Artcles

ድርቁን ለመቋቋም የሚደረገው ጥረት

By Admin

June 26, 2017

ድርቁን ለመቋቋም የሚደረገው ጥረት

                                       ሰለሞን ሽፈራው

ሰሞኑን ከወደ ባህር ማዶ በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት ስለተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጉዳይ የሚያወሳ ዜና ነበር፡፡ በቢቢሲ እንደተዘገበ የተነገረለት ሰሞነኛ ዜና “በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ተጠቂዎችን ለመርዳት እየተደረገ ያለው ጥረት ባጋጠመ የምግብ እህል ምክንያት ሊስተጓጎል እንደሚችል የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ” የሚል ነው፡፡ ይህ መረጃ ነባራዊ እውነታውን ያላገናዘበና ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስቴር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገልጸዋል፡፡

በአሁን ወቅት የዕለት ደራሽ ምግብ  ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከታመነባቸው፤ ወደ 7.8 ሚሊዮን ገደማ ዜጎቻችን መካከል ከአምስት ሚሊዮን ለሚበልጡ ወገኖች ማንኛውም እርዳታ እያቀረበ ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በመሆኑም የተረጂዎች ቁጥር ታሳቢ ያደረገ በቂ የምግብ እህል ክምችት መኖሩንም ጭምር ክቡር ሚኒስቴሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለፋና 98.1 በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን አጠቃላይ ቁጥር ሰባ አምስት በመቶ ያህሉን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቡ በሚሸፍኑት ወጪ እየተገዛ የሚመጣ የምግብ እህል አቅርቦት እንዲደርሳቸው የሚደረግበት አግባብ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ቀሪዎቹ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የድርቅ ተጠቂ ኢትዮጵያውያን፤ በዓለም የምግብ ድርጅትና የካቶሊካውያን ክርስቲያናዊ ተራድኦ በሚባል ሌላ አንድ የውጪ በጎ አድራጎት ተቋም አማካኝነት እንደሚረዱም አክለው ገልጸዋል፡፡

“ስለዚህ ሰሞኑን ለድርቅ ተጠያቂዎች ሲቀርብ የቆየው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንዳለቀና 7.8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለከፋ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተደርጎ የውጪ ሚዲያዎች ላይ የቀረበው ዜና ስህተት እንደሆነ ለመግለጽ ነው የፈለግኩት” ያሉት ዶክተር ነገሪ፤ ስህተቱን የፈጠረው ምክንያት የዓለም ምግብ ድርጅት ሰዎች ለራሳቸው ቀጣይ የምግብ እህል አቅርቦት የሚያስፈልጋቸውን የዕርዳታ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የተድበሰበሰ መረጃ በመስጠታቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

“ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚገኝ ድጋፍና ዕርዳታ መጣም ቀረም ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ለምግብ እህል እጥረት የተጋለጡ ዜጎቿ እንዳይራቡ አቅሟን አሟጣ እስከ መጠቀም የሚደርስ ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች እንጂ እነርሱን ተማምነን አንቀመጥም” ሲሉ የተደመጡት ሚኒስቴሩ፤ መሰል የድርቅ አደጋ በተከሰተ ቁጥር የለጋሽ ሀገራትን እጅ መጠበቅ እንደማይገባ ያመነው የኢፌዴሪ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ፈርጀ ብዙ የልማት እንቅስቃሴ ስለመጀመሩም ጭምር አመልክተዋል፡፡ ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋና በህዝባችን ላይ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ ቀውስ ለመቋቋም እንችል ዘንድ ዘላቂ መፍትሔ ስለማፈላለግ አስፈላጊነት ጉዳይ ምን ያህል ታስቦበታል? በሚል ጥያቄ ዙሪያ  ያለኝን አስተያየት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት የሚነገርለት “አሊኖ” የተሰኘ ተፈጥሯዊ ክስተት በሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ ምክንያት እየተባባሰ የመጣውን ድርቅና እንዲሁም ድርቁን ተከትሎ ለሚያጋጥም የምግብ እህል እጥረት ችግር የምንጋለጥበትን ድግግሞሽ ለታዘበ ሰው ሁሉ፤ ጉዳዩ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የሀገራዊ ህልውና ጉዳይ ወደ መሆን ደረጃ ስለመድረሱ መረዳት አያዳግትም ማለት ይቻላል፡፡

ድርቅ አመጣሹ የምግብ እጥረት በከፋ መልኩ ሲደጋገም የሚስተዋልባቸው የሀገራችን ክፍሎች ነዋሪ የሆነው የገጠሪቷ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ እንኳንስ የዕለት ጉርስ፤ የዓመት ልብስ ማሟያ ሊቸገር ሌሎችን ለመመገብ የሚያስችል መጠነ ሰፊ የእርሻ መሬትና የተትረፈረፈ የውሃ ሀብት እንዳለው ሲታሰብ፤ ጉዳዩን አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የተሻለ አብነት ይሆናል የምለውም በተለይ የአሁኑ የድርቅ አደጋ ግንባር ቀደም ሰለባ ተደርጎ የሚወሰደው የኢትዮጵያ ሱማሌ ብሔራዊ ክልል አርብቶና ከፊል አርሶ አደር ህዝብ ነው፡፡

ክልሉ ያንን ሁሉ የተትረፈረፈ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት ይዞ፤ በዝናብ እጥረት ምክንያት ለሚከሰት የድርቅ አደጋ እየተጋለጠና ለተደጋጋሚ የማህበራዊ ቀውስ አዙሪት እየተዳረገ ህልውናው ሲፈተን ማየት በእርግጥም እንቆቅልሽ እንጂ ሌላ ስም አይገኝለትምና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዋቢ ሸበሌን ጨምሮ፤ እንደ ገናሌና ዳዌ ያሉት ትልልቅ ተፋሰሶች የውሃ ሀብቱን በመጠቀም  የመስኖ እርሻ ልማት ስራ ተጠናክሮ ቢቀጥል፤ እንኳንስ የራሱን ህዝብ ኢትዮጵያ ለመመገብ የሚያስችል ውጤት ከማምጣት የሚያግደው ምንም ዓይነት አይኖርም፡፡ በመሆኑ በጎዴ ዞን አንድ አካባቢ ያለውን እጅግ የተመቸ ድንግል መሬት ብቻ አይቶ መፍረድ አይከብድም ባይነኝ፡፡

ስለዚህም፤ እንደኔ እንደኔ ቢያንስ ከአሁን በኋላ እንኳን የተትረፈረፈ የውሃ ሀብት ላይ ተቀምጠን እየኖርን በዝናብ እጥረት ምክንያት ለሚከሰት የድርቅ አደጋ እየተጋለጥን ህልውናችን ሲፈተንና እጃችንን የምግብ እህል ዕርዳታ ለመጠየቅ ወደ ባለጸጋዎቹ ምዕራባውያን ሀገራት ስንዘረጋ የሚስተዋልበት አግባብ መቆም እንዳለበት ነው የሚሰማኝ፡፡ ሰለዚህ የየክልሉ መንግስታት በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች ስም የሚመደበውን የዓመት በጀት ለዚህ ለዚህ ዓይነቱ መሰረታዊ ቁምነገር እንዲውል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን በዚህ መንፈስ ይረዱልን ዘንድም አደራ ጭምር አቀርባለሁ፡፡

አለበለዚያም ግን፤ የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዘመናት ትግላቸው የተጎናጸፉትን ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት እንዳሻቸው እየሸራረፉ በማጓደል ለየግል ኑሮ መደላደል ሲሉ የክልላዊ መንግስት በጀትን ከመቆራመት ያለፈ ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የተረዱ የማይመስሉ ጥቂት ህሊና ቢስ የአመራር አካላት ስልጣን ላይ ስለተፈራረቁ ብቻ የለውጥ ሂደቱን “ስርነቀል” ሊያስኘው አይችልም፡፡ ስለዚህ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ ላይ የምትገኝ አገር ናት የሚል ቅን እምነት ያለን ዜጎች ሁሉ ይህን አቋማችንን አጠንክረን ለመቀጠል የሚያስችል የሞራል ብቃት እንዲኖረንም ጭምር፤ ድርቁ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል የሚለው ነጥብ ይሰመርበት፡፡ በተረፈ እኔ አበቃሁ፡፡