Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የውጭ ኢንቨስትመንት ማእከል

0 525

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የውጭ ኢንቨስትመንት ማእከል

ዮናስ

 

ኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለኃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጓን ተያይዛዋለች። ይህንኑ ተከትሎ ታዲያ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡና ይልቁንም ወሳኝ በሆነው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአለማችን ሃገራት ቁንጮው ላይ የተቀመጠችው  ጃፓን ባለሃብቶቿ ፊታቸውን ወደዚህችው ሃገር ኢንዲያዞሩ የመከረች ሲሆን ሃገሪቱን ሲያጠኑና ሲያጤኑ የነበሩ በርካታ ጃፓናውያን ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት እንደሚፈልጉ ከሰሞኑ አረጋግጠዋል።

በዘንድሮው የበጀት ዓመት አንዳንድ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ መረጋጋት የራቃት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የምትተዳደር አገር አድርገው በማቅረብ የአገሪቱ ኢኮኖሚ  ከፍተኛ  ተግዳሮት እንደተጋረጠበት አድርገው ሲያቀርቡ  ነበር። ይሁንና በተጨባጭ የታየው ግን ኢትዮጵያ  በዘንድሮው ዓመት አገሪቱ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። በርካታ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ላይ ለመሆኗም ከላይ የተመለከተውን ጨምሮ በርካታ ማረጋገጫዎች ማቅረብና እንደዜጋ እውነታውን በመግለት ሌሎቹንም ማንቃት የዚህ ተረክ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

በአገራችን የውስጥም ሆነ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) በመስፋፋት ላይ ነው ብለን መስፋፋቱን የሚያጠይቁ አስረጂዎች ወደመጥቀስ ከመሻገራችን በፊት አገራችንን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ካደረጓት እና የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ማእከል እንድትሆን ካደረጓት ነገሮች  መካከል  የተወሰኑትን እና ወሳኝ የሆኑትን መጀመሪያ ብናነሳ ምክንያታዊ ያደርገናል።

ዋስትና ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት መዘርጋቱና ዘላቂ ሰላም መስፈኑ የመጀመሪያውና መሰረታዊው ነው። ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች  ጽንፈኛ አካሎች በርካታ ኢንቨስትመንቶች ላይ ጉዳት ቢያደረሱም መንግስት ለባለሃብቶች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ማድረጉም ሌላኛውና መተማመንን የፈጠረ ምክንያት ነው። ይህ የመንግስት አካሄድ ባለሃብቶች በመንግስትና ህዝብ ላይ ያላቸውን ጽኑ ዕምነት እንዲያጎለብቱ አድርጓቸዋል። በያዝነው ዓመት ብቻ  በርካታ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደአገራችን ከመምጣታቸው ባሻገር ነባር ኢንቨስትመንቶችም  በመስፋፋት  ላይ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ ግልጽና ሳቢ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ያላት አገር  በመሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አገር ለመሆን በቅታለች። መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ  በመላ አገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስፋት በመገንባት ላይ ይገኛል። በመንግስት ወጪ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሟላ መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው በመደረጋቸው ባለሃብቶች በአጭር ጊዜና በቀላል ወጪ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ያስቻለ መሆኑ ጥቂቶቹ ግን ደግሞ ወሳኞቹ ምክንያቶች ናቸው። በቂ መነሻ ይሆነናልና አሁን ወደ አስረጂዎቻችን ብንሻገር የሚያስማማን ይሆናል። መነሻችንንም ከላይ ከመግቢያው በተመለከተው አግባብ ከጃፓን ልናደርግ ግድ ይለናልና ወደዚያው እንሻገር ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካትሱሚ ሂራኖ የሚመራውን ልዑክ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን ሰምተናል። ንግግራቸውም ሁለቱ አገሮች ጃፓናውያን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ  ይበልጥ በሚያጎለብቱበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ካትሱሚ ሂራኖ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያመቻቸውን አጋጣሚ በመጠቀም የጃፓን ባለኃብቶች በአገሪቷ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት ይፈልጋሉ። ባለሃብቶቹ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት እንዲችሉ የሚያነሳሳ መሆኑን በተመለከተ እኚህ የልኡኩ መሪ ሲናገሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ክፍልና የሞጆን ደረቅ ወደብ አስተማማኝ አገልግሎት በቀዳሚነት ጠቅሰዋል።

እሳቸው እነዚህን ተቋማት በዋናነት ያንሱ እንጂ በኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን አግባብ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት ለሚፈልጉ ጃፓናውያን ባለሃብቶችም መንግሥት አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ  አረጋግጠዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲው እንደሚገልጸውም ሆነ በዚሁ መሰረት ያሳለፍናቸውን 12 ዓመታት ባስመዘገብነው ተጨባጭ ውጤቶች መነሻነት በቀላልና መንግስት ትኩረት በሚሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ባለሃብቶች ሃገሪቱ በርካታ ድጋፎችን ታደርጋለች። ስለሆነም ነው በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በሚገነባው የቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለጃፓን አምራቾች የሚውል ልዩ የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ያለው፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በጃፓን ወገን የሚፈረመው የመግባቢያ ስምምነት፣ በቦሌ ለሚ ሁለት ውስጥ ለጃፓኖች ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማምረት የሚውል ልዩ የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት የሚያስችልና የሃገራችንን ኢኮኖሚ የበለጠ ለማሳደግ የሚያግዝ የቴክኖሎጂ አቅም  ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡

ስምምነቱን በጃፓን ወገን የሚፈርሙት ተሞኒየስ የተባለው የጃን የኢንቨስትመንት ኩባንያ ሲሆን፣ ዘፊር የተሰኘውና በካምቦዲያ የፕኖም ፔን ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን ባለድርሻ የሆነው የዚህ ኩባንያ ወኪሎች እንደሚሆኑ ከጃፓን ኤምባሲ እንዲሁም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘውን መረጃ ዋቢ ያደረጉ በርካታ የብዙሃን መገናኛዎች አመልክተዋል፡፡ እነዚሁ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ከሆነ እ.ኤ.አ በ2012 የተመሠረተው ቶሞኒየስ ኩንያ፣ በጃፓን የሪል ስቴት ዘርፍ እንዲሁም የደረቅ መርፌ ሕክምና ማዕከል በሰፊው ይንቀሳቀሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር በካምቦዲያ ትልቁ እንደሆነ የሚነገርለት፣ የፕኖም ፔን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለድርሻ በመሆን ያስተዳድራል፡፡

መንግሥት የጃፓን ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ለማድረግ በብዙ ሲወተውት ከርሟል፡፡ የዚህ ልዩ ዞን ስምምነት ወደ ተግባር መሸጋገር ከቻለም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ጃፓናውያን አምራቾች የሚሳተፉበት ፕሮጀክትይሆናል ፡፡ይህ ደግሞ የሚሳካ ለመሆኑ የመጣንባቸው መንገዶች ይልቁንም ይህንኑ መሰረት አድርገን መገንባት የቻልነው አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ የሚያረጋግጥልን ይሆናል። ከዚህም ባሻገር የጃፓን ንግድና ኢንቨስትመንትን በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚሠራ ተቋም ጽሕፈት ቤት ሥራ ከጀመረ ወራትን ማስቆጠሩ፣ ጃፓን በኢትዮጵያ ስላላት የወደፊት ፍላጎት ማሳያ ነው፡፡  ጃፓንን ጨምሮ ሌሎችንም ግዙፍ አለም አቀፍ ኩባንያዎችን ማስከንዳት የቻለው ኢኮኖሚ የተገነባውም በዚሁ የውጭ ኢንቨስትመንትና ዘርፉን በሚያበረታታው ፖሊሲ ለመሆኑ የሚመለከታቸው አለም አቀፍ ተቋማት ማረጋገጣቸውም ሊዘነጋ የማይገባው ሌላኛው ማስቻያ ነው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፈው ዓመት በ73 ቢሊዮን ዶላር የሚለካ አቅም ያለው ስለመሆኑና ይህም ከካቻምናው የ64.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚልቅ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፤ በተያዘው ዓመት (እ.ኤ.አ. 2017) ወደ 78.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ትንበያውን በዚሁ መረጀው አመልክቷል።  

በተመሳሳይም የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ትንበያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በ8.3 በመቶ እንደሚያድግ የሚያረጋግጥሲሆን፤ ይህም ወደሃገራችን ያሰፈሰፉትን የውጭ ባለሃብቶች መበራከት የሚያጠይቅ ነው፡፡ የነዚህ ተቋማት መረጃና ትንበያ በዚህ ብቻ አያበቃም። ኢትዮጵያ የኬንያን ኢኮኖሚ በ3.6 ቢሊዮን ዶላር በመብለጥ በቀጣናው ግዙፉን የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ስለመቻሏና ለዚህም ያበቃት በየዓመቱ ያስመዘገበችው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ አውራነቷን ከሁለት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ ያስረከበችው ኬንያ በበኩሏ፣ ካቻምና ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ መጠን ግዝፈቱ በገንዘብ ሲተመን 64 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር፡፡ ዓምና የ69 ቢሊዮን ዶላር ግምት የነበረው ኢኮኖሚዋ፣ በዘንድሮው እንቅስቃሴው 75 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የሚገመት በመሆኑ ከኢትዮጵያ አኳያ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በታች ሆኗል፡፡

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መግዘፍ ተጠቃሽ ከሆኑ የልሂቃን ምክንያቶች መካከልም ይኸው ይውጭ ኢንቨስትመንት በቀዳሚነት ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ የሕዝቡ መብዛትም ለአገር ውስጥ ገበያ የፈጠረው አቅም እንዲሁም ለውጭ ባለሀብቶች እንደልብ የቀረበው የሰው ኃይል እና ከላይ የተመለከቱ ማበረታቻዎች በልሂቃኑ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል፡፡  

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ የዚህ ዓመት የኢንቨስትመንት ሪፖርት እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚጠቀሱ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ ሆኗለች፡፡ በአንጎላ የ14 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን ከሚመራው ጎራ የተሰለፈችው ኢትዮጵያ፣ ከግብፅ፣  ከጋና እና ከናይጄሪያ በመከተል በአፍሪካ ዋና ዋና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ተብለው ከተደለደሉ አገሮች አንዷ መሆኗን የተመድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 የተመዘገበው የውጭ ኢንቨስትመንት 3.2 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የጠቀሰው ይኸው ሪፖርት፣ እንዲህ ያለው የኢንቨስትመንት መጠን የተመዘገበው የዓለም የሸቀጥ ንግድ እጅጉን እየተቀዛቀዘ በቀጠለበት፣ የውጭ ኢንቨስተሮችም ወደ አፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች ወዳሉት አገሮች ለመምጣት መነሳሳቱን ባጡበት ወቅት መሆኑ ግምት እንደሚሰጠው የሚያስገድድ የኢንቨስትመንት መጠን መሆኑን አመላክቷል፡፡ በዚያም ላይ በኢትዮጵያ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚያሳየው ለውጥ ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል ያለው ይህ ሪፖርት፣ ኢንቨስትመንቱ የ46 በመቶ ዕድገት እንደነበረውም አትቷል፡፡

ልሂቃኑም ሆነ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማቱ እንዳረጋገጡት ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገው ጉዞ ለማሳካት መንግስት ለማምረቻው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎችም ያመለክታሉ፡፡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ውጤታማነት የማምረቻው ዘርፍ የማይተካ ሚና እንዳለው  የሚገልጸው የሚንስቴሩ መረጃ፤ በዚሁ መነሻ ሁሉን አቀፍ ዕድገት ለማስመዝገብ መሠረት ለሚሆነው ለማምረቻው ዘርፍ መንግስት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዘርፉ በተለይ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገው ጉዞ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው በዚሁ መረጃ ላይ ተመልክቷል፡፡ ለዚህም በ2010 በጀት ዓመት ለዘላቂ ልማት የሚመደብ በጀት ሙሉ በሙሉ ለዚህ ዘርፍ ድጋፍ ይውላል። በዚሁ መሠረት ለአነስተኛና መካከለኛ ማምረቻዎች   ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ፣ ዘላቂነትና ተመጋጋቢነት ያላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ መንደር ይቋቋማል፡፡

የሚቋቋመው የአምራች ኢንዱስትሪ መንደር እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በዋና ዋና ከተሞችና በወረዳ መስተዳድሮች ሲሆን፤ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  የተቀመጠውን ዘርፉ ለ758ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል፡፡ እንዲሁም ዘርፉ በሀገራዊ ዕድገት ላይ የነበረውን ድርሻ ከአምስት ወደ ስምንት  በመቶ ከፍ ያደርጋል፤ ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት 25 በመቶ ይሸፍናል፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬም  ያስገኛል፡፡ ከሰሞኑ ይፋ የሆነው የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርትም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 በአፍሪካ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ያሽቆለቆለ መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፤ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ግን ጠንካራ ስኬት ማስመዝገባቸውን ጠቅሷል። በዚህም የ46 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት በማሳየት ኢትዮጵያን በአህጉሩ ቀዳሚዋ መዳረሻ አገር አድርጓታል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱም 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን አስነብቧል።  በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በየብስ በተከበቡ አገሮች ቅናሽ ቢያሳይም ኢትዮጵያ ግን ለአራት ተከታታይ ዓመታት ጭማሪ ማሳየቷን ሪፖርቱ አመልክቷል። ኢትዮጵያም በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር 2015 በየብስ ከተከበቡና ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ታዳጊ አገሮች መካከል 5 ደረጃ የነበረች ሲሆን ሪፖርቱ ወደ 2 ደረጃ ማደጓን ጠቅሷል። እንደ ሪፖርቱ ገለጻ የመሰረተ ልማትና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች አገሪቷን በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስኬታማ አድርገዋታል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy