Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርቅ ወደረሃብ የማይለወጥበት አቅም ተገንብቷል!!

0 518

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድርቅ ወደረሃብ የማይለወጥበት አቅም ተገንብቷል!!

ዮናስ

አገራችን የተያያዘችው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግቦች በተሃድሶ የመጀመሪያ ዓመታት በግልፅ እንደተቀመጠው ፈጣንና ህዝብ የሚጠቀምበት ዕድገት ለማምጣት የሚያልሙ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት የተነደፈው ግብርና መር የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ኢኮኖሚያችን ባለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ አስችሏል፡፡ ከዚህ ዕድገት ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ያላሰለሰ ትግል የተካሄደ ቢሆንም፤ ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠመንና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቀው የድርቅ አደጋ በጸረ ድህነት ዘመቻው ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፏል። እንደዚያም ሆኖ ግን ትርጉም ያለው የውጭ እርዳታ ሳናገኝ በራሳችን አቅም ልንቋቋም መቻላችን በአገራችን ምን ያህል የተጠናከረ የኢኮኖሚ ግንባታ ሲካሄድ እንደቆየ የሚያመላክት ነው፡፡

ከግንቦት 20 ድል ማግስት ጀምሮ መንግስት በገጠር ዋናው የሀብት ምንጭ የሆነውን የአርሶ አደሩ ጉልበትና መሬት ይዞ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡   የአርሶ አደሩን የምርት ነፃ ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥና ለልማቱ ተፈላጊ የሆነውን ሙያዊ እገዛ በመስጠት የሃገራችን ገጠሮች ድህነት የሚቀበርባቸው አውድማዎች እንደሚሆኑ አመላካች የሆኑ አፈጻጸሞችም ከዚሁ ድል ማግስት ጀምሮ ተመዝግበዋል፡፡ የግብርና ምርት  ከነበረበት የ73 ሚሊዮን ኩንታል አመታዊ ምርት ተነስቶ በ2008 ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መድረሱን መንግስትና አለም አቀፍ ድርጅቶች አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ውጤት ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የስራስር ምግቦችንና የመስኖ ምርትን ሳይጨምር የተገኘ መሆኑ የእድገታችንን ልክ እና የፖሊሲያችንን ትክክለኛነት የሚያሳይ ነው፡፡

በዚህ ውጤት ታዲያ የኢትዮጵያ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ተነቃቅተዋል፡፡ ከተመፅዋችነት አስተሳሰብ ተላቀው በራሳቸው ጥረት አካበቢያቸውን አልምተው ለመጠቀም እንደሚችሉ የመተማመን መንፈስ አዳብረዋል፡፡  ምክንያቱም በዚህ እድገት የኢትዮጵያ ህዝቦች ንቁ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆኑ ዋነኞቹ ተጠቃሚዎችም በመሆናቸው ነው ፡፡

አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ዋስትና አግኝተው በመንግስት እየታገዙ ምርታማነታቸውን የሚጨምሩበት እድል ሰፍቷል፡፡ ምርታማነታቸው ከአመት ዓመት እየተሻሻለ ከራሳቸው ቀለብ አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ሰፊ ምርት ማግኘት ጀምረዋል፡፡ አርብቶ አደሮች ለአካባቢያቸው ተስማሚ የእድገት አቅጣጫ ተተልሞላቸው በእድገት ሂደት ላይ ናቸው፡፡ መንግስት በነደፈው የፖሊሲ አቅጣጫ የምርት ነፃ ተጠቃሚነት መብታቸው በመረጋገጡ የልፋታቸው ውጤት ተጠቃሚዎች ራሳቸው ሆነዋል፡፡ በግንቦት 20 ድል መርሆ እንደመንግስት ኋላቀርነቱን መፍታት የሚያስችል  ተሃድሶ ተደርጎ በመንደርደር ላይ ባለንበት ወቅት ደግሞ ሌላና የተያያዝነውን የጸረ ድህነት ዘመቻ የሚያንገራግጭ ከባለፈው አመት የቀጠለ ፈተና ተደቅኖብናል። ይኸውም ድርቅ ነው።

የሃገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን ይዞ መንግስት የመሰረተው ኢህአዴግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ቢሆንም በተቃራኒው ግን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የድርቅ ሰለባ መሆናችን አስገራሚም የሚያስጨንቅ ነው። አስገራሚም ይሁን አስጨናቂ  ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣን ክስተት እና ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ንብረት  ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምን ያህል አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚገለጸውም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ የምትገኘውን ሃገራችን ዛሬም ይልቁንም ተከታታይ ለሆኑ አመታት ቁም ስቅሏን ለማሳየት በመቻሉ እንደሆነ ልብ ይሏል። የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኤጄንሲ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን አስታውቋል። ነገርግን ይህ አኃዝ ከፍ ሊል እንደሚችል ደግሞ አስተያየታቸውን የሰጡን ምሁራን ተናግረዋል።  

ባልተለመደ መልክ ባለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት ለመከራ የዳረገን  ኤልኒኖ ጦሱ ከባድ እንደሆነ የበለጠ ለመገንዘብ ይልቁንም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ውጥረን መያዝ አማራጭ የሌለው አጀንዳ መሆኑን ለመገንዘብ እና የግንቦት 20ን ድል ለማስቀጠል ወደኋላ ተመልሰን ጥቂት አብነቶች ማስታወስ ተገቢ ይሆናል። የኢንዶኔዥያ ጫካዎች በ2015 በእሳት ለማጋየት የበቁት በኤሊኒኖ ምክንያት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የአየር ብክለት ከ100 ሺዎች በላይ ሕይወት ለህልፈት ተዳርጓል፡፡   

ኤልኒኖ በሃገራት የግብርና ምርትና ምርታማነትም ላይ ተጽእኖው የከፋ ነው ፡፡ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡት ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካዊያን የክፋቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ቀጥሎም ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሴቶ፣ ናሚቢያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ማዳጋስካር ስፋቱ ይለያይ እንደሆነ እንጂ ግብርናቸው የኤልኒኖ ሰለባ ሆኗል፡፡  

ኤልኒኖ ያስከተለው ጉዳት ሳያገግም፣ ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት እየጠበቀ የሚመጣውና ጎርፍ የሚያስከትለው ላሊና ሌላ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በኤልኒኖ ለተጎዱ አገሮች ላሊና የዝናብ ተስፋ ቢሆንም፣  ላሊና የሚያስከትለው ከባድ ዝናብ ለጎርፍ መንስዔ ነው፡፡ ሰብሎችን ያወድማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ውኃ ወለድ የከብት በሽታዎችን ያስከትላል፡፡

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት ከተከሰተው ድርቅ ዛሬም አላገገመችም፡፡ ከብቶች አልቀዋል፣ ሰዎች የምግብ ተረጂ ሆነዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. መጀመሪያ 5.6 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂዎች የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከስድስት ወራት በኋላ ወደ 7.8 ሚሊዮን ማሻቀቡን መንግስት አረጋግጧል፡፡  ችግሩን የከፋ የሚያደርገው በእነዚህ የድርቅ ሰለባ የሆኑ አካባቢዎች በአየር ንብረቱ ምክንያት የተራዘሙ ደረቅ ወራት በመኖሩ ምክንያት የዝናብ እጥረቱም የተራዘመ የሚሆን መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የዕርዳታ አቅርቦቱን ማፍጠን የግድ ይሆናል ማለት ነው። ፍጥነት ከሌለው ተጎጂዎች ለምግብና ለውኃ እጥረት ይጋለጣሉ፡፡ ዕርዳታ ዘግይቶ ቢደርስ እንኳን ለማገገም አይችሉም፡፡ ስለሆነም በመንግስት በኩል በምግብ ዕጥረት የተጎዱ ሕፃናት ሕይወታቸውን ከማትረፍ አልፎ ቀድሞ ወደነበሩበት ለመመለስ እየተደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ለምን ቢሉ ይዞት የሚመጣው አደጋ በአንድ የሚወሰን ሳይሆን ተያያዥና በርካታ ስለሆነ ጥቂቶቹን እንመልከት።

በድርቅ ወቅት ከሚከሰቱ ችግሮች መካከል አንደኛው የጤና ጉዳይ ነው፡፡ በምግብ እጥረት በሚፈጠረው ጉዳት ምክንያት የሕፃናትና የአዋቂዎች ጤና በእጅጉ ከመቃወሱም በላይ፣  በቫይታሚኖች እጥረት የተለያዩ በሽታዎችን በማስከተል ሕይወታቸውን ለአደጋ ይዳርጋሉ፡፡ ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶችም እንዲሁ ይጎዳሉ፡፡ የድርቅ ተጎጂዎች በተገቢው ጊዜ ተገቢውን ዕርዳታ ካላገኙና አካባቢያቸው ንፅህና ከጎደለው ወረርሽኝ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ይፈጥራል፡፡በመንግስት በኩልም ይኸው ግንዛቤ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ አንድ ነገር ሆኖ በተቀናጀ መልክ በመስራት ረገድ እጥረቶች እንዳሉ ተመልክቷልና ከወዲሁ መንቃት ያስፈልጋል።

በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት 30 ዓመታት ከታዩት የከፋ ነው ቢባልም፣ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እንኳን ሳይገኝ መቋቋም መቻሉ ለአደጋ የማይበገር መንግስት መፈጠሩን ቢያመላክትም ለአደጋ የማይበገር ህብረተሰብ ግን ገና አልተፈጠረም ፡፡ ዛሬም  የዝናብ ጥገኛ የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች አሉን።ስለሆነም በአደጋ የማይበገር ህብረተሰብ ለመፍጠር በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ ሥፍራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ከዝናብ ጠባቂነት ማላቀቅ ያስፈልጋል። የእድገታችን ልክ የሚሻው በድርቅ የሚጠቃ አርሶአደር እና አርብቶአደሮችን ሳይሆን ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ትርፍ አምራች የሆኑ አርብቶና አርሶ አደሮችን ነው፡፡ስለሆነም ሰፊ ለም መሬት፣ መጠነ ሰፊ ውኃ፣ ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የአየር ፀባዮች ባሉበት አገር ውስጥ ድርቅ የማይከሰትበትን አማራጮች ሁሉ በስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።በርግጥ አሁን ከመንግሥትም ሆነ ከሃገሪቱ ዜጎችና ባለሃብቶች የሚጠበቀው የድርቅ ተጎጂዎችን በፈጣንና በተቀናጀ ጥረት መታደግ ነው፡፡ ይህ ጥረት ፍትሐዊ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ደግሞ የመንግሥት አሠራሮች በሙሉ ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡ የዕርዳታ አቅርቦቱም ሆነ የመረጃ ቅብብሎሹ በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡

በእርግጥ በሃገራችን ድርቅ ረሀብ  የማይሆንበት  ሁኔታ  ተፈጠሯል። ግን ደግሞ የድርቅ ተጎጂው ቁጥር ወደ 7 ነጥብ 8 አድጓል። ይህ አሃዝ በርካታ ቢሆንም ህዝብና መንግስት በቅርበት በመስራት ዜጎችን መታደግ እንደሚችሉ ከአምናው ሁኔታ መገንዘብ ስለሚቻል አሁንም ይህንኑ በተጠናከረ መልኩ መድገም ያስፈልጋል። መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው ከሰሩ ለሁሉም ችግሮቻችን መፍትሄ እንደሚሰጡ ባለፈው አመት የታየው ልምድ ያሳያል። የአገራችን ህዝቦች የመረዳዳት ባህላቸውን  (የአማራና የትግራይ ክልሎች  በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ያደረጉትን ድጋፍ) እንዲሁም በኦሮሚያ ያሉ በድርቅ ያልተጎዱ ዞኖችና ወረዳዎች እያደረጉ ያሉትን ድጋፎች  ሌሎቹም ክልሎች ሊያደርጉት ይገባል። በተመሳሳይ በርካታ ባለሃብቶች  በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች  እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ  ሌሎቹም ባለሃብቶች ሊያደርጉት ከተገባ ጊዜው አሁን ነው። ምክንያቱም ድርቁ በተከታታይ ዓመትም ሊቀጥል እንደሚችል አንዳንድ የሜትሪዮሎጂ ትንበያዎች ያመላክታሉ።  የግብርና ባለሙያዎቹ ደግሞ እንደ ዜጋ የሚያደርጉት ሰብአዊ እርዳታ እንደተጠበቀ ሆኖ አርብቶና አርሶ አደሩን በማስተባበር ጠብ የምትለውን የዝናብ  ወሃ የማቀብ ስራ መስራት  ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ በመጠቀም  የመስኖ ስራዎች ማከናወን ቁልፍ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። እንዲህ አይነቶቹን ተግባራት ሁሉም ከላይ በተመለከቱት አግባቦች እንደድርሻው ከተወጣ በግንቦት 20 ድል ለአደጋ የማይበገር ህብረተሰብ መገንባት  ይቻላል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy