Artcles

ድርድር በስልጣንና በችሎታ የተገደበ ነው

By Admin

June 24, 2017

ድርድር በስልጣንና በችሎታ የተገደበ ነው

ብ. ነጋሽ

በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር ወደድርድር ለመግባት አጀንዳዎችን በማጽደቅ ላይ ይገኛሉ። እስከአሁን በተደረጉ አጀንዳ የማጽደቅ ውይይቶች፣ አምስት የድርድር አጀንዳዎች ጸድቀዋል። ከእነዚህ መሃከል የምርጫና ተያያዥ ህጎች (የ1999 የምርጫ ህግ፣ የ2002 የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር አዋጅና የ2000 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ) ቀዳሚው የድርድር አጀንዳ ሆኖ ጸድቋል። ይህን አጀንዳ ኢህአዴግን ጨምሮ 17ቱም በድርድሩ ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በአጀንዳነት ያቀረቡት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ለማካሄድ ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት፣ ሁሉም የህዝብ ድምጽ በመንግስት ውስጥ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ማበልጸግ በመሆኑ ይህን አጀንዳ ወሳኝ ነው ብሎ መወሰድ ይቻላል።

ተደራዳሪዎቹ ያጸደቁት ሁለተኛ አጀንዳ፤ የጸረሽብርተኝነት ህግ፣ የበጎአድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ምዝገባ አዋጅ፣ የመረጃ ነጻነትና የመገናኛ ብዙሃን አሰራር አዋጅ ላይ የሚደረግ የህግ ማሻሻያን የሚመለከት ነው። እነዚህ አዋጆች በተለይ የጸረሽብርተኝነት እንዲሁም የበጎአድራጎት ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ምዝገባ አዋጆች ላይ የሚቀርብ ተቃውሞ፣ የተቃውሞ ፖለቲካ አፍ መፍቻ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

የትኞቹን የህጎቹን አንቀጽ፣ በምን ምክንያት እንደሚቃወሙ ለሁሉም ሊገባ በሚችል ግልጽ ቋንቋ የተናገሩ ፓርቲዎች ባይኖሩም፣ ህጎቹ አፋኝ ህጎች የሚል ቅጥል ተለጥፎባቸው ዋነኛ የተቃውሞ አጀንዳዎች ሆነው ቆይተዋል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ድርጅቶችና ማህበራትም ይህንኑ ተቀብለው የኢትዮጵያን መንግስት ማብጠልጠያ ሲያደርጉት ቆይተዋል። በመሆኑም ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ችግር አለባቸው የሚሏቸው የህጎቹ ድንጋጌዎች ላይ ለመደራደር ያነሱት ጥያቄ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳ መሆኑን ግን እጠራጠራለሁ።

ከዚህ ውጭ ያሉት የመደራደሪያ አጀንዳዎች የፍትህ አካላት አደረጃጃትና አፈጻጸም፣ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አሰራርን የሚመለከቱ እንዲሁም ብሄራዊ መግባባት የሚሉ ናቸው። በቀጣይ ውይይቶች ተጨማሪ አጀንዳዎችም ሊጸድቁ ይችላሉ በለን እንጠብቃለን። በዚህ ጽሁፍ በእነዚህ ለድርድር በጸደቁ አጀንዳዎች ዙሪያ አሰተያየት መስጠት አልፈልግም። ድርድሩ እስኪያበቃ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ ነው የሚል እምነትም የለኝም። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ልደራደርባቸው አልችልም እና/ወይም ለድርድር ሊቀርቡ አይችሉም በሚል ሳይቀበላቸው የቀሩ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ መሃከል የተወሰኑትን በዚህ ጽሁፍ ልመለከታቸው ወድጃለሁ።

ኢህአዴግ ለድርድር ሊቀርቡ አይችሉም እና/ወይም ልደራደርባቸው አልችልም ብሎ ሳይቀበላቸው ከቀራቸው አጀንዳዎች መሃከል፤ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን፣ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ማሻሻልን፣ የሃገሪቱን ድንበር፣ እንዲሁም የመሬት ፖሊሲን የሚመለከቱተ ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚህ መሃከል የተወሰኑትን እንመለከታቸው።

ከመሬት ፖሊሲው እንጀምር። ኢህአዴግ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የህዝብ ሃብት ነው የሚል አቋም እንዳለው ይታወቃል። ኢህአዴግ ይህን አቋም የያዘው በትጥቅ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ጭምር ነው። የትጥቅ ትግሉ አብቅቶ የኢፌዴሪ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ በተካሄዱ ምርጫዎች ላይም ይህን አቋሙን እንደአማራጭ ፖሊሲ አቅርቦ አብላጫ ድምጽ ማግኘት መቻሉ የታወቃል። የኢህአዴግ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ፖሊሲዎች በዚህ የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እርግጥ መሬት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ወሳኝ ስፍራ የነበረው ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በነገራችን ላይ በተለይ በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች በመሬት ይዞታ ፖሊሲ  ከኢህአዴግ ጋር ተመሳሳይ ሊባል የሚችል አቋም ያላቸው መሆኑ እንዲታወስ እፈልጋለሁ።

ሰሞኑን በድርድሩ ላይ የሚሳተፉ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሬት ይዞታ ፖሊሲን እንደርድድር አጀንዳ ሲያቀርቡ፣ ኢህአዴግ ይህ ጉዳይ ልደራደርበት የምችልበት አይደለም የሚል ፈርጠም ያለ አቋሙን ገልጿል። ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ ልደራደር አልችልም ሲል ጉዳዩ የፓርቲዬ ምሰሶ ነው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለ አቋሜን ሸርፌ ብሰጥ የፓርቲው ምንነት ይቀየራል፣ እናም ማንነቴን በሚለውጥ ጉዳይ ላይ አልደራደርም እያለ ነው። ድርድር ሰጥቶ መቀበል በመሆኑ ትንሽ እንኳን ቢሰጥ ህልውናውን የሚንድ ጉዳይ ላይ ላለመደራደር መወሰኑ ምክንያታዊ ነው።

ይህ ማለት ግን የመሬት ፖሊሲው ጉዳይ ሊነካ የሚችል አይደለም የሚለውን አያመለክትም። ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረው በመሬት ይዞታ ላይ ያላቸውን አማራጭ ፖሊሲ አቅርበው ለምርጫ መፎካካር ይችላሉ። ከኢህአዴግ ጋር የእኔ ይሻል የእኔ ክርክር ሊያደርጉበትም ይችላሉ፤ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረው ማለት ነው።

ኢህአዴግ ልደራደርበት አልችልም ያለው ሌላው ጉዳይ፣ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች መፍታትን የሚመለከት ነው። ይህ አጀንዳ አዲሰ አይደለም፤ ነባር፣ ብዙ የተባለበት የጠነዛ አጀነዳ ነው። አንዳንድ ተቃዋሚዎች ህጋዊ ሆነው በተንቀሳቀሱባቸው ዓመታት በሙሉ መሪዎቻችን፣ አባሎቻችን፣ ደጋፊዎቻችን . . . ታሰሩ የሚል ስሞታ ሲያቀረቡና ይህነኑ ለሌሎች አቀብለው ሲያስነግሩ መኖራቸው ይታወቃል። አንዳንዶቹ እንደውም ይህን ጉዳይ የመቃወሚያ አጀንዳ አድርገው ካላቀረቡ ህዝብ የሚረሳቸው ሁሉ ሳይመስላቸው አይቀርም። አንዳንዶቹ ህጋዊ ሰውነት አግኝተው ለመጀመሪያ ጊዜ ከህዝብ የሚተዋወቁት አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ታሰሩ በሚል መግለጫ ነው።

ሰዎች በፖለቲካ አቋማቸው የሚታሰሩበት ሁኔታ መቼም የትም ኖሮ አያውቅም የሚል አቋም የለኝም። ሰዎች በያዙትና በሚያራምዱት አቋምና አመለካካት፣ በገለጹት አመለካካት ምክንያት ብቻ ይታሰሩ፣ መታሰር ብቻ ሳይሆን ይገደሉ የነበረበትን ስርአት አይቻለሁ፤ የወታደራዊውን ደርግ ስርአት። ታዲያ በያዙት፣ ባራመዱትና በገለጹት ሃሳብ ምክንያት ብቻ የታሰሩ ሰዎች የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ናቸው።

አሁን ዋናው ጥያቄ በአሁኗ ኢትዮጵያ አምኖበት በያዘው፣ ባራመደውና በገለጸው አመለካከትና አቋም ብቻ የታሰረ ሰው አለ ወይ? የሚለው ነው። እርግጥ በፖለቲከኝነት የምናውቃቸው በቁጥጥር ስር ውለው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ፣ በይፋ የፍርድ ሂደት ጥፋተኛ ተብለው ተቀጥተው ቅጣታቸውን በመወጣት ላይ ያሉ ሰዎች መኖራቸው አይካድም። እዚህ ላይ አሁንም ዋናው ጉዳይ፣ እነዚህን ሰዎች ለመከሰስና ለቅጣት ያበቃቸው የያዙት፣ ያራመዱትና የገለጹት አቋም ነው ወይ? የሚለው ነው።

እንግዲህ፣ የዜጎች የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ በግል ወይም ከመሰሎች ጋር ተደራጀቶ የማራመድ፣ የመግለጽ፣ በአመለካካት ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር መብት በኢፌዴሪ ህገመንግስት ተረጋግጧል። በዚህ መሰረት በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በህዝባዊ ስብሰባ፣ በመገናኛ በዙሃን፣ በመጻህፍት . . . ከገዢው ፓርቲ ፖሊሲና ከኢፌዴሪ ህገመንግስት ድንጋጌዎች ጋር የሚጻረሩና የሚቃወሙ አቋሞች በይፋ ሲገለጹ ቆይተዋል። ከገዢው ፓርቲ አቋምና ከኢፌዴሪ ህገመንግስት ፍጹም ተጻራሪ የሆኑ አቋሞችና አመለካከቶች የምርጫ አጀንዳ ሆነው ፓርቲዎችና ግለሰቦች በክርክር ላይና ፖሊሲዎቻቻውን ሲያስተዋውቁ በይፋ ሲናገሩ ስንሰማ ቆይተናል። ይህን በማድረጉ የታሰረ፣ የተከሰሰና የተፈረደበት ግን አላየንም፤ አልሰማንም።

ፖለቲከኛ መሆን በወንጀል ከመጠየቅ አይከልልም። በመሆኑም በሃገሪቱ የተደነገጉ ህጎችን በመተላለፍ ወንጀል የተጠረጠሩ ስራቸው ፖለቲከኛ የሆኑ ሰዎች ግን ክስ ተመስርቶባቸውም፣ ቀጣት ተወስኖባቸውም ያውቃል። እነዚህ ግን የፖለቲካ እስረኞች አይደሉም። ህግ በመተላላፍ በወንጀል የተጠየቁ ናቸው። እናም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ስላሉ ይፈቱ የሚለው ጉዳይ ፖለቲከኞች ወንጀል ሰርተው ያለመጠየቅ ከለላ አላቸው ከማለት የተለየ አይደለም። ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ መሰረት የሆነውን የህግ የበላይነት የሚጻረር አቋም ነው። በመሆኑም በዚህ አጀንዳ ላይ እንደራደር የሚለው አቋም በህግ የበላይነት ላይ እንደራደር ከማለት የተለየ ሆኖ አይሰማኝም።

ሌላው ኢህአዴግ ከድርድር ውጭ ያደረገው ጉዳይ የሃገሪቱን ድንበር የሚመለከተው ነው። የአንድ ሃገር ድንበር ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ነው። በመሆኑም አንድ ፓርቲ፣ ገዢ ፓርቲም ቢሆን በመርህ ደረጃ ሊደራደርበት አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ የድንበር ጉዳይ የአንድ ሃገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ በሁለት ሃገራት መሃከል በሚፈጸም ስምምነት የሚወሰን በመሆኑ መንግስትም ቢሆን ከፓርቲዎች ጋር ሊደራደርባቸው አይችልም።

እናም ኢህአዴግ፣ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ በተለያየ ጊዜ ከአጎራባች ሃገራት ጋር የተፈጸሙ የድንበር ስምምነቶች ላይ በሰጠቶ መቀበል መርህ ሊደራደር በፍጹም አይችልም። በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ሊሰጥ፣ ምንም ሊቀበል አይችልም። እናም ይህ አጀንዳ ከድርድር ውጭ ይሁን በሚል የተያዘው አቋም ትክክል ነው የሚል እምነት አለኝ።

እንግዲህ ከድርድር ውጭ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። ሰሞኑን ተጨማሪ የድርድር አጀንዳዎችን እንደምንሰማው ሁሉ ከድርድር ውጭ የሚሆኑ አጀንዳዎችም ሊኖሩ ይችላሉ ብለን እንገምታለን። እናም እነዚህን ከድርድር ውጭ የሆኑና የሚሆኑ አጀንዳዎች በሌላ ጽሁፍ ላነሳ እንደምችል እየገለጽኩ በዚሁ አበቃለሁ።

በአጠቃላይ በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ወገኖች መሃከል የሚደረጉ ድርድሮች ላይ የሚቀርቡ የመደራደሪያ አጀንዳዎች በቅድሚያ በተደራዳሪዎቹ ወገን ስልጣንና ችሎታ ውስጥ ያሉ መሆን ይገባቸዋል። ማንም ከስልጣኑና ከችሎታው ውጭ የሆነ ጉዳይ ላይ ሊደራደር አይችልም። ከስልጣንና ችሎታ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መስጠትም መቀበልም አይቻልም። ድርድር ሰጥቶ መቀበል በመሆኑ በስልጣንና በችሎታ የተገደቡ ጉዳዮች ላይ መደራደር የሚባል ነገር የለም። ይህን ተደራዳሪ ወገኖችም የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ህዝብም ሊያስታውሱ ይገባል።