Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ5 ሚሊየን ብር የሂሳብ ሰነድ መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተቱ ግለሰቦች በ17 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

0 521

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከደንበኞች የቁጠባ ገንዘብ ያጭበረበሩት 95 ሺህ ብር እንዳይታወቅባቸው የ5 ሚሊየን ብር የሂሳብ ሰነድ መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተቱ ሁለት ግለሰቦች በ17 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

ውሳኔውን ያስተላለፈው በደቡብ ክልል የከንባታ ጠንባሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።

ተከሳሾቹ 1ኛ ገዛኸኝ ድጉና 2ኛ ታዲዮስ አለኖ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ በከንባታ ጠንባሮ ዞን ውስጥ ነዋሪነታቸው ያደረጉ ናቸው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ በዞኑ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ብድርና ቁጠባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሂሳብና የግዥ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ ደንበኞች ገንዘብ ወደ ተቋሙ ሲያስገቡ በቁጠባ ደብተሩና ለተገልጋዮች በሚሰጥ ደረሰኝ ላይ ትክክለኛ የገንዘብ መጠኑን በማስፈር ለተቋሙ የሚቀረው ደረሰኝ ላይ ገንዘብ በመቀነስ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ ቆይተዋል።

10 ሺህ ብር ለመቆጠብ ከመጣ ደንበኛ 8 ሺህ ብር በመወሰድ 2 ሺህ ብር ብቻ እንደቆጠበ ማስመሰላቸው ነው በክሱ የተገለፀው።

የብድርና ቁጠባው ድንበኞች የቆጠቡትን ገንዘብ ለማውጣት ወደ ተቋሙ ሲመጡ በቁጠባ ደብተራቸው የሰፈረውና በተቋሙ በሚገኘው ደረሰኝ መካከል ልዩነት በመምጣቱ ደንበኞች ቅሬታ ያቀርባሉ።

ተቋሙም አጠቃላይ የሂሳብ ኦዲት ስራ ማከናወን ይጀምራል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በሂደቱ 95 ሺህ ብር ማጉደሉ ይደረስበታል።

ቀሪ የኦዲት ስራ እየተሰራ በሚገኝበት ጊዜ 1ኛ ተከሳሽ 2ኛ ተከሳሽን ከደንበኞች ሂሳብ በማበላለጥ ካጭበረበረው ገንዘብ እንደሚያካፍለው በመግለፅና በማስማማት ኦዲት የሚደረጉ ሰነዶችን ለመስረቅ ይስማማሉ።

በስምምነታቸው መሰረት ኦዲት እየተደረገ ከሚገኘው ሰነድ የ5 ሚሊየን ብር ሰነድ ከቢሮ ሰርቆ በማውጣት መፀዳጀ ቤት ውስጥ ይከታሉ።

ፖሊስ ባደረገው ምርምራ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀማቸው ተረጋግጧል።

ግለሰቦቹ በፈፀሙት ከባድ የእምነት ማጉደልና ሰነድ የማጥፋት የሙስና ወንጀሎች አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ በከንባታ ጠንባሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምን በማለት ክደው ቢከራከሩም የጠቅላይ አቃቤ ህግ ማስረጃን ማስተባበል አልቻሉም፤ በዚህም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ በመያዝ ሌሎችን ያስተምራል፤ ተከሳሾችን ያርማል በማለት በ17 ዓመት ፅኑ እስራትና በ35 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

መረጃውን ከደቡብ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ደሳለኝ ብሩ አድርሰውናል። FBC

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy