Artcles

የደቡብ ሱዳን የሠላም ጉዳይ የእኛም ጉዳይ የሚሆነው …

By Admin

June 26, 2017

የደቡብ ሱዳን የሠላም ጉዳይ የእኛም ጉዳይ የሚሆነው …

ወንድይራድ ኃብተየስ

የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ በርካታ ክስተቶችን አምቆ ይዟል።  ደቡብ ሱዳኖች ከሰሜን ሱዳን ጋር በነበራቸው የረዥም ጊዜ የሽምቅ ውጊያ ጦርነት ውስጥ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሽምግልናው የተሳካ እስኪመስል ድረስ ሁለቱን ባላንጣዎች አዲስ አበባ ላይ አሸማግለው እጅ ለእጅ አጨባብጠዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ከሽምግልናው በኋላ ወደ ወትሮው ግጭትና ጦርነት ተመለሱ እንጂ።

ታዲያ ያኔ የደቡብ ሱዳኑ የመጀመሪያው ንቅናቄ አኛኝያ አንድ ሁለተኛው ደግሞ አኛኝያ ሁለት ይባል ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን የሽምቅ ተዋጊዎች ይጠለሉ የነበረው ጋምቤላ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ በኋላም በደርግ የደቡብ ሱዳን ሽምቅ ተዋጊ ኃይል ሙሉ በመሉ ሲሰለጥን የነበረውም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ነበር። በደርግ ዘመን ብቻ 40 ሺህ የደቡብ ሱዳን ሠራዊት የሰለጠነው ኢትዮጵያ ተቀምጦ ነው፡፡ ዛሬ በህይወት የሌሉት የደቡብ ሱዳን ንቅናቄ መሪ ኮሎኔል ጆን ጋራንግ የዛሬው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ምክትላቸው ሬክ ማቻር ሌሎችም መቀመጫቸውን ኢትዮጵያን መርጠው ነበር።

ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ራሷን ችላ መቆም ከጀመረችበት ጥቂት ዓመታት አንስቶ ሠላምና መረጋጋት ያላት አገር ሆና ልማትና ዕድገቷ ላይ እንድታተኩር ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡ ነፃይቱ አገር ሠላምና መረጋጋት ያላት አገር እንድትሆን በተደጋጋሚ ጊዜም ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች፡፡

በደቡብ ሱዳን የነገሰው ኋላ ቀር የጎሣ አስተሳሰብ በፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ዲንካ ጎሣና በምክትል ፕሬዚዳንቱ ሬክማቻር የኑዌር ጎሣ መካከል ያለው የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቅና ፉክክር በጥላቻ የተሞላ በመሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በእነዚህ ኃይሎች የተቆሰቆሰው ጦርነት ለብዙ ሺህዎች ደቡብ ሱዳናውያን ሞትና ለሚሊዮኖች ደግሞ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ብቻ በጦርነቱ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ሠላም አግኝታ በተረጋጋ ሁኔታ እንድትኖር ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላም ሰፊ የሽምግልና ሥራ ከውናለች። ያለመሰልቸት ሁለቱንም ወገኖች አቀራርባ ሠላምና እርቅ እንዲፈጠር የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡

የአፍሪካ ሕብረት፣ የአሜሪካና እንግሊዝ መንግሥታት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጉዳዩ ውስጥ ገብተው በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፤ አመራር ላይ ያሉት ኃይሎች ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሠላም ሲሉ ሠላም እንዲያወርዱ ከእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት እንዲወጡ ከፍተኛ የማሸማገል ሥራ ተከናውኗል። ሆኖም ጊዜያዊ እርቅ እንጂ ዘላቂ ሠላም አላስገኘም – የሚያሳዝን ነው። ተስፋ የተጣለበትና ብዙ የተደከመበት እርቅ ውሎ ሳያድር ይፈርሳል፡፡ ከአሸማጋዮቹ በላይ ለራሳቸው አገር ሆነ ህዝብ ማሰብና መቆርቆር የነበረባቸው ደቡብ ሱዳናውያኑ ነበሩ – ይህም አልሆነም፡፡

በቅርቡ በዚያች አገር ሠላም የሰፈነ በመሰለ መልኩ ሁለቱ ተቀናቃኞች የጋራ መንግሥት መሥርተው እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ ሬክ ማቻር ከጋምቤላ ወደደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ገብተው ጥቂት ጊዜ ደቡብ ሱዳን በሠላም ውላ ማደር ጀምራም ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ሁሉም ወገን የተመኘውና የናፈቀው ሠላምና መረጋጋት ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ ዳግም ሁለቱም ወገኖች ጠመንጃ አንስተው ጦርነት ውስጥ ገቡ። የአገሬ ሰው ለያዥም ለገራዥም አስቸገረ የሚለው ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው።

ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን አግኝታ እፎይ ማለት ከጀመረች ትንሽ ዓመታትን ያስቆጠረች አገር ነች፡፡ የመሠረተ ልማት ግንባታ ለመጀመር ደፋ ቀና የሚባልበት፣ አብዛኛው ህዝብ የኑሮ መሠረቱን በግብርናና በከብት እርባታ ላይ አድርጎ የሚኖርባት፣ መብራት፣ ንጹህ ውኃ፣ ጤና፣ ትምህርትና መንገድ በመጠኑም ጁባ አካባቢ ካልሆነ በስተቀር ጭርሱንም የለም ማለት የሚቻልባት አገር ነች – ደቡብ ሱዳን።

በዚህ የከፋ ኋላ ቀርነት ድጥ ውስጥ የገባች አገራቸው ከድህነት አረንቋ ተላቅቃ ወደ ልማት፣ ዕድገትና ሥልጣኔ እንድታመራና ህዝቡም ያለልዩነት በፍቅር፣ በመቻቻልና በመከባበር እንዲኖር ከማድረግ ፋንታ ህዝባዊም ሆነ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለባቸው የደቡብ ሱዳን ሹማምንት እጅግ ኋላ ቀር በሆነው የጎሣ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ተደፍቀው እርስ በእርስ መፋጀታቸውና መጫረሳቸው በሌላው ዓለም ዘንድ አፍሪካን አሳፋሪ ግምት ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡

የጎሣ ፖለቲካ የዓለማችን እጅግ ኋላ ቀሩ ፖለቲካ ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ቀድሞም ለነበሩ አስከፊ ጦርነቶች ሁነኛ መነሻ በመሆን ለአገራቱ መውደምና ለህዝቦች እልቂት ግዙፉን ድርሻ ተጫውቷል። አፍሪካ ማደግና መለወጥ በሚገባት ደረጃ እንዳትራመድ ሰቅዞ ይዟታል። ለዘመናት የኋሊት ሲጎትታት የኖረው ይኸው የጎሣ ጦርነት የከፋው ምክንያት ሆኗል።

በደቡብ ሱዳን ውስጥ በተለያየ ጊዜ እያገረሸ ከሚከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ጀርባ የተለያዩ የውጭ ኃይሎችም እጅ እንዳለበት ይጠረጠራል። በነዳጅ ዘይት ሀብታም አገር ብትሆንም ይህንኑ በሠላምና በአግባቡ እንዳትጠቀም፣ የህዝቧም ኑሮ እንዳይሻሻልና እንዳይለወጥ በእርስ በእርስ ጦርነት ተጠምዳ ስትታመስ በመሀል የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በማግበስበስ ሥራ የተጠመዱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዳሉ መገመት አያዳግትም፡፡

በሌላም ወገን ኢትዮጵያን ዒላማ ማድረግ የዘወትር ምኞታቸው የሆኑት የግብጽና የኤርትራ ሰዎችም ደቡብ ሱዳንን መረማመጃ በማድረግ እግራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የሚያደርጉት የማያባራ ሙከራ እንዳለ ሆኖ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ገብተውና ሰፍረው በንግድና በተለያየ ሽፋን ስም ተከልለው የሚሰሩት ተግባር ግጭቱን የሚያባብስ እንጂ የሚያበርድ አልሆነም።

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ጎሣ አባላት የሆኑት ኑዌሮች በኢትዮጵያ ውስጥም ስለሚገኙ ይህንን በተፋለሰ አቅጣጫ እንዲተረጎም በማድረግ ኢትዮጵያ ኑዌሮችን ትረዳለች የሚል የተዛባ ፕሮፓጋንዳ ሲያዛምቱም ቆይተዋል። ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን መንግሥት እንደ መንግሥት ራሱን ችሎ ተደማምጦ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ ለአገሩና ለህዝቡ ልማትና ዕድገት እንዲቆም፤ የተረጋጋች አገር እንዲፈጠር የጎረቤቶቼ ሠላም የእኔም ሠላም ነው በሚለው የውጭ ጉዳይ መርህዋ መሠረት ብርቱ ድጋፍና እገዛ አድርጋለች፡፡ አሁንም በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

ደቡብ ሱዳን የተረጋጋች ሠላም ያላት አገር እንድትሆን ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም እየሰራች ነው። አገሪቷ እንድትበጠበጥና እንድትታመስ የሚያደርጉት በእጅ አዙር ሚና የሚጫወቱት ወገኖች የደቡብ ሱዳንን አለመረጋጋት በመጠቀም የአገሪቱን ሀብት ለመዝረፍና ለመቀራመት ትግል የሚያደርጉ ኃይሎች ናቸው፡፡

በደቡብ ሱዳን እርቅ ለማስገኘት ብዙ ተደክሞበታል፡፡ በተደጋጋሚ እርቅ ቢያደርጉም  ዘላቂ ሠላምን መሬት ላይ ሊያወርዱ አልቻሉም፡፡ በቅርቡም በሁለቱ ወገኖች መካከል በዓለም አቀፍ ሽምግልና የተደረሰበት እርቅ ፈርሶ ዳግመኛ የተነሳው ጦርነት ለበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ መፈናቀልም አስከትሏል፡፡ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ከነጻነት በኋላ ለሊት ከቀን ወደአገር ግንባታ ሥራ ፊታቸውን ማዞር ሲገባቸው የእርስ በእርስ ጎሣ ጦርነት ውስጥ በመዘፈቃቸው አገራቸውንም ሆነ ህዝባቸውን እየገደሉት ይገኛሉ፡፡

የደቡብ ሱዳን መከላከያ ጄኔራሎች ከሁለቱ ተቀናቃኝ ጎሣዎች የተውጣጡ ናቸው። የሚያሳዝነው በጋራ ስለአገርና ስለህዝባቸው ማሰብና መሥራት ያልቻሉ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የጎሣ አስተሳሰብ ውስጥ ተነክረው የማያባራ ጥፋትና ውድመት እያደረሱ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዚህም ስለ ጋራ አገራቸው ከማሰብ ይልቅ ከጎሣ አስተሳሰብ በላይ ርቀው መራመድ አልቻሉም። ከጎጥና ጎሣ መንደርተኛ እሳቤ ወጥተው በላቀ አገራዊ ራዕይ እየተመሩ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ ትራንስፖርት፣ የተለያዩ ተቋማትን መመሥረት፣ መገንባትና ማሳደግ ተስኗቸዋል። በአገር ግንባታ ተግባር የመሳተፍ ቁርጠኝነትን ሊያሳዩ አልቻሉም። ገና ከኋላ ቀር አስተሳሰባቸው አልወጡም፡፡ አልዘመኑም፡፡

የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ከሠላምና መረጋጋት፣ ከአገር ግንባታ ልማትና ዕድገት ይልቅ እርስ በርስ ጎጥ እየለዩ መፋጀቱን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው ይዘውታል፡፡ ይኼ አካሄድ አሳፋሪም፤ አስፈሪም ነው፡፡ ችግሩ ለጎረቤት አገራትም ይተርፋል፡፡ ህዝቡ ጦርነቱን በመፍራት የሚሰደደው ወደ አጎራባች አገራቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከአቅሟ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ የምትገኝ አገር ናት፡፡ ሠላምና መረጋጋት በአገራቸው ቢኖር እዚያው እየሰሩ በሠላም መኖር ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ሊሆን ባለመቻሉ ነው ህይወታቸውን ለማትረፍ ስደትን የመረጡት፡፡

የደቡብ ሱዳንን ጎጣዊና ጎሣዊ ደም አፋሳሽ ችግር ከመሠረቱ ለማምከን በአጭር ዓመታት የሚቋጭ የሚፈታም አይመስልም፡፡ የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ የመለወጥ፣ የአብሮ መኖርና የመቻቻልን ባህል ማሳደግ፣ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ የመፍታትን አገራዊ ጥቅም እንዲረዱት ለማድረግ ሰፊ የማስተማር ሥራ በመከወን ብቻ ነው በዓመታት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው፡፡

በደቡብ ሱዳን ህዝብ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት አልተስፋፋም፡፡ ቀድሞም ቢሆን የደረሰው ለጥቂቶች ነው፡፡ እሱም የመማር ዕድሉን ላገኙት ብቻ፡፡ ዋናዎቹ በመንግሥት አመራር ላይ ያሉት በትምህርታቸውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ተብለው የሚታሰቡት ወገኖች በጎጥና ጎሣ አስተሳሰብ አንዱ ሌላውን በማጥፋት ደረጃ ጦርነት የሚከፍቱና ህዝባቸውን የሚያፋጁ ከሆኑ ምንም ትምህርት የሌለውና የጫካ ኑሮውን ብቻ የለመደው በከብት ዕርባታና በግብርና የሚተዳደረው በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ህዝብ ምን እንደሚያስብ ለመገመት አይከብድም፡፡ አደጋው በእጅጉ ያሳስባልና፡፡

ይህንን የተዛባና አንካሳ የሆነ የጎጥ አስተሳሰብና እምነት መለወጥ የሚቻለው ሰፊ የማስተማር ሥራ በመከወን የኅብረተሰቡን ኑሮና ህይወት በመለወጥ የምጣኔ ሀብት የትምህርቱ የጤናው አገልግሎት የትራንስፖርት ዘርፉና የመሳሰሉት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ህይወቱን ከመሠረቱ የሚለውጥ ተጨባጭና መሠረታዊ ርምጃ በመውሰድ ብቻ ይሆናል። በዚህ ረገድ የደቡብ ሱዳን መንግሥት በባለቤትነት አጎራባች አገራትና የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት በአጋርነት ርብርብ በማድረግ ሰፊ ሥራዎችን በህብረትና በትግግዝ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በህዝቡ ውስጥም ሆነ በአመራሩ መሠረታዊ ለውጥና የአስተሳሰብ ሽግግር ሊመጣ የሚችለው በማስተማርና በማስተማር ብቻ ነው፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በደቡብ ሱዳን ያለው ሠላም በመድፍረሱ ግጭቱም አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላምን በኃይል የሚያስከብር ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ከሩዋንዳ የተውጣጣ ሠራዊት በደቡብ ሱዳን እንዲሰማራና ሠላምን እንዲያስከብር የዚያን ሰሞን ተወስኗል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ግዳጅ አስፈላጊ የሆነበት ትልቁ ሥጋት ሁኔታው እየከፋ ሄዶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ብሎም የሚፈራው የጎሣና የዘር እልቂት እንዳይከተል በማሰብ ጭምር ነው፡፡ ርምጃው ተገቢም አስፈላጊም የሆነው ለዚሁ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን የሠላም ጉዳይ የእኛም ጉዳይ የሚሆነው ለዚሁ ነው።