Artcles

የፌዴራል ስርዓቱን በፅናት እንያዝ

By Admin

June 08, 2017

የፌዴራል ስርዓቱን በፅናት እንያዝ!

 

አሜን ተፈሪ

የፌደራል ሥርዓቱን ህገ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ እንዳንድ ውስንቶች ያሉ ቢሆንም ህገ መንግስቱ የሐገራች፤ የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ መሠረት ሆኖ፤ ሐገራችን በትክክለኛው ጎዳና የምታደርገውን ጉዞ የሚመራ የብልጽግና ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስት ሐገራችን ለብዙ ዘመናት ያጣችውን ብዙነትን የማስተናገድ ዕድል በማመቻቸት ረገድ ትልቅ ስኬት አቀዳጅቶናል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት እንዲከበር ያደረገ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት አስችሎናል፡፡

 

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የመጀመሪያው፤ ሐገሪቱን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገው እና ለሦስት አስርት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነትን እንዲቆም ማድረጉ ነው፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ የብሔሮችን ግንኙነት በማሻሻል ከደርግ ውድቀት በኋላ አንዛዣብቦ የነበረው የመበታተን አደጋ እንዲወገድ ማድረግ ችሏል፡፡ ጠብመንጃ ያነሱ ኃይሎች መሣሪያ ለማስቀመጥ ፈቃደኛ እንዲሆኑ እና በአዲሱ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን እንዲነሳሱ አድርጓል፡፡ በዚህም የእርስ በእርስ ጦርነት የመነሳት ዕድሉን በእጅጉ ገድቦታል፡፡ በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታ ሰፊው የሐገሪቱ ህዝብ ሰላም እና መረጋጋትን እንዲያጣጥም አድርጎታል፡፡

 

የፌዴራል ስርዓቱ የኢትዮጵያን የብሔር-ብሔረሰብ ብዙነት ከልብ መቀበሉ፤ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ማህበራዊ ትስስር እና ብሔራዊ ውህደቱን እንደሚያጎለብተው ይታመናል፡፡ የብሔር-ብሔረሰቦችን የመከባበር እና የመደጋገፍ ስሜት በማዳበር፤ በመካከላቸው የነበረውን የመቃቃር ስሜትን አስወግዶታል፡፡

 

ለዘመናት የቆየውን የአንድ  ቡድን ባህላዊ እና ፖለቲካዊ የበላይነት በእኩልነት እንዲተካ አድርጓል፡፡ ሌሎችን በመጫን የባህል እና የማንነት መዋጥ አደጋን አስወግዷል፡፡ ማንነትን የሚደፈጥጥ ማዕከላዊነትን በማፈራረስ፤ ሁሉም በቂ ፖለቲካዊ አየር የሚያገኝበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የአናሳዎችን ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክን የማናናቅ እና ብሔር-ብሔረሰቦችን ክብር እና ማዕረግ የሚያዋርደው ሁኔታ እንዲለወጥ አድርጓል፡፡ ከሁሉም በላይ ያልተመጣጠነ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት በፍትሐዊነት ለሁሉም እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ በሐገሪቱ የሚገኙ በርካታ አናሳ ብሔረሰቦች የሚገለሉበትን ሁኔታ በመሻር፤ ለዘመናት የተገፉ አናሳዎችን እኩልነት በማረጋገጥ፤ የአናሳዎች ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ እውቅና የሚያገኙበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

 

በፌዴራሉ ስርዓታችን አናሳዎች በፖለቲካዊ መዋቅሩ የተሻለ ውክልና ማግኘት ችለዋል፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በብሔራዊ የፖለቲካ ሂደት ውክልና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሐገሪቱ የቋንቋ፣ የሐይማኖት እና የባህል ቡድኖች ወኪል የሚሆኗቸውን ሰዎች በሁሉም መቋቅሮች ለማየት የቻሉበትን ዘመን ፈጥሯል፡፡ የተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች፤ የሐገሪቱን መልክ ይዘዋል፡፡

 

በሐገሪቱ ታሪክ ሌላ ወደር በሌለው መጠን፤ በሥራ አስፈጻሚው አካል ሙሉ ቁመና የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እና ሐይማኖቶች በግልጽ የሚታዩበትን ዕድል አስገኝቷል፡፡ የፌዴራሉ መንግስት ተቋማት እና የፐብሊክ ሰርቪሱ በየጊዜው እያደገ በሚሄድ መጠን ብዙነታችን የሚንጸባረቅበት መድረክ ሆኗል፡፡

 

ሁሉንም አናሳዎች ባይሆን የሚበዙት የብሔራዊ ፕሮጀክቱ አካል የመሆን ስሜት እና የመካተት አመለካከት እንዲፈጠር ያደረገው ይህ የፌዴራል ስርዓት፤ ብሔር ብሔረሰቦች የእኩል ተጋሪነት እና የእኩልነት መብት እንዲጎናጸፉ ያደረገ በመሆኑ፤ ሁሉም ዜጋ ራሱን የኢትዮጵያ ሙሉ ዜጋ አድርጎ የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የሐገሪቱን ብሔር-ብሔረሰቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት በእጅጉ እንዳሻሻልና አንዱ ለሌላው እውቅና የመስጠት አመለካከት እንዲዳብር ያደረገው ህገ መንግስታዊ ለውጥ፤ የተለያዩ ብሔሮች ያጡትን የክብር እና የኩራት ስሜት ለማግኘት አስችሏቸዋል፡፡

 

አዲሱ የፌደራል ሥርዓት የራስን አካባቢ በራስ ማስተዳደር የሚያስችል ማዕቀፍ በመፍጠር አናሳዎች ፖለቲካዊ ሥልጣን እንዲይዙ አድርጓል፡፡ በታሪክ ዘመናት የተጣቃሚነት ዕድል ያልነበራቸው አናሳዎች፤ ሚዛናዊ የሐብት እኩል ተጠቃሚነት ዕድል እንዲያገኙ እና የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጠናከር አድርጓል፡፡

 

ህገ መንግስቱ የብሔር ቡድኖች ከየራሳቸው የማንነት ክበብ አሻግረው እንዳይመለከቱ ወይም የየራሳቸውን ማንነት አጥብቀው እንዲይዙ በማበረታታት የሐገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች አብሮ ለመኖር የሚያስችላቸውን የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለአደጋ የሚያጋላጥ አካሄድ ይዟል በሚል የሚወቅሱ ወገኖች ቢኖሩም፤ አዲሱ ህግ መንግስታዊ ስርዓት የህዝቡን ሁለንተናዊ ህይወት ምን ያህል እንደ ቀየረው በግልጽ ለመገንዘብ የዳር ሐገር ህዝቦችን ህይወት መመለከት በቂ ነው፡፡

ጋምቤላን ቤኒሻንጉልን፣ አፋር እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብን ሁኔታ መመለከት ጠቃሚ ነው፡፡ ለፌደራላዊ ስርኣቱ ምስጋና ይግባውና፤ ህገ መንግስቱ ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ድንጋጌ ያለው ነው፡፡ ይህም የመሐል ሐገር ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ፤ እንደተጠቀሰው የዳር አገር ህዝቦችም በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና ከሐገሪቱ ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ አስተዳደር ተፈጥሯል፡፡

በማህበራዊ መስክ በትምህርት እና በጤና ረገድ የተፈጠረው ለውጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቂ ይሆናል፡፡ የአናሳ ብሔረሰቦች ቋንቋ በተለይ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት መስጫ ቋንቋ ለመሆን በቅቷል፡፡ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ፣ እና በኦሮሚያ ክልሎች የአርብቶ አደር አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአርብቶ አደር ልጆች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡ ክልላዊ የትምህርት ሚዲያዎች የተስፋፉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡

ይህ አዲስ ክስተት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ልጆቻችን ከእኛ የተለዩ ሆነዋል፡፡ ከተዛባ አመለካከት ተጠብቀው አድገዋል፡፡ ከሐገሪቱ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ከልጅነታቸው ጀምረው ተዋውቀው ስለሚያድጉ፤ ሥነ ልቦናቸው በአንድነት ስሜት የታነጸ ይሆናል፡፡ በእውነት ልጆቻችን ይበልጡናል፡፡ ከእኛ ከወላጆቻቸው በተለየ የአስተሳሰብ ዘዬ እያደጉ ነው፡፡ ከፊውዳላዊ እሴቶች እና ከአብዮት እብደቶች ተጠብቀው፤ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ታንጸው ማየት ደስታ ነው፡፡ ሆኖም ልጆቻችን በፌዴራላዊ ስርዓታችን ከሚስተዋሉ አንዳንድ መጥፎ አዝማሚያዎች እና ጉድለቶች ተጠብቀው እንዲያድጉ መሥራት ይኖርብናል፡፡ የሚታዩ ችግሮችንም በቶሎ ማረም ይገባናል፡፡ ከትናንት የተሻገሩ ጸረ- ዴሞክራሲያዊ እሴቶች እና ባህሎች ወደ ልጆቻችን እንዳያልፉ መትጋት ያስፈልገናል፡፡ ይህን ካደረግን፤ በእውነት የሐገራችን መጻዒ ጊዜ በጣም ብሩህ ይሆናል፡፡  እነዚህ ክቡር ፌደራላዊ እሴቶች፤ ወላጆቻችን ባወረሱን ድንቅ የታሪክ ቅርስ መደብ ላይ ሲያድጉ የሚፈጠረው ነገር ያስደስታል፡፡ እናም የፌደራል ስርዓቱን በፅናት መያዝ ይህን ደስታ ዘላቂ ያደርጋል፡፡