Artcles

የዚያ ማዶ ፅንፈኞች

By Admin

June 05, 2017

የዚያ ማዶ ፅንፈኞች…

                                                           ቶሎሳ ኡርጌሳ

የዚያ ማዶ ፅንፈኞች ናቸው። የፅንፈኞቹ ስብስብ ከግለሰብ እስከ በሀገራችን በአሸባሪነት የተሰለፉ ቡድኖች ድረስ ይዘልቃል። ግለሰቦቹና ቡድኖቹ የዚህን ሀገር አጠቃላይ ሁኔታ በዓይናቸው ሳይሆን በስማ በለው የሚያውቁ ናቸው። ምናልባትም በዘመነ ደርግ በኢህአፓነት የተሰደዱ፣ በደርግ ዘመን የኢህአፓ አቀንቃኞችና የመድረክ ላይ ተዋናዩች አሊያም ለባዕዳን አድረው ለገንዘብ ሲሉ የገዛ ህዝባቸውን የካዱ አሸባሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የሁሉም መገለጫ ግን ፅንፈኝነት ነው። ወላጅ አባታቸው ዕንፈኝነት ነው። ለኢትዮጵያ በጎ የማያስቡ፣ ህዝባቸውን በገንዘብ የለወጡ፣ መርሆአቸውን አሉባልታ አድርገው ‘ወደቀ’ ሲባል ‘ተቃጠለ’ ማለት የሚቀናቸው እንዲሁም እንደ ጠላት ሀገር በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁለንተናዊ ስኬቶች ዓይናቸው ደም የሚለብስ ጥቂት የዲያስፖራ “ቆማሪዎች” ናቸው። የዚያ ማዶ ፅንፈኞች።…   

ፅንፈኞቹ ሀገራችን ውስጥ አንድ ክስተት በተፈጠረ ወቅት የሚያካሂዱት ተመሳሳይ ዝማሬ እዚህ ሀገር ውስጥ ሆኖ ሁኔታውን በገለልተኝነት ለሚከታተል ሰው አስቂኝ ነው። ሀገር ቤት የተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ምንም ይሁን ምን ፅንፈኞቹ ሁከት ቀስቃሽ አሉባልታዎቻቸውን ሰንቀውና የነገር ካራቸውን ስለው በየሚዲያዎቹ ሲያቅራሩ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ገሚሳቸው ገንዘብ ተከፍሏቸው አሊያም ያለፈውን ማንነታቸውን በእዝነ ልቦና እያስታወሱ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸውን ስለሚያንፀባርቁ ሃፍረት የሚባል ነገር የሚነካካቸው አይደሉም። አንዳንዶቹ ደግሞ በጥራዝ ነጠቅነት ሲያሻቸው ከምዕራቡ በል ሲላቸው ደግሞ ከምስራቁ ጎራ እየጠቀሱ መለፈፍን ስራዬ ብለው የያዙ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ እዚያ ማዶ…ውጭ ሆነው በጠባብነት የታጀለ የኃይማኖት አክራሪነትን በመስበክ ኮሮጇቸውን ለመሙላት የሚከጅሉ ናቸው።

ርግጥ ለፅንፈኞቹ “የሰው ወርቅ አያደምቅ” የሚለው ይትብሃል ምናቸውም አይደለም። አባባሉ ግን የራስ ባልሆነ ወርቅና ጨርቅ መድመቅ የማያኮራ፣ የሰው ነገር ሁሌም የሰው መሆኑን እንዲያውም የማታ ማታ የሃፍረት ሸማን ማከናነቡ እንደማይቀር የሚያመላክት ነው። እነርሱ ገንዘብ እስካስገኘላቸው ድረስ የሰው ወርቅ ‘የእኔ ነው’ የሚሉ ናቸው። እናም የእነርሱ የሚመስላቸውን የሰው ወርቅ ለብሰውና አምረው ለመታየት ይከጅላሉ። አንዳንዶቹ የሰው ወርቁን ለብሰው በምሬት የሚቃወሙትም ባህር ማዶን እንደ ማምለጫና የወንጀል መሸሸጊያ አድርገው ስለሚቆጥሩት ነው። በዚህም ሳቢያ በሌላው ወርቅ አምረውና ደምቀው ኢትዮጵያዊንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዋረድ የማይቆፍሩት ድንጋይ፤ የማይቧጥጡት ዳገት የለም።

በዚያ ማዶ ፖለቲከኝነታቸው የሚያውቁትና የቀሰሙት “ዕውቀት” ቢኖር፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፈጠሩት ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓት በሰላማዊ ሰልፍ የሚናድ እንደሆነ መቁጠራቸው ነው። ግና ዴሞክራሲያዊውና ልማታዊው ስርዓት ዋልታ፣ ማገሩና ውጋግራው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው እንደ ድቡሽት ቤት የሚናድ አይደለም። የዚያ ማዶ ፅንፈኞች የህዝብን ሃያልነት በሰልፍ ለመቀልበስ የሚሹ የሞኝ ስብስቦች ይመስሉኛል።

ፅንፈኞቹ አባታቸው አንድ ቢሆንም፤ ለመቃወም ብቻ ብለው የሚቃወሙ ናቸው። ለተቃውሞ ሲሉ በአንድነት የሚሰለፉ፣ በርዕዩተ-ዓለምና ለተቃውሞ ባነሳሰቸው ጉዳይ ግን የማይተማመኑ ናቸው። አንዱ ያረጀውን “የአንድነት” የትምክህት ቀኖናን ይዞ ሲነሳ፣ ሌላው ደግሞ በጠባብነት ይታመሳል። አስገራሚው ጉዳይ የዚያ ማዶ ፅንፈኞቹ “የትግል አንድነት ፈጥረናል” በማለት ትምክህተኛው ከጠባቡ ጋር የሚያደርገው የውህደት ጋብቻ ነው።

ለዚህ አባባሌ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ ወቅቶች ባህር ማዶ ሆነው ከተጋቡት ውስጥ ጥቂት የግንቦት ሰባትን ድራዎችን ማንሳት እችላለሁ። ግንቦት ሰባት የተሰኘው የሽብር ቡድን ራሳቸውን “ኦነግ” እና “ኦብነግ” እያሉ ከሚጠሩ የሽብር ቡድኖች እንዲሁም “ጃዋር” ከሚባለው አክራሪ ሙስሊም ጋር አስቂኝ ጋብቻ ፈጥሯል።

ራሱን “ግንቦት ሰባት” እያለ የሚጠራው የሽብር ቡድን ኤርትራን በመሳሰሉ የሀገራችን ጠላቶች ጉያ ስር ተወሽቆ በሻዕቢያ አንጋሽነት አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብቶ ኢትዮጵያን በአንድነት ሲያስተዳድር በየቀኑ በህልሙ እያየ የሚያድር ሲሆን፤ “ኦነግ” እና “ኦብነግ” ደግሞ ኦሮሚያንና በኢትዮጵያ ሶማሌ ስር የሚገኘውን ኦጋዴንን እንገነጥላለን ብለው የተነሱ ፀረ-አንድነት ኃይሎች ናቸው። “ጃዋር ባለ ሜጫውም”ና ጥቂት ተከታዮቹም ቢሆኑ፤ በኦሮሚያ ስም የአክራሪ ሃይማኖተኝነትን ለማስፋፋት በውጭ ሃይሎች የተደራጁ ሃይሎች ናቸው። ውሉ የጠፋበትና ከእነማን ጋር እየተቧደነ እንደሆነ የማያውቀው አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” በእንዲህ ዓይነቱ ፌዝ ውስጥ ያለ ነው። እናም የዚያ ማዶ ፅንፈኞቹ “በእሳትና ጭድነት” የተሰባሰቡ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ናቸው።        

በዚህ ዓይነት አስቂኝ ትብብር ተቧድነው እዚያ ማዶ በፅንፈኝነት የሚራወጡት አካላት፤ በወንጀል የሚፈለጉ፣ የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች፣ የሀገራችን ጠላት የሆነው የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች እንዲሁም ከእንቅልፋቸው ብንን ሲሉ ኢትዮጵያ ተበታንና የምትታያቸው ሟርተኞች ናቸው። በሚሰበሰቡበት ሀገረ አሜሪካ አሊያም አውሮፓ ውስጥ ሆነው የሚሰጥዋቸው መሰረተ ቢስ አስተያየቶች፤ ቁም ነገር አልባ ከመሆናቸው ባሻገር የኮሜዲያንነት ባህሪይን እየተላበሱ መጥተዋል።

የእነዚህ ፖለቲካን የማያውቁ አሊያም ፖለቲካውን ገና ዳዴ እያሉ የሚገኙ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች አስቂኝ ድራማ በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም። አሁንም ጥቂት ምሳሌዎችን ላንሳላችሁ። እነዚህ “ሞትኩ ለገንዘብ” የሆኑ ፌዘኞች በሀገረ አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያዊ የእምነት ተቋማትንና የንግድ ቦታዎችን በፖለቲካ ስም እስከመፈረጅ እንደሚደርሱ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል። ይህ ወዳጄ ለ20 ዓመታት ያህል አሜሪካ የኖረ ሲሆን፤ የወዳጄን ወግ በብዕሬ እንዲህ እንደወረደ አቀርበዋለሁ።

…ፅንፈኛ ፖለቲከኞቹ በአንድ የእምነት ተቋም አሊያም የንግድ ቦታ ተቀጣጥረው ለመገናኘት ከፈለጉ፤ በዚሁ ሁኔታ ቀጠሮ ይይዛሉ። ታዲያላችሁ እኔም “በምን መልኩ” ማለቴ አልቀረም። ወዳጄም ለጠቀና…ይኸውልህ በሀገረ አሜሪካ አንድ ስቴት ውስጥ ሁለት የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ካለ…‘እገሌ የት እንገናኝ?’ ማለት አዲስ ነገር አይደለም። እናም የፅንፈኞቹ ምላሽ እንደ ፖለቲካ እምነታቸው በርከት ብለው የሚገኙበት ቤተክርቲያን ውስጥ ይቀጣጠራሉ። ከዚህም “የግንቦት ሰባት” ወይም የሌላ የፖለቲካ አቋም ገብርኤል መኖሩን ለመገንዘብ አይከብድም። ነገሩ የሚደንቅ ነው። አሁን እስኪ የፖለቲካ አቋምንና ሃይማኖትን ምን አገናኛቸው?…

ፅንፈኞቹ ንግድ የሚጧጧፍበት ቦታ ለመገናኘት ከፈለጉም በተመሳሳይ መልኩ ቀጠሮ መያዛቸው አይቀርም። ርግጥም ጉዳዩ ያስገርማል። እነዚህ ወገኖች በሰለጠኑት ዓለም እየኖሩ ኃይማኖትንና ፖለቲካን እንዲሁም ንግድንና ፖለቲካን ለይተው አለማወቃቸው ፅንፈኝነት ምን ያህል ዓይናቸውን እንደጋረዳቸው የሚያሳብቅ ነው። ያም ሆኖ ግን ፅንፈኞቹ ኃይማኖትን ጨምሮ በእያንዳንዱ ጉዳይ ሽፋን እየተጠቀሙ ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለመፈፀም የማይወርዱት ቁልቁለት የማይወጡት ዳገት የለም።

የዚያ ማዶ ፅንፈኞች ለሀገራቸው የሚመኙት የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ አሊያም ዕቅድና ኘሮግራም አይደለም። የእነርሱ ዓላማ ብሔርንና ኃይማኖትን ከለላ በማድረግ ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት ሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን ዕድገት እንደምንም ብሎ ለማስተጓጎል መሞከር ነው—ባይሳካላቸውም። ዳሩ ግን ዛሬ ሀገራችን ውስጥ የህዝብን ኑሮ በተጨባጭ በመለወጥ ላይ የሚገኝ መንግስት ያለና ባህር ማዶ ቁጭ ተብሎ ለሚቀነቀን ተራ ወሬ ጆሮውን የሚሰጥ ህዝብ ባለመኖሩ ፍላጎታቸው አልሰመረም፤ ሊሰምርም አይችልም።

ምንም እንኳን የዚያ ማዶ ፅንፈኞቹ እንደ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ከመሳሰሉ አክራሪ ኒዮ ሊብራል ኃይሎች ጋር እጅ እና ጓንት ሆነው አሉባልታን በማቀንቀን ሀገራችን ውስጥ ነውጥ ለማስነሳት ቢጥሩም፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵየያውስጥ ስልጣን በሀገራችን ህዘቦች ስር ያለ በመሆኑ ፍላጎታቸው መና ሆኖ ቀርቷል። ዛሬ ላይ የዚያ ማዶ ፅንፈኞችን የነውጥ እሳቤ የሚያስተናግድና በውጭ ሃይሎች መዘውር የሚመሰረት አሻንጉሊት መንግስትን የሚያስተናግድ ህዝብ የለም።

ዳሩ ግን “የእሳትና ጭድ” ስብስብ ፅንፈኞቹ የክፋት ካባቸውን ደርበው፣ አስበውና ቀምረው ለፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ ሆነው ቢንቀሳቀሱም፤ ይህን እኩይ ተግባር መቀበል የሚችል ህዝብ እንደሌለ የገባቸው አይመስልም። አሊያም ለሚያገኙት ዳረጎት ሲሉ እንዲገባቸው አይፈልጉም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ኢትዮጵያን አትርዷት፣ ኢትዮጵያዊን አትምረጡ” በማለት በየአደባባዩ ዶሴያቸውን ይዘው የሚታዮት ለዚህ ይመስለኛል። በአሸባሪው “ግንቦት ሰባት” የቅርብ ተቆጣጣሪነት፣ ነገር ግን በሻዕቢያና በሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው እንዲሁም የሀገራችንን ህዝቦች ለማጫረስና ዘር እየለየ ለማባላት ሌት ተቀን እሳት የሚረጨው “ኢሳት” በተሰኘው ባንዳ ጣቢያ አሉባልታን የሚያንቦለቡሉት ይህን ሃቅ ለገንዘብ ሲሉ ለመረዳት አለመፈለጋቸው ነው። ያም ሆነ ይህ ግን በጨዋ ደንብ ለዚያ ማዶ ፅንፈኞች “በጩኽት የፈረሰ ሀገርና ህዝብ የለም” ብሎ ማለፉ ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም።