቀ ቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል።  

ለዚህም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም፤ ልማታዊነትን ለማጠናከርና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን  የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር፤ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ብሎም ብልሹ አሠራርን የማይሸከምና ሙስናን የሚጠየፍ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ትርጉም ያለው ርብርብ ማድረግ የግድ ይላል።

መልካም አስተዳደር የሚጀምረው አብላጫው ህዝብ ድምጹን በሰጠው ፓርቲ ሲተዳደርና አሸናፊውም የገባውን ቃል ሲያጥፍ ሊያወርደው እንደሚችል መተማመኛ ሲያገኝ ነው። በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከተዘረጋ   ሁለት  አሥርት ዓመታት አልፈዋል።

 

በአገሪቱ የተፈጠረውን ይህን ምቹና ሰፊ  የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀምም ቁጥራችው ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ባለፉት ጊዜያት በየአምስት ዓመቱ በተካሄዱ ምርጫዎች እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች የነበራቸው ተሳትፎ የጎላ እንደነበር እሙን ነው።

 

ይህ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሲጠናከር መልካም አስተዳደር ጎን ለጎን እየተጠናከረ የሚመጣበት ዕድል ሰፊ ነው። ባለፉት ዓመታት የነበረው ተሞክሮም በርካታ ውጣ ውረዶች ያጋጠሙት ነበር። ሂደቱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። ሆኖም የህዝቦችን መብትና እኩልነት ያረጋገጠውና ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ ድርጅት ያለምንም ተጽዕኖ ተደራጅተው እንዲሳተፉ ሙሉ ነጻነታቸውን ያጎናፀፈውና የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመናድ ያለመ እንቅስቃሴ ሲፈፀም የነበረበት ሁኔታም እንደታለፈ ይታወሳል። በጎ ሁኔታዎችን የፈጠረላቸውንና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ያስቻላቸውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አክብረው መጓዝና የፖለቲካ አጀንዳቸውን በሕዝብ ዘንድ በማስረፅ  በምርጫ አሸንፈው ወደ ኃላፊነት ለመብቃት ቀና መንገድን ከመከተል ይልቅ ይህ ነው የሚባል አጀንዳ ሳይዙ በሕዝቡ መካከል ሁከትና ትርምስን በመፍጠር በግርግር  ለመጠቀም የሚያልሙ ተቃዋሚ የፖለቲካ  ድርጅቶች ሕገ መንግሥቱን ሲተላለፉ ተስተውለዋል።

 

በቀደሙት ዓመታት በአገሪቱ አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያራምዷቸው ሕጋዊነት የጎደላቸው ተግባራት ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዴሞክራሲ ግንባታ መጎልበት በተግዳሮትነት የሚወሰዱ ለመሆናቸው አያጠራጥርም። እነዚህ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በሥጋትነት የሚጠቀሱ  እንደነበሩ ይታወሳል። በተለይም አገራችን የምታካሂዳቸውን ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጣጣልና ተገቢ ያልሆነና የተዛቡ አስተያየቶችን በመስጠት የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነትን ሊፈታተኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የሚተላለፉ ውሣኔዎችን በመቃወምና ከአገሪቱ የውጭ ጠላቶች ጋር በማበርና በመተጋገዝ የተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ መስተዋላቸው ያስተዛዝባል።  

 

ሌላው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረትን በመናድ የልማታዊ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በገጠር የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት ለመናድ የተለያዩ  ርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወቃል። የኢሕአዴግ መንግሥት ሰው በላውን የደርግ ሥርዓት ገርስሶ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት በከተማም ሆነ በገጠር የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የተንሰራፋበትና ልማታዊ አስተሳሰብ የሚባል ነገር ያልታየበት ሁኔታ ነበር።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በገጠር የመሬት ክፍፍል የተደረገና አርሶ አደሩ መሬት ያገኘበት ሁኔታ ቢኖርም አንዳንድ የፍትሃዊነት ችግሮችን የማስተካከል ሥራ ተከናውኗል። ክፍፍሉ በተገቢው መልክ ባልተደረገባቸው አንዳንድ አካባቢም የማስተካከያ ሥራዎች የተከናወነበት ሁኔታ ነበር።

 

ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ በአርሶ አደሩ የነበረ ኋላ ቀር አስተሳሰብን ለመቅረፍ ያላሳለሰ ጥረት ተደርጓል። አርሶ አደሩ በላቡ ሰርቶ ጥሮና ግሮ አኗኗሩን መቀየር የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸትና የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወነው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው። በዚህም በገጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ዋስትና ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻ ለመወጣት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ለመዝጋት የተደረገው ጥረትም ለዚህ ውጤታማነት አጓዥ ሚና እንደነበረው ለማየት ይቻላል።   

 

ዛሬ ላይ አርሶ አደሩ በተሰጠው የእርሻ ቦታ የራሱንና የቤተሰቡን ላብ አፍስሶና በመንግሥት ከሚመደቡ ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እያገኘ ሰርቶ ከድህነት እንደሚላቀቅ በተግባር መገንዘብ ችሏል። ልማታዊነቱም እያደገ በመጣ ቁጥር በገጠር የኪራይ ሰብሳቢነት መሠረቱ እየተናደ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስትርነት የተቀየሩ ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በገጠር ሞዴል አርሶ አደሮች ሌላውን እየመሩና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመሰባሰብ ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው በመነሳት ልማታቸውን እያረጋገጡ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት መናድ ሌላው ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

 

በዚህ መልክ ልማታዊነት እየተረጋገጠና ኪራይ ሰብሳቢነትን ነቅሎ ለመጣል ትንቅንቁ ቀጥሏል። በከተማም በተመሳሳይ መልኩ የኪራይ ሰብሳቢነትን የበላይነት ለመድፈቅና ልማታዊነትን ለማንገስ ቀላል የማይባል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

 

እንደ መሬት፣ የመንግሥት ግዥ፣ ግብርና ንግድ የመሳሰሉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ምንጭ ተደርገው የሚወሰዱ ዘርፎች ተለይተው ታውቀዋል። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና ልማታዊነትን ለማጠናከር መልካም አስተዳደርን ማስፈን አማራጭ  የሌለው ተግባር ነው። መልካም አስተዳደርን ማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነትን አንድ መንገድ መዝጋትና የአገሪቱን ልማት ማፋጠን መሆኑን የተገነዘበው የኡትዮጵያ መንግስት ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር የአንድ ጀምበር ተግባር አይደለም። ጊዜን የሚጠይቅና በሂደቶች የሚከወን እንደሆነ ይታወቃል።

 

በኢትዮጵያ የፖለቲካል  ኢኮኖሚ ዕድገት የሚወሰነውንና በየጊዜው መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር ክንዋኔን በአንድ ጀምበር እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉ አንዳንድ ወገኖች መልካም አስተዳደር በአገሪቱ የለም እያሉ በተደጋጋሚ  ከማስተጋባትም ባሻገር የተለያዩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በማምጣትና በአገሪቱ የተረጋገጠውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማያግዝና ለማጠናከር በማይጠቅም መልክ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።  


ይሁንና መንግሥት በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር ልማታዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው ሚናና የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ የያዘው ጉዳይ ነው። መልካም አስተዳደር የህልውና ጉዳይ ነው። ምክንያቱም መልካም አስተዳደርን ማስፈን ካልተቻላ ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቆ ልማታዊነትን ማረጋገጥ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ አለውና።

 

የመልካም አስተዳደር ትግበራ የአገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕለታዊ ህይወት በቀጥታ የሚነካ በመሆኑ ጭምር በአተገባበሩ ዙሪያ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ መጠነ ሰፊ ተግባራዊ ክንዋኔዎች ተደርገው አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መጥተዋል። ይህም ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል። የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን በመድፈቅ ልማታዊ መንግሥትን የማጎልበት ሂደቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy