Artcles

የገፅታ ግንባታ ስራችን ውጤቶች

By Admin

June 20, 2017

የገፅታ ግንባታ ስራችን ውጤቶች

                                                          ደስታ ኃይሉ

በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ያላሰለሰ ጥረት ጠንካራና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ከመሆኑም በተጨማሪ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ሀገሪቱ እነዚህን ስኬታማ የሆኑትን ድሎች ለመቀዳጀት የቻለችው ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በተለያዩ ዘርፎች ተቀርጸው ተግባራዊ በተደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካኝነት ነው፡፡

በሀገሪቱ ውጤታማ ከሆኑት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አንዱ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 86 ላይ የተዘረዘሩትን የውጭ ግንኙነት መርሆዎች መሰረት በማድረግ ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም፣ ህልውናና ደህንነት ከአደጋ ለመከላከል፣ ገጽታዋን በበጎ ለመገንባትና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማስቀጠል እንዲሁም የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሥርዓትን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ ተቀርጾ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በስራ ላይ ውሏል፡፡

እርግጥ የየሀገሮች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባህሪ፣ ይዘትና ቅርጽ እንደየ ሀገሮቹ ርዕዮተ ዓላማዊ መስመርና እንደሚከተሉት የዕድገት አቅጣጫ ይለያያል፡፡ ከዚህ አኳያ የቅርብ ጊዜ የሀገራችንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ስንመለከት የአለፉት ሥርዓቶች በተለይም የደርግ የውጭ ግንኙነት ከሥርዓቱ አምባገነናዊ ባህሪይ የሚመነጩና በርካታ ጉድለቶችም የነበሩበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ሀገሪቷን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ድቀትና ለማያባራ ጦርነት ዳርጓታል፡፡ ከሠላም ታገኝ የነበረውን ጥቅምም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡

ደርግ ይከተለው በነበረው አምባገነናዊ ሥርዓት ሳቢያ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከጎሮቤት ሀገሮች ጋር በጥርጣሬ ከመተያየታቸውም በላይ ግንኙነታቸው ወታደራዊ አቅምን በማፈርጠምና በጠብ መፈላለግ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ በዓይነቱ ሆነ በይዘቱም ተለወጧል፡፡ በጋራ ጥቅምና ህልውናን በማስከበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡  

የኢፌዴሪ ህገ – መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሠላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገራችን በሠላምና በዕድገት መጓዝ በጀመረችባቸው ሁለት አስርት ዓመታት ፖሊሲውና ስትራቴጂው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ያስገኛቸው ስኬቶችን እንደሚከተለው መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡

የፖሊሲውና የስትራቴጂው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ነው። በዚህ ስራም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 22 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡

በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሠላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረትም በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ የቀጣናው አዋኪ ከሆነው ከኤርትራው ገዥ ፓርቲ በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ሲል ሀገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በጽንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡ ይኸውም የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ጽኑ እና ቁርጠኛ እምነት መያዙ መቻሉ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነጻ ልትሆን የምትችለው፤ ፈጣን የምጣኔ ሃብት ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄዱና ህዝቡም በየደረጃው የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን እንደሆነ በጥብቅ ያምናል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ካሁን በፊት ዘላቂ የልማትና ድህነት ቅነሳና ፈጣን ዘላቂ ልማት ድህነትን የመቀነስ ብሎም የማጥፋት ዕቅድ እንዲሁም ሌሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራሞች በሚገባ ለማሳካት ተችሏል፡፡

ፖሊሲው ኢንቨስትመንትን በመሳበ ረገድም ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ሁላችንም እንደምናውቀው አንድ ሀገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት ለማለት በርካታ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሠላምና የተረጋጋ ፖለቲካ፣ የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ የመሰረተ – ልማት አውታር፣ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ በቂ የሰለጠነና ውጤታማ የሆነ ሰው ኃይል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያሳካ ፖሊሲና ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራችን ውስጥ ሠላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መኖሩ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋና ፈጣን ዕድገት ማሳየቱ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የመሠረተ ልማት አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሆናለች፡፡ እነዚህ ውጤቶች የተገኙት ገፅታችንን በተገቢው መንገድ ገንባት በመቻላችን በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።