Artcles

የየአካባቢውን ሰላም በአዋጅ ብቻ ማስጠበቅ ይቻላልን?

By Admin

June 29, 2017

የየአካባቢውን ሰላም በአዋጅ ብቻ ማስጠበቅ ይቻላልን?

                                      ዳዊት ምትኩ

ሰላም ከሌለ ስለ ልማትም ይሁን ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማሰብ ብሎም መናገር ትርጉም ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱ እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ሊነጣጠሉ የማይችሉ ከመሆናቸውም ባሻገር፤ አንዱ በሌለበት ሌላው ፈፅሞ ሊኖር ስለማይችል ነው። እናም ይህን ነባራዊ ዕውነታ ለማረጋገጥ፤ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ ሰላምን በማጠናከር ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ዕውን ለማድረግ ሀገራችን ረጅም መንገድ ተጉዛለች።

ታዲያ ይህ ጉዞዋ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በአንድ በኩል በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱና የውጭ ሃይሎችና ፅንፈኞች ተላላኪ በመሆን የሚንቀሳቀሱ፣ በሌላኛው ዘውግ ደግሞ እዚሁ ሀገር ውስጥ ቁጭ ብለው ‘በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንቀሳቀሳለን’ የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሀገሪቱ ከምትመራባቸው የህግ ማዕቀፎች ውጭ በመሄድ የተገኘውን አስተማማኝ ሰላም ለመቀልበስ ጥረት ማድረጋቸው እንደ ተግዳሮት የሚታይ ይመስለኛል።

ይሁንና ሰላምን በፅኑ የሚሹት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያመጧቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገዳቸው እንዳይደናቀፉ ብሎም የኋሊት እንዲቀለበሰሱ ስለማይፈቅዱ እነዚህን ሃይሎች ሊቀበሏቸው አልቻሉም።

እንዲያውም በተለያዩ ወቅቶች እነዚህ ሃይሎች በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ይህ ሰላምን አጥብቆ የመሻት ጉዳይ የሀገራችን ህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑም፤ ዛሬ ሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ሊገነባ ችሏል። በዚህም ሳቢያ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሰላማዊ ትግልን ማካሄድ የሚችልበት አውድ ዕውን ሆኗል። ይህ ሰላማዊ አውድ ሊገኝ የቻለው ህዝቡ ስለ ሰላም ካለው ቀናዒ ምልከታ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የየትኛውም ሀገር ህዝብ ሰላም ከሌለ መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂቶች እንደሚሆኑ ያውቃል። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል። በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች የሚወሰን ይሆናል። ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል።

ይህን የሰላም እጦት ፈተና የትኛውም ሀገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል።

ርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው። ህዝብ ያልተሳተፈበት ነገር ትርጉም የለውም። የተፈለገውንም ዓላማ ሊያሳካ አይችልም። ይህም የየአካባቢውን ሰላም በህዝቡ ተሳትፎ እንጂ በአዋጅ ብቻ እውን ማድረግ እንደማይቻል ያመላክታል።

በየአካባቢው የሚገኘው የሀገራችን ህዝብ ትናንት ያለፈበት አስከፊ መንገድ ዛሬ ያገኘውን አስተማማኝ ሰላም ገለል አድርጎ ቦታውን እንዲረከበው ቅንጣት ያህል ፍላጎት የለውም። በትውስታነት የኋሊት የሚሸሸውና ዳግም እንዳይመጣም ዶሴውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋው የያኔው አባጣና ጎርባጣ መንገድ ተመልሶ እንዳይመጣ ለሰላሙ ፀር የሆኑ ሃይሎችን በማውገዝ፣ በማጋለጥና ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በባለቤትነት መንፈስ የመንቀሳቀስ ፍላጎቱ መሰረት ይኸው ይመስለኛል።

ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ መቅረብ የሚችል ህዝብ ነው። ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል ሩብ ክፍለ ዘመንን እልፍ ባለ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትምህርት ወስዷል።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ ስለሰላም ቢናገር የሚበዛበት አይደለም። አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት በሚገባ ይገነዘባል።

ያኔ ተራራ የሚያክለውን የሀገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውስ ህዝብ ነው።

በመሆኑም በአንድ በኩል የሀገሪቱን ሰላም ማረጋጋትና የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ልማት የማዞር ስራ፣ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን የማምጣትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የወሰደው ጊዜና የጠየቀው ሁሉን አቀፍ መስዕዋትነት ከዚህ ህዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚጠፉ አይመስለኝም።

ከዛሬ 15 ዓመት በኋላም ቢሆን የነበሩት የተዛቡ አስተሳሰቦች ከሞላ ጎደል በመታረማቸውና መንግስትም ድህነትን ለመቀነስ በወሰዳቸው ሰፋፊ ርምጃዎች ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ የሰላም መኖር ምን ያህል ፋይዳ እንደነበረው ያውቃል። የሀገራችን ህዝብ በአምባገነኑ የኤርትራ መንግስት የተቃጣበትን ወረራ ፈጥኖ በመመከት፣ ውሰጠ-ድርጅት ህፀፆችን በአስቸኳይ ፈትቶ ፊቱን ወደ ልማት ባይመልስ ኖሮ፤ ያለ ሰላም በጦርነትና በንትርክ ጊዜውን ያጠፋ እንደነበር ግልፅ ይመስለኛል። ይህን ደግሞ ከዚህ ህዝብ በላይ ሊገነዘብ የሚችል አይመስለኝም።

እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን ማድረግና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር። ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ባላለመ ነበር።

በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ መሳ ለመሳ ዴሞክራሲው ሀገር በቀል ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት፤ እንዳለ ሆኖ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳድር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ህዝቡ የየአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እስካሁን ድረስ ያበረከተው አስተዋፅኦ ዋነኛው የሰላም ተዋናይ እርሱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። የየአካባቢውን ሰላም በአዋጅ ብቻ ማስጠበው እንደማይቻልም እንዲሁ።