Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሰኔ ወር መጨረሻ ለባለዕድለኞች ይተላለፋሉ- ሚኒስቴሩ

0 614

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሰኔ ወር መጨረሻ ለባለዕድለኞች በዕጣ እንደሚተላለፉ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ገለፁ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

ዶክተር አምባቸው ቤቶቹን በዕጣ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ርክክብ እየተደረገ ሲሆን፥ ስራውን ለማጠናቀቅ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

ቤቶቹን በሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንት ለባለዕድለኞች በዕጣ የማስተላለፍ ስነስርዓትን ለማካሄድም ፕሮግራም መያዙን ነው ዶክተር አምባቸው የገለፁት።

ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በዕጣ ከሚተላለፉት ቤቶች መካከል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ርክክብ ያልተደረገባቸውን ሁለት ብሎኮች፥ ለመረካከብና በቅርቡ ስራውን ለመጨረስ ከባንኩ ጋር መነጋገራቸውን አንስተዋል።

ዶክተር አምባቸው እነዚህን ሁለት ብሎኮች የመረካከብ ስራ የሚዘገይ ከሆነ እንኳ፥ ከሰኔ ወር መጨረሻ እስከ ሃምሌ ወር መጀመሪያ ባሉት ሳምንታት ለባለዕድለኞች እንዲተላለፉ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

በሌሎች የቤት መርሃ ግብሮች የተጀመሩ 20 ሺህ 932 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ 69 በመቶ መድረሱን፥ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል፡፡

የፋይናንስ አቅም ማነስ፣ የፕሮጀክት ግንባታ አስተዳደር ውስንነት እና የተቋራጮች የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ቤቶችን በሚፈለገው ጊዜ ግንበቶ ለማስተላለፍ እንዳይቻል ካደረጉት ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል።

የፋይናንስ አቅርቦትን በተመለከተም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በጀት በማቅረብ የቤቶቹ ግንባታቸው እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ2008 ዓ.ም ሃምሌ ወር መጨረሻ 1 ሺህ 290 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ እጣ ይወጣባቸዋል ከተባለ ቢቆይም እንደ ባንክ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር መደረግ ያለበት ዝግጅት ባለመጠናቀቁ ዘግይቷል መባሉን ሀምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም መዘገቡ ታወሳል።

በያዝነው ዓመት መስከረም ወር በሰንጋተራና ክራውን ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቀ የ40/60 ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ማስታወቁ አይዘነጋም።

በሰንጋተራና ክራውን ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 1 ሺህ 292 ቤቶች ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ነበር በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተመረቀው።
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በ2009 በጀት ዓመት 18 ሺህ 496 የ40/60 ፕሮግራም ቤቶችን እንደሚያስተላልፍ ቢገልፅም እስካሁን የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አልወጣም። FBC

በበላይ ተስፋዬ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy