Artcles

ግድቡ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር ነው!

By Admin

June 13, 2017

ግድቡ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር ነው!

                                                              ደስታ ኃይሉ

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሩካ ቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ብርቱ ጥረት እያደረገች ነው። በዳርፉር፣ በሱዳን አብዬ፣ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለችውን ጥረት መጥቀስ ይቻላል። አገራችን ይህን ጥረት የምታደርገው የአካባቢው ሀገራት ሰላም ሆነው ከተፈጥሮ ፀጋቸው በጋራ እንዲቋደሱ ካላት አስተሳሰብ የመነጨ ነው። ሀገራቱ ከሰላም የሚገኘውን ጥቅም እንዲያጣጥሙ ለማድረግ ከምታደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ የህዳሴው ግድብ አንዱ ማሳያ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሌላውን ሀገር የውሃ ዋስትና የማይጻረር እንዲሁም በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት መርህ የመጠቀም መብታቸውን በማረጋገጥ ያለባቸውን የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለመቅረፍ ስምምነት ላይ መድረስ ችለዋል— ምንም እንኳን በግብፅና በሱዳን  በኩል ይህ ሰናይ እሳቤ ተቀባይነት ሳያገኝ ዛሬም ድረስ ቢቆይም፡፡

ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል፡፡ ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡

በታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መሰረቱ የተጣለው ይህ ግድብ፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ደግሞ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል፡፡ ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንደሚያደርገው የሚያመላክት ነው።

እዚህ ላይ ልብ ማለት ያስፈልጋል። እርሱም ግድቡን በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመጽዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ – ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የይቻላል መርህን በተግባር ማዋል ያስቻለ ብሎም ከራስ አልፎ በሚደረገው ሽያጭ የህዝቡን ውለታ በዕድገት የሚመልስ በመሆኑ ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል፡፡

ግና የምናድገው ለብቻችን አይደለም።እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ መኖርን፣ ማደግንና መበልጸግን ከማንም በላይ የምንቀበልና የማንነታችን መገለጫም ነው። ልክ እንደ ሌሎች ለብቻችን እንጠቀም ብለን አናውቅም። እናም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታችን ትኩረትም ማንንም ለመጉዳት ያለመ እንዳልሆነ ማንኛውም አካል ሊያውቅ ይገባል፡፡ አብሮ መብላትና ተያይዞ ማደግ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት መለያ ባህሪ እንደሆነም ጭምር፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊው የእኩልነትና የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ላደረገው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊነት በግምባር ቀደምትነት የተሰለፈችውም ለዚሁ ነው፡፡ መላው ዜጎቿም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እያበረከቱ የሚገኙት ደግሞ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ የህዳሴውን ግድብ ፋይዳ የተገነዘቡ የጎረቤት ሀገሮች መንግስታት ድጋፋቸውን ከማሳየትና አቋማቸውን ከማንጸባረቅ አልፈው፤ የግብጽ መንግስትን ኢ- ፍትሃዊ አቋም በግልጽ እስከማውገዝ ደርሰዋል።

የተፋሰሱ ሀገራት በዚህ ብቻ አልተወሰኑም። በተፈጥሯዊው የውሃ ሃብታቸው በእኩልነትና ፍትሃዊነት መርህ የመጠቀም መብታቸው የማይገደብ መሆኑን ሊገነቧቸው ያቀዷቸውን ፕሮጀክት ይፋ በማድረግ ቁርጠኝነታቸውንም አመላክተዋል፡፡ ይህ አቋማቸውም የግድቡን ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ በግልጽ ማመላከት የቻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት ጠንካራ አቋምንም እንዲሁ፡፡

ግና እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እርሱም “ዕውን ግድቡ የግብጽ መንግስት ባለስልጣናት እንደሚሉት ሀገራዊ ጥቅማቸውን ይጎዳልን?” የሚል ነው።  እሰቲ ለማንኛውም ሃቁን በመጠኑ እንመርምረው— “ከቃል ይልቅ ስራ ጉልቶ ይወጣል” እንዲል የሀገራችን ሰው።  

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲከናወን የተወሰነው ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ተጠግቶ ነው፡፡ ይህም ግድቡ ለመስኖ አገልግሎት ሊውል እንደማይችል ያሳያል።

እናም ውሳኔው የኤሌትሪክ ሃይልን የማመንጨትና የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ሀገራዊ ልማትን ከማፋጠን ውጪ፤ እነርሱ እንደሚሉት “በውሃ ለማስጠማት” ያለመ እንዳልሆነ በቀላሉ የሚያስገነዝበን ነው፡፡ ሌላ ምክንያት ላክል፡፡…የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦች ሃይልን ከማመንጨት ባሻገር፤ አንድ ጠብታ ውሃም ቢሆን እንደማያባክን ሁሉም ጠንቅቆ የሚያውቀው ዕውነታ ነው፡፡

ግድቡ የማንኛውም ሀገር ጥቅም ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ የማያበረክትና የማይነካና የጉዳት መጠኑም እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይልቁንም ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ በየዓመቱ ሲደርስ የቆየውን ከፍተኛ የውሃ ትነት መጠን የሚያስቀር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አስምረውበታል። እናም ይህ ምስክርነት የግብፅን “የይጎዳኛል” እሳቤ ዋጋ የሚያሳጣው ነው።

ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገራችን አልፎ ሌሎች ሀገሮችም መጠናቀቁን በተስፋ የሚጠብቁት ፕሮጀክት እየሆነ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የምትተለውና ከሁሉም ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማደግ ያላት ቁርጠኛ አቋም ፍሬ እያፈራ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል። ሀገራችን ለሩዋንዳ 400 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርማለች።

ሱዳንና ኬንያም ቢሆኑ የህዳሴውን ግድብ መጠናቀቅ በተስፋ እየተጠባበቁ ነው። ቀደም ሲል 100 ሜጋ ዋት ከኢትዮጵያ የወሰደችው ካርቱም እንዲሁም 400 ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጫ የምትጠብቀው ናይሮቢ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለባቸውን የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እንደሚያቃልላቸው በማመን ፍፃሜውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የ100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ከሀገራችን በመውሰድ ተጠቃሚ በመሆን ላይ የምትገኘው ጅቡቲም ተጨማሪ ሃይል ለመውሰድ የግድቡን ግንባታ ፍፃሜ እየጠበቀች መሆኑ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም።

ታዲያ እነዚህ ሁሉ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦቶች ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር ከሌሎች ሀገራት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ በጋራ የማደግ ትልሟን የሚያሳዩ መሆናቸውን ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል።