Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግብፅ የፓርላማ ውሳኔ ሕዝቡን አስቆጥቷል

0 328

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግብፅ ፓርላማ በቀይ ባህር ላይ የሚገኙ ሁለት ደሴቶች ለሳዑዲ አረቢያ እንዲሰጡ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የአገሪቱ ሕዝብ ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ ቲራን እና ሳናፊር የተባሉት ሁለቱ ደሴቶች ለሳዑዲ አረቢያ ተላልፈው ሊሰጡ መሆናቸው ያበሳጫቸውና ለታቃውሞ አደባባይ የወጡ ግብፃውያንም ሳዑዲ ለግብፅ ለምታደርገው እርዳታ የግብፅ መንግሥት ደሴቶቹን ሸጠላት በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

የፓርላማው አፈ ጉባኤ አሊ አብደላል፣ ውሳኔውን ለማሳለፍ የሚያስፈልገው ድምፅ እንደተገኘና ውሳኔው የግብፅና የሳዑዲ አረቢያ የባህር ወሰን አከላለል አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤቱ የመከላከያና የብሔራዊ ደህንነት ኮሚቴ የደሴቶቹን መሰጠት በሙሉ ድምፅ ደግፎታል፡፡

የደሴቶቹን ለሳዑዲ አረቢያ ተላልፈው መሰጠት ከጅምሩ አንስተው ሲቃወሙ የነበሩ የአገሪቱ የምክር ቤት አባላትም የመጨረሻው ውሳኔ በተላለፈበት ዕለትም ድምፃቸውን ጎላ አድርገው ውሳኔውን ሲቃወሙ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ሀተም አልሃሪሪ የተባሉ የምክር ቤት አባል “ዛሬ ለግብፅና ለግብፃውያን አስከፊ ቀን ነው፤ ግብፅ የግዛቷ አካል የሆኑትን ደሴቶች አጣች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ውሳኔውን በመቃወም ምክር ቤቱን ጥለው እንደወጡ ተዘግቧል፡፡

አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ያሰሙ ግብፃውያን በበኩላቸው ሳዑዲ አረቢያ የምትባል አገር ከመመስረቷ በፊት ጀምሮ ደሴቶቹ የግብፅ ግዛት አካል እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ውሳኔውን ተቃውመው አደባባይ ከወጡት ዜጎች መካከልም ጋዜጠኞችን ጨምሮ ጥቂት ሰልፈኞች እንደታሰሩ ተገልጿል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦችም ያለፈቃድ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግና የአገሪቱን ፕሬዝዳንት በመሳደብ ይከሰሳሉ ተብሏል፡፡

የፕሬዝዳንት አብደልፋታህ አልሲሲ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው “ሰውየው ሳዑዲ አረቢያ ለምታደርግላቸው ድጋፍ ሕጋዊዎቹን የግብፅ ግዛቶች በገፀበረከትነት አቅርበዋል” ሲሉ ይከሷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ በበኩላቸው፣ ደሴቶቹ የሳዑዲ አረቢያ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ከመናገር አልቦዘኑም፡፡

ፓርላማው ባለፈው ዓመት የደሴቶቹን ለሳዑዲ አረቢያ መሰጠት የወሰነውን ውሳኔ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ቢቃወመውም ፓርላማው ውሳኔው የእኔ ነው በማለት ክርክር አድርጎ በአብላጫ ድምፅ አሳልፎታል፡፡ የመጨረሻው ውሳኔ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ነው ቢባልም ፕሬዝዳንቱ ለፓርላማው ውሳኔ ይሁንታ እንደሚቸሩት ይጠበቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግብፅ ሁለቱን ደሴቶች ለሳዑዲ አረቢያ አሳልፋ ስትሰጥ በይሁንታው ውስጥ የሚካተቱ ተጨማሪ ስምምነቶች እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡

የቲራን እና የሳናፊር ደሴቶች ለሳዑዲ አረቢያ እንዲሰጡ አገራቱ ከስምምነቱ ላይ የደረሱት የሳዑዲው ንጉስ ሳልማን ቢን አብደልአዚዝ አልሳዑዲ እ..አ በሚያዝያ 2016 ግብፅን በጎበኙት ወቅት እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲን ከስልጣን አስወግደው እርሳቸው መንበሩን እንዲይዙ ዋነኛ አጋራቸው እንደነበረች አይዘነጋም፡፡

..አ በ1956 እና በ1967 እስራኤል ሁለቱን ደሴቶች ከግብፅ ነጥቃቸው እንደነበርና መልሳ ለግብፅ መስጠቷ የሚታወስ ነው፡፡ ከግብፅ ጦር ኃይል ውጭ ነዋሪ ህዝብ የሌላቸው ደሴቶቹ ለሳዑዲ አረቢያ ተላልፈው መሰጠታቸው በቀጠናው ሌላ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡

አንተነህ ቸሬ

addiszemen

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy